Thursday 28 April 2011

የየዋሖቹ ዘመን

አንድ ሻምበል ሄንሪ ዳርሊ የሚባል፣ አገር እቀኛለሁ፣ አረመኔ አሰለጥናለሁ ባይ እንግሊዛዊ በ 1899 ዓመተ ምሕረት ከአሁኗ ኡጋንዳ ተነስቶ በደቡብ-ምዕራብ ኢትዮጵያ በኩል ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ተልኮ ሲጓዝ፤ በመንገድ ገጠሙኝ ከሚላቸው ሁኔታዎች አንዱ ከዚህ የሚከተለው በ'ባሪያዎችና የዝሆን ጥርስ' (Slaves & Ivory)ብሎ በሠየመው መጽሐፉ ላይ ያሰፈረው አስቂኝ ነው።


ከ ጅማ የተነሳን ዕለት ከበቅሎዎቼ ሁለቱ አምልጠው የሰው ጤፍ ማሳ ውስጥ ይገቡና እሽቱን በልተው ሲጠግቡ [የተፈጥሮ ግዴታቸው ነውና] ሌላውን እየንተንከባለሉ የዚያን የምስኪን ገበሬ ምርት አጥፍተውበት ኖሯል። እኔ ደግሞ ከማረፊያ ግቢዬ መጥፋታቸውን ስገነዘብ ፈላጊዎች ልኬ፣ ሰዎቼ ወዲያው በቅሎዎቹን እየነዱብቅ ሲሉ አብረዋቸው ብዙ ኦሮሞዎች እየተጯጯሁ በግርግር ተከትለዋቸው እግቢዬ ገቡ። ታዲያ የጤፉ ባለቤት የበቅሎዎቹ ጌታ እኔ መሆኔን ሲገነዘብ፣ ሸማውን አጣፍቶ ተጠጋኝና እሱ በቁጣ መሰል ጩኸት፣ አጃቢዎቹ ደግሞ አየር ለመሳብ ባረፈ ቁጥር በጭብጨባና ሆሆታ ብዙ ደነፉብኝ። እኔ ግን ኦሮምኛ ባለማወቄ ምን ጉድ እንደተፈጠረ ሊገባኝ አልቻለም። ደግነቱ ከተከታዮቼ አንዱ በስንት መከራ ድምጹን ለማሰማት ችሎ ሰውዬው ችግሩ ምን እንደሆነ ገለጸልኝ።

ለካስ እንዲህ ያቁነጠነጠውና ደም-ሥሩ እስኪገተር ያስደነፋው የኔ በቅሎዎች ማሳውን ያጠፉበትን ኪሣራ እንድከፍለው ኖሯል። እኔም ወዲያው ገንዘብ ያዢዬን ጠራሁና አንድ ብር ባሰጠው፣ ብሩን እያገላበጠ አፉ እስኪደርቅ ድረስ በዚያው ኦሮምኛው ይለፈልፍ ጀመር። 'ለጉዳቴ በቂ አይደለም' የሚለኝ መሰለኝና አንድ ብር አስጨመርኩለት። እንዲያውም ባሰበት! እኔም ጩኸቱ ሰለቸኝና 'በቃ ሁለት ብር ጨምርለት አልኩ፡' አራት ብር
አይበቃኝም ካለ ወደዳኛ ሄዶ ይክሰሰኝ በሉት አልኩና ደመደምኩ።

ገበሬው አራት ብሩን በጁ ይዞ፣ ተስፋ በቆረጡ ዓይኖቹ ካተኮረብኝ በኋላ ጩኸቱን አቁሞ በቅሎዎቼ ካታሰሩበት ፈታና እየነዳ ከግቢዬ ወጥቶ ሰደድ ብሎ እዚያው ማሳው ወስዶ ለቀቃቸው። የኔ ሰዎች ታዲያ በጉልበት ቀምቶ መውሰዱ ነው ብለው ሊያስጥሉት አካኪ ዘራፍ ብለው ነበር። ተዉት! እንደዚህ በዚህ ሁሉ ሰው ፊት ሊሰርቃቸው አይችልም። እስቲ እልሑ ይውጣለት ብዬ አረጋጋኋቸው እንጅ።

በኋላ ሲያስረዱኝ ለካስ ሰውዬው ካሣ ብሎ የገመተው (የጠበቀውም) አምሣ ሣንቲም የማያወጣ ሁለት አሞሌ ጨው
ኖሯል። አንድ ብር ሲሰጠው እንደዚያ ያጉረመረመው ለካ 'ለዚህ ምንዛሪ አሁን ከየት እንዳመጣልህ ነው?' እያለ ኖሯል። ሁለት ብር ሲሆንለት ደግሞ የባሰውን 'ምን አይነት ደንቆሮ ሰው ነህ? ብሎ እየተገረመ ኖሯል። ይሔም አልበቃ ብሎ አራት ብር ሲሆን በቅሎዎቹን መልሶ ማሳው ውስጥ የከተታቸው ለካ፣ 'በል እንግዲህ ከማሳው እህል ዋጋ እጅግ በላይ አድርገህ ከፍለሃልና ሒሣብህ አይቅርብህ! በቅሎዎችህም የቀረውን እንደልባቸው ይብሉትም ይንከባለሉበትም" ማለት ኖሯል።
እንግዲህ ያ ዘመን በአገራችን የሚመረጠው መገበያያው የማርያ ጠሬዛ (ጠገራ) ብር እና አሞሌ ጨው የነበረበት ዘመን፤ [ዳግማዊ ምኒልክ ከዚህ አጋጥሚኝ 13 ዓመት በፊት አንድ ብር፣ የብር ግማሽ፣ የብር ዕሩብ፣ የብር ስምንተኛ እና የብር ሃያኛ ዋጋ የነበራቸውን ሣንቲሞች አሰራጭተው ቢሆንም እንኳ!] አባቶቻችን ሐቅን ተመርኩዘው መብታቸውን ከማስከበር ወደኋላ የማይሉበት፤ በሐቅ በወዛቸው ያላፈሩትን የማንንም ንብረት የማይመኙበት ዘመን መሆኑን ልብ ይሏል።

ይህ ክስተት ዛሬስ ቢሆን ኖሮ? ምን ዓይነት ዝገባ ይጻፍ ይሆን?
የዚህን ተጓዥ አጋጥሚኝ ሳነበው የሳቅኹትን ያህል ያስገርመኝ ይሆን?
ያ የጤፍ ማሳ በትንሹ ተገምቶ አራት አምሥት ኩንታል እህል ያመርታል ብንል፣ አንዱ ኩንታል ከሺ ብር በላይ በሚያወጣበት በዚህ ከይሲ ዘመናችን፣ ያ ምስኪን ሐቀኛ የኢትዮጵያ ገበሬ ከሞት ዕንቅልፉ ቢነቃ ምን ይል ይሆን?

መልሱን ለየአንዳንዳችን ልቦና እተወዋለሁ።

በሌላ የታሪክ አውሎ ነፋስ ጽሑፍ እስከምንገናኝ ድረስ የሎንዶኑ ቡልጌ ነኝ።