Sunday 9 December 2012

የመቅደላው ዮሐንስ እሸቴ በሎንዶን



መቶ አርባ-አምስት ዓመት ያስቆጠረው መቅደላን ስናነሳ መቼም ዓፄ ቴዎድሮስና ታላቁ ጀብዷቸው፤ ሮበርት ናፒዬር እና እንግሊዞች በሀገራችን ላይ ያካሄዱት ከ‘ግዳጅ ወሲብ’ ጋር የማይተናነስ ደፈራ እና ብዝበዛ፣ የነደጃች ካሣ ምርጫ ሴራ፤ የልጅ ዓለማየሁ መሰደድና በለጋ ዕድሜው ከሀገርና ከዘመድ ተለይቶ ሳለ የሕይወቱ በአጭሩ መቀጠፍ፣ ወ.ዘ.ተ. ይታወሱናል። ስለዚያ ወቅት ታሪክ በጥልቀት ለሚያጠና፣ አያሌ መጻሕፍትና ማስታወቻዎች፤ አብዛኞቹ በነጮቹ፣ አንዳንድም በኛው ሰዎች ተጽፈው በታሪክ ማኅደር ውስጥ ይገኛሉ።

ታዲያ እነዚህን መጻሕፍት ስንመረምር፣ ከዋነኞቹ ተዋንያን ውጭ አልፎ አልፎ በጨረፍታ፤- መጠሪያ ስም ያልተሰጣቸው አያሌ ኢትዮጵያውያን ሲኖሩ አንዳንዴ ደግሞ ከታሪክ መዛግብት መኻል አንዳንድ የአበሻ ስሞች ገጹ ላይ ብልጭ ሲሉ እናያቸዋለን። በምንም መልኩ ቢሆን እነዚህን አበሾች ያንሷቸው፤ ለታሪክ ተማሪው/ተመራማሪው፤ በስደት ዓይናችን ለምናጤናቸው ግን ማን ነበሩ? በአገሪቱ ታሪክ ላይ የነበራቸው እውነተኛ ሚና ምን ነበር? መጨረሻቸውስ ምን ሆኖ ይሆን? የሚሉትን ጥያቄዎች ስለሚጭሩ ለግል እርካታና ጠለቅ ላለ ግንዛቤ መዳበር የሚረዳ ቅኝት ነው። አርኪ መልስ ግን እንደ ማስረጃዎቹ እጥረት የህልም ሩጫ ነው።

መቸም የነጮቹ ግምገማ አልፎ አልፎ በጥሩ መልክ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ ግን በዚያው በዘረኝነት በተበከለው ብዕራቸው ሲለቀልቋቸውና ቀጣፊ፡ አታላይ፡ ዋሾ፡ ዘራፊ፡ ከሀዲ፡ አድርባይና ቀላማጅ ከሚሉ ቅጽላት ጋር እያጣመሩ እንደ ዐረመኔ ገልቱ ሲገልጿቸው ቢሆንም በኢትዮጵያዊ አመለካከታችን ከውስጡ ፈልቅቀን ለማውጣት የምንችለውን ቁም ነገር ግን ሊሸፍኑት አልቻሉም።

በዚህ መልክ ከምንተዋወቃቸው ኢትዮጵያውያን መሐል በከፊሉ፦
ሰናፌ የተወለዱት የደንቀሌው ባላባት ልጅ፣ በአረብኛ ቋንቋ የተካኑት እና ሚሲዮናውያኖቹ ካይሮ ወስደው ክርስትና ያነሷቸው ሳሙኤል ጊዮርጊስ፤ ከንጉሥ ሣህለ ሥላሴ፤ ከዓፄ ቴዎድሮስ እና ከዓፄ ዮሐንስ ጋር ታሪካቸው ተሰባጥሮ የሚገኝ ሲሆን በተለይም በመቅደላ ክስተት በባልደረባነት፤ በአስተርጓሚነት፤ በተላላኪነት፤ ወዘተ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።

ሁለተኛው፤ በልጅነታቸው ዘመን አገር ለመዳሰስ የመጣው ሄንሪ ለፌቭር የተሰኘው ፈረንሳዊ ይዟቸው ወደአገሩ ከወሰዳቸው በኋላ እዚያው ሲማሩ በነበሩበት ወቅት ከፈረንሲሱ ንጉሥ ሉዊ ፊሊፕ ጋር መልካም ግንኙነት መሥርተው የነበሩ፤ በኋላም ወደእንግሊዝ አገር ተጉዘው ትምህርታቸውን ሲያዳብሩ ቆይተው በካይሮ በኩል ወደአገራቸው የተመለሱት የአድዋው ተወላጅ ዐለቃ  ማኅደረቃል ናቸው። ዐለቃ ማኅደረቃል በጠቅላላው ለ፲፩ ዓመታት በውጭ የቆዩ ሲሆኑ፣ የዓፄ ቴዎድሮስ አስተርጓሚ ሆነው ያገለግሉ እንደነበር ተዘግቧል።

ሌላው ደግሞ በልጅነት ዕድሜያቸው ከወንድማቸው ጋር በሚሲዮናውያኑ ወደ ሕንድ ተወስደው፣ እዚያው ተምረው ሲመለሱ መጀመሪያ በየደጃች በዝብዝ ካሣ ጸሐፊና አስተርጓሚ የነበሩት፣ በኋላም ጌታቸው ዓፄ ዮሐንስ ከተባሉ በኋላ ደግሞ ነጮቹ “ጠቅላይ ሚኒስትር” የሚሏቸው ፤ ወደ እንግሊዝ አገርና ንግሥት ቪክቶሪያ “ልዩ መላክተኛ” ተደርገው የተላኩት፣ እንግሊዝኛ ተናጋሪው ምርጫ ወርቄ ናቸው። እኒህ ሰው እንግሊዞች ወደመቅደላ ሲያልፉ መስፍናቸውን ወክለው ከጦር ዓለቆቹ ጋር በመደራደር የትግራይ ሕዝብና ሹማምንት በግብረ አበርነት መንፈስ እንዲተባበራቸው ያደረጉና በኋላም ሮበርት ናፒዬርና ደጃች ካሣ ማክሰኞ የካቲት ፲፰ ቀን ፲፰፻፷ ዓ/ም ግንባር ለግንባር ተገናኝተው ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ያደረጉ ናቸው።

ሌሎች ደግሞ በጦርነቱ ምክንያት እንደ ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ፣ ወላጅ አልባ የሆኑ ወይም እዚያው ምሽጉ ውስጥ ተጠግተው የተገኙ ወይም ደግሞ ነጭ እስረኞቹን ተጠግተው ያገለግሉ የነበሩ፤ ጦርነቱ ሲገባደድም ነጮቹን ተከትለው የተሰደዱ ሕፃናት ነበሩ። አዛዥ/ሐኪም  ወርቅነህ  እሸቴ በዚህ ጊዜ የሦስት ወይም የአራት ዓመት ልጅ ነበሩ። ከጦሩ መልስ ወደ ሕንድ አገር ተወስደው እዚያው ያደጉ፤ የኖሩ እና በቀዶ ጥገና ሙያ የተሠማሩ ሰው ሲሆኑ አሳዳጊ አባቶቻቸው በሰጧቸው ስሞች ቻርልስ (በወሰዳቸው መኮንን ስም) ማርቲን (ባሳዳጊያቸው ሐኪም ስም) (Charles Martin) ይባሉ ነበር። አዛዥ ወርቅነህ ለመጀመሪያ ጊዜ በዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ዘመን ወደኢትዮጵያ ተመልሰው እንደነበርና ንጉሠ ነገሥቱም በታመሙ ወቅት ከሚያክሟቸው የጤና ባለሙያ አንድ እንደነበሩ ታሪክ ይዘግባል። በኋላም በሎንዶን የኢትዮጵያ ዋና መላክተኛነቱን ሥልጣን ተሹመው የፋሽስት ኢጣልያ መንግሥት የኢትዮጵያን ግዛት በሥሩ ማስተዳደር እስከጀመረ ድረስ ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

እንግዲህ እነዚህ በታሪክ አውሎ ነፋስ እየከነፉ በሕሊና ልቦናችን የምንቃኛቸው ኢትዮጵያውያን በሙሉ የየግል ታሪካቸው ትንተና እንደሚያስፈልገው አንዳችም ጥርጣሬ ባይኖርም፤ የዛሬው እንግዳዬ የመቅደላ ጦርነት ሲያከትም የአሥራ አራት ወይም የአሥራ አምስት ዓመት ወጣት የነበረው ዮሐንስ እሽቴ ነው። ይኼንን ኢትዮጵያዊ የምንተዋወቀውም ድምጹም የሚጠፋብን በንግሥት ቪክቶሪያ ዘመን፤ በአንድ መጽሐፍ ላይ ብቻ፤ በብሪታንያ ርዕሰ ከተማ ምዕራባዊ ጎን፣ ስቴይንስ(Staines) እና ሪችሞንድ (Richmond) ከሚባሉ መንደሮች ነው፤ እንዲሁም በኮቬንት ጋርደን እና በዋይት ሆሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቢሮ ነው።  

ዮሐንስ የዬት አገር ተወላጅ እንደነበረ ባናውቅም፤ ሰኔ ፳፬ ቀን ፲፰፻፶፪ ዓ/ም በንግሥት ቪክቶሪያ ተሹሞ ወደ ዓፄ ቴዎድሮስ የብሪታኒያ ሁለተኛ ቆንስላ ተብሎ[1] ወደአገራችን የተላከውና በአንዳንድ ምሑራን አስተያየት ለጦርነቱ መነሻ ክብሪት ነበር የሚባለውን ቻርልስ ዳንከን ካሜሮን (Charles Duncan Cameron, Esq.,)  መቅደላ ላይ ተጠግቶ ያገለግለው እንደነበርና ከእንግሊዞችም ድል በኋላ ይሄንኑ ካሜሮንን ተከትሎ በግብጥ በኩል አድርጎ ወደ እንግሊዝ አገር እንደገባ ተራኪው አስፍሮታል። ካሜሮን ከመቅደላ እስራት ሚያዝያ ፬ ቀን ፲፰፻፷ ዓ/ም ተፈቶ ወደብሪታኒያ የተመለሰው በሐምሌ ወር ፲፰፻፷ ዓ/ም እንደነበር እና በስድስት ወሩ ጡረታውን አስከብሮ ኑሮውን ዠኔቭ ላይ መሥርቶ ሲኖር እዚያው በስዊሷ ከተማ ግንቦት ፳፫ ቀን ፲፰፻፷፪ ዓ/ም እንደሞተ ከሌላ የታሪክ መዝገብ እንረዳለን። ታዲያ ዮሐንስ ጌታውን ተከትሎ ወደዠኔቭ ተጉዞ ይሆን? ከሆነስ ካሜሮን ሲሞት እሱ እንዴት ሆነ? እንቀጥልና የሰር ኤድዋርድ ትረካ ስለዚህ ምዕራፍ ምን እንደሚል እንየው።

የዮሐንስ እሸቴን (በደራሲው አጻጻፍ፣ JOHANNES SCHATEY) እጅግ አጭር ታሪክ የሚዘግበው፤ በወቅቱ በብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይሠራ የነበረውና “በዚያ ወቅት የቆንስል ካሜሮን የግል ወኪል” ነበርኩ የሚለን፤ ለብዙ ዓመታት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኃላፊ የነበረው ሰር ኤድዋርድ ኸርትስሌት (SIR EDWARD HERTSLET, K.C.B.) ነው። ይኼም ዘገባ እ.አ.አ በሺ ዘጠኝ መቶ አንድ (፲፰፻፺፫ ዓ/ም) በታተተመው “የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትውስታዎቼ” (RECOLLECTIONS OF THE OLD FOREIGN OFFICE) በተባለ መጽሐፉ ላይ ይገኛል።

ሰር ኤድዋርድ ዮሐንስ እሸቴን የሚያስተዋውቀን፤ “ሰር ሮበርት ናፒዬር የብሪታኒያን ሠራዊት እየመሩ መቅደላ ምሽግ ሲደርሱ ወደ ንጉሠ ነገሥት ቴዎድሮስ እስረኞቹን በፈቃዳቸው ካልፈቱ መቅደላን በኃይል እንደሚደመስሱትና እስረኛ ወገኖቻቸውን ነፃ እንደሚያወጧቸው መላክ የፈለጉትን ደብዳቤ ‘ማን ያድረስ?’ የሚለው ጥያቄ ተነስቶ እንደነበር መስማቴን አስታውሳለሁ።” በሚል ሐረግ ሲሆን፤ ቀጥሎም “ከእስር በፊትም በእስር ጊዜም የካፕቴን ካሜሮን አገልጋይ የነበረው፣ በግምት የአሥራ አራት ዓመቱ ወጣት፣ ሎጋ፣ መልከ-መልካሙ ዮሐንስ እሸቴ በራሱ ፈቃደኛነት ‘እኔ አደርሰዋለሁ’ ብሎ፤ ለራሱ ደህንነት ምንም ሳያስብ፣ ደብዳቤውን አደረሰ” ይለናል። ሰር ሮበርት ናፒዬርም ለዚህ ጀብዱው ፳፭ ይሁን ወይም ፶ የእንግሊዝ ፓውንድ እንደሸለሙት ተነግሮኛል ይልና በኋላ ይህ ኢትዮጵያዊ ወጣት ካሜሮንን ተከትሎ ወደብሪታኒያ ለመጓዝ ሲነሳ ግማሹን ገንዘብ ለ’ወላጆቹ’ ሰጥቶ ግማሹን ይዞ ተጓዘ ይላል፣ ሰር ኤድዋርድ።

በወቅቱ መቅደላ ልይ ታስረው ከነበሩት ነጮች አንዱ፤ ሐኪም ሄንሪ ብላንክ ደግሞ፣ ሐምሌ ፲፯ ቀን ፲፰፻፷ ዓ/ም በታተመው “በአበሻ ምድር የእስረኝነት ትንታኔ” (A Narrative of Captivity in Abyssinia) በተሰኘው መጽሐፉ ላይ፤ ሰር ሮበርት ናፒዬር ስለላከው ደብዳቤ ሲተርክ፣ “ከጥቂት ቀናት በፊት የጦሩ ጠቅላይ አዛዥ ወደንጉሠ ነገሥቱ ደብዳቤ እንዲልኩ” ጄኔራል ሜሪዌዘር እንዲያስታውሷቸው ብዬ የላኩት ወጣት ልጅ ዛሬ [ሚያዝያ ፫ ቀን ፲፰፻፷ ዓ/ም] ከክቡር ጠቅላይ ጦር አዛዡ ለንጉሠ ነገሥቱ የተጻፈ ደብዳቤ ይዞ ሰፈራችን ደረሰ” ብሏል። ይሄንን መላክተኛ እገሌ ብሎ ባይጠራውም የሁለቱን ደራስያን ዘገባዎች ማዛመድ የሚቻል ይመስለኛል።

ሰር ኤድዋርድ የዮሐንስ ‘ወላጆች’ እነማን እንደነበሩ ወይም ዮሐንስና ካሜሮን እንዴት? በየት? ከማን ጋር? መቼ? ከኢትዮጵያ ተነስተው ግብጽ እንደደርሱ አይነገረንም። የሰር ኤድዋርድ ዘገባ ግን በቀጥታ ግብጽ ምድር ያገባንና ከዚያም ወደ እንግሊዝ አገር ለመነሳት ሲዘጋጁ ካፕቴን ካሜሮን ዮሐንስን ‘በጣም አሸብራቂ’ ልብስ - ሰማያዊ የግብጽ እጀ-ጠባብ ሱሪ፣ በብር አዝራሮች ያሸበረቀ ሰደሪያ፣ አረንጓዴ እጀ-ሰፊ የግሪክ ኮት እና ቀይ የቱርክ ‘ፌዝ’ (ኮፊያ) አልብሶት ነበር ይለናል። ሎንዶንም እንደደረሱ የዮሐንስ አሸብራቂ ልብስና የበለጠውንም እጅግ ብሩሕ ፈገግታው ብዙ ትኩረት እንደሳበና የካፕቴን ካሜሮን ወዳጆች በየተገኙበት ቦታ በተለይም በሴቶቹ በኩል የላቀ ተፈላጊነትና እውቅና ሰጥቶት እንደነበር ያወሳል።

በዚያ ወቅት፤ ከአንድ ስፍራ ላይ ሁለት በእድሜም ሆነ በሚጠብቃቸው የሕይወት ዕጣ ፈንታ የተለያዩ ኢትዮጵያውያን፤ በተለያዩ እንግሊዛውያን ከአገራቸው ተወስደው እንደነበር ልብ ይሏል። አንዱ ወደሕንድ ሲወሰድ ሌላኛው ደግሞ እንግሊዝ አገር ላይ የምናገኛቸው አዛዥ ወርቅነህ እሸቴ እና ዮሐንስ እሸቴ ሲሆኑ፤ ከስም አልፈው ታላቅና ታናሽ ወንድም ሊሆኑ ይችሉ ይሆን? ሁለቱም በጊዜው መቅደላ ላይ ታስረው የነበሩት የነጋድራስ እሸቴ ወልደማርያም ልጆች ይሆኑ?

በሎንዶን “ከዕለታት አንድ ቀን፣” ይላል ሰር ኤድዋርድ “ዮሐንስ ካሜሮንን ተክትሎ በሰረገላ ‘ሪጀንት ስትሪት’(Regent Street) በተባለው ጎዳና ካሉ መደብሮች ውስጥ ከተገበያዩ በኋላ ሲወጡ ከመደብሩ አሻሻጭ ልጃገረዶች አንዷ ለዮሐንስ በስጦታ ፊሽካ አበረከትለች” ይለንና “ብርቅዬ የሆነበት ዮሐንስ ሰረገላው ላይ ሆኖ ፊሽካውን ያቀልጠው ጀመር” ታዲያ አላፊ አግዳሚው የ ሎንዶን ሰው የፊሽካው ጩኸት ትርጉሙ ስላልገባው ግራ ተጋብቶ እንደነበር ዘግቦታል።

ዮሐንስ በእንግሊዝኛ ቋንቋ መግባባት ቢችልም በንባብ ዕውቀቱን ለማዳበር የነበረውን ጥረት ሰር ኤድዋርድ ሲያስረዳን “ካፕቴን ካሜሮንን እየተከተለ እኔም ቤት ይመጣ ነበር፤” ይልና “ከኪሱ የመሠረተ ንባብ ደብተሩን ያወጣና የማያውቃቸውን ሰዎች እንኳ ‘ማንበብ አስተምሩኝ’ይል ነበር” በሚል መልክ መጽሐፉ ላይ አስፍሮታል። ለጥቆም “ወጥ-ቤቷም ‘ኤሊዛም’ (ከቤት ሠራተኞቹ አንዷ መሆኗ ነው) ሁሉም የቤት ሠራተኞች ማንበብ ይችላሉ፤ እኔንም አስተምሩኝ” እያለ ዮሐንስ ይማለድ እንደነበር ይነግረንና “ታዲያ ከማንም ሰው ብዙ እርዳታ ያገኘ አይመስለኝም።” በማለት ይደመድማል።

ካፕቴን ካሜሮን እያስከተለው ወደውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ያመጣው እንደነበረና ወደቆንስላው ኃላፊ ቢሮ ሲሄድ ዮሐንስን ሰር ኤድውራድ ቢሮ ትቶት በሚሄድበት ጊዜ “ዮሐንስ እኔ ምንጣፍ ላይ ይዘረጋ ነበር” ታዲያ ከዕለታት አንድ ቀን “ወደቢሮዬ ስመለስ ዮሐንስ ምንጣፌ ላይ እንደተጋደመ እሳት ሲሞቅ እንቅልፍ ጭልጥ አድርጎት አገኘሁት።” ይላል

በዚህ ወቅት፣ እንደ ሰር ኤድዋርድ ዘገባ፤ ካፕቴን ካሜሮን ስቴይንስ (Staines) በሚባለው አጥቢያ ካፕቴን ዲ ብቻ በሚለው ከእህቱ ባል ጋር ተዳብሎ ይኖር እንደነበር ይነግረንና ካሜሮን ግን ከተማው ውስጥ ሆቴል ማደር ያዘወትር ነበር ይለናል። ዮሐንስ ታዲያ ካፕቴን ዲ ወሮ በላ ይዘርፈዋል ከሚል ሥጋት በመነሳት እንዳይወጣ ቢከለክለውም እንኳ አካባቢውን ለብቻው እየዞረ ይውል እንደነበር፤ ያለችውንም ገንዘቡን ሁሌ በኪሱ እየያዘም ይወጣ ነበር ካለን በኋላ አንድ ቀን ካፕቴን ዲ በጣም ተቆጥቶት እምቢ ያለ እንደሆን በሰንሰለት እንደሚያስረው ዛተበት ብሏል። ጌታው ካፕቴን ካሜሮን መቅደላ ውስጥ ለዘጠኝ ወራት እግሩን ከጁ ጋር በሰንሰለት ታስሮ እንደነበር የቅርብ ትውስታው የነበረው ዮሐንስ ታዲያ ‘በሰንሰለት ትታሰራለህ’ ሲባል እድል እስኪያገኝ አድፍጦ ከቆየ በኋላ ከስቴይንስ ጠፍቶ ወደአሥር ማይል ያህል በግሩ ተጉዞ ሪችሞንድ (Richmond) ወደነበረው የሰር ኤድዋርድ ቤት ድረስ ኮብልሎ ገባ።

ሰር ኤድዋርድ ስለዚህ ጉዳይ ሲያወሳ “አንድ ቀን ከሥራዬ ስገባ ዮሐንስን በጣም ተከፍቶና የካፕቴን ዲን ቤት ጥሎ በመምጣቱ ምን ዓይነት ቅጣት ይደርስብኝ ይሆን በሚል ተጨናንቆ እቤቴ አገኘሁት፤” “ነገር ግን በደስታና በርኅራኄ እንደተቀበልነው ሲገነዘብና ራቱን አብልተን እኔው ቤት እንደሚያድር ሲገባው ሰውነቱ ሁሉ ተፍታቶ ገጽታው እጅግ በጣም ፈካ አለ።” ይላል ይሄ እንግሊዛዊ። ዳሩ ግን የዚህ የ’ጥቁር’ ልጅ በአንድ ጣራ ሥር እነሱ የሚተኙበት ፎቅ ላይ መተኛቱ ያላስደሰታቸው የሰር ኤድዋርድ ገረዶች እዚያው ቀዝቃዛ ማዕድ ቤት ውስጥ እንዲያድር ፈረዱበት። እታዘዘበት መሬት ላይ ከማንቀላፋቱ በፊት ግን መኝታው ጋ ቆሞ ለቅዱስ ጊዮርጊስ የሕሊና ፀሎት እንዳደረሰ ሁሉ ሲነግረን ስለዮሐንስ የሚተነተንልንን ታሪክ በኢትዮጵያዊ ዓይነ ልቦናችን እንድንገነዘበው ይረዳናል።

በማለዳ የተነሳው ዮሐንስ የተነፈሳቸው ቃላት፤ “ወደጌታዬ መሄድ እፈልጋለሁ” ሲሆን ካፕቴን ካሜሮን በ ‘ኮቬንት ጋርደን’ (Covent Garden ) አካባቢ ያረፈበትን የሆቴል ስም ልብ አድርጎ አጥንቶት ስለነበር “አሽከሬ ይዞት ወደ ሪችሞንድ የምድር ባቡር ጣቢያ እንዲሄድና እስከ ‘ወተርሉ የምድር ባቡር ጣቢያ’ የሚያጓጉዘውን ካርኔ እንዲያስቆርጥለት አዘዝኩ” ይለናል። ለጋሪ አንድ ሽልንግ፤ በ’ወተርሉ’ ድልድይ ላይ መሻገሪያ ደግሞ ሁለት ‘ፔንስ’ እንድተሰጠውም አብሮ ይነግረናል።   

ከመድረሻው የምድር ባቡር ጣቢያ እስከ በ‘ኮቬንት ጋርደን’ አካባቢ የሚገኘው የጌታው ሆቴል ድረስ ስለሚገጥመው የዋጋ ድርድር ካስረዱት በኋላ ከመሳፈሩ በፊት “ጌታዬን እሆቴሉ ያላገኘሁት እንደሆነ፤ እርስዎ (ሰር ኤድዋርድ) ቤት፤ ነጩ ቤት፤ ውጭ ጉዳይ ቤሮ ልምጣ ወይ ቢለኝ እሺ ስላልኩት ተደሰተ። ነገር ግን ሆቴል የሚባለውን ጽንሰ ሐሳብ ስለማይረዳው ጌታው ያለበትን ቦታ ለማስረዳት ጥቂት ተቸግረን ነበር።” ይለንና ደራሲው “በመጨረሻ ግን ዮሐንስ በገጽታው ላይ የማወቅ ፈገግታ ተላብሶ “ይሄ ነገር ፣ እቤት ውስጥ ይገቡና እራት-አልጋ ይላሉ በማግሥቱ ቁርስ ይላሉ ፤ ባለቤቶቹ አንድ ፓውንድ - ሁለት ፓውንድ ይላሉ?>> አለ።” በዚሁ ተሳፍሮ ወደሎንዶን አመራ።

ሰር ኤድዋርድ ከሰዐታት በኋላ የዮሐንስን መድረስ አለመድረስ ለማረጋገጥ ወደ ካሜሮን ማረፊያ ሆቴል ሄዶ  ከካሜሮን ጋር ሲያወጋ በደስታ የተሞላው የዮሐንስ ፊት ከጓዳው ብቅ አለ።

ፀሐፊው፣ ዮሐንስ እሸቴ ለካፕቴን ካሜሮን የላቀ አክብሮታዊ ስሜት እንደነበረው ከገለጸልን በኋላ ግን፤- ካፕቴኑ “ከጊዜያት በኋላ ዮሐንስን እየሰለቸው ሳይመጣ አልቀረም” ይላል። በዘለቄታ ምን እንደሚያደርገው ግራ የገባው የሚመስለው ካፕቴን ካሜሮን፤ ከግብጽ ገዝቶለት የነበረው ልብስ  ሲያልቅበት የተራ የአሽከር ልብስ አለበሰው። ዮሐንስ ይሄ ‘ውርደት’ እና እንደውም ይባስ ብሎ ካሜሮን መጫሚያውን እንዲጠርግለት ስላዘዘው ተናዶ “እኔ ወደ እንግሊዝ አገር የመጣሁት ጫማ ለመጥረግ አይዶለም።” ብሎት ነበር። የሚያስደንቀው ግን ካሜሮን የአሽከር ደውል ደውሎ ወይን-ጠጅ ወይም ሌላ ጠንከር ያለ መጠጥ እንዲያመጣለት ሲያዘው፤ መጠጥ የሚወደውን ጌታውን እንደሚጎዳው በማሰብ፤ የታዘዘውን ካዘጋጀ በኋላ እንባውን እየጠረገ ቡጢውን በመጠጡ ላይ ይቃጣና በረድ ሲልለት አምጥቶ ያቀርብለት ነበር።

አንድ በጎ አድራጊ ወዳጅ ወደካቶሊካዊ ማሠልጠኛ ቤት ለመላክ ዝግጁ እንደነበረ/ች እና ሌላ ወዳጅ ደግሞ ወደ መደበኛ ትምህርት ቤት ለማስገባት ፈቃደኛነታቸውን ገልጸው ቢሆንም የዮሐንስ የመጨረሻ ዕጣው ግን ወደአገሩ መላክ እንደነበር ሰር ኤድዋርድ በቁጭት ይተርካል። እንደሱ አስተያየት ዮሐንስ እንግሊዝ አገር ቆይቶና ትምህርቱን ተከታትሎ  ቢሆን ኖሮ የብሪታኒያ ወዳጅ ይሆን ነበር ይለናል።

እንግዲህ ካሜሮን ወደ ዠኔቭ ሲጓዝ ይሁን አስቀድሞ፤ ብቻውን ይሁን ከባልደረባ ጋር፤ በሰላም አገሩ ይግባ ወይም እንደወጣ ቀረ የሚሉትንና ሌሎችንም ጥያቄዎች የሰር ኤድዋርድ ሐተታ ባይገልጽልንም ይሄንን ታሪክ ከመቶ አርባ አምሥት ዓመታት በኋላ ለምንከታተል ኢትዮጵያውያን የዮሐንስ እሸቴ ታሪክ አርኪ ድምዳሜ ባለማግኘቱ ያስቆጨናል። ካሜሮንን ተከትሎ ዠኔቭ ሄዶ ነበር ቢለንም እንኳ፤ ጌታው  ግንቦት ፳፫ ቀን ፲፰፻፷፪ ዓ/ም ዠኔቭ ላይ ሲሞት የዮሐንስ መጨረሻው ምን ነበር? ማለታችን አይቀርም።

ደራሲው ዮሐንስ ከእንግሊዝ አገር ከሄደ በኋላ ባዝ ከተማ ላይ ስለዚሁ ኢትዮጵያዊ ታሪክ ያነሳውን ትንታኔ ታዳምጥ የነበረች አንዲት ሴት ወይዘሮ ይሄንን ልጅ ማስተማሪያ እንዲሆን የሃምሳ ፓውንድ የዓመት አበል ለመመደብ መወስኗን እንዳስታወቀችውና ዮሐንስም ወደአገሩ መመለሱን ሲነግራት በጣም እንዳዘነች ያጫውተናል።

ዮሐንስን ሳስታውሰው ይላል ሰር ኤድዋርድ “አንድ ቀን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ውስጥ ከሌሎች መሪዎች ምስል መኻል የአበሻውን ንጉሥ ምስል ሲያይ “ወየው! ንጉሤ ዓፄ ቴዎድሮስ ነፃ መሪ መሆናቸውን እንደዚህ (በንግሊዞቹ) ታውቆላቸው እንደነበር ለማየት አብቅቷቸው ቢሞቱ ኖሮ አይቆጫቸውም ነበር።” ማለቱንም ነው በሚል ጥልቅ አበሻዊ ግንዛቤ ይደመድማል።



[1] The London Gazette; [p. 2719], Foreign Office, June 30, 1860