Monday 5 December 2011

‘እስከመቼ ፊትህን ታዞርብናለህ!’


ሰሞኑን በየድረ-ገጹ አበሾችን ወደየኮምፒውተር ሰሌዳቸው (ክትበ-ገበራቸው) እየገፋፋቸው ያለው በአገር ቤት ግብረ-ሰዶማውያን በኢትዮጵያ መንግሥት ድጋፍ ሊያደርጉት የተዘጋጁበት ስብሰባ ነው።

ስለዚህ ጉዳይ መጀመሪያ ያነበብኩት አዲስ-ሪፖርተር ባለፈው ዕሮብ ያወጣው ዘገባ ሲሆን፤ ይኼም የሃይማኖት አባቶች ጉዳዩን ለማውገዝ ያዘጋጁትን ውሳኔ ለጋዜጠኞች እንዳይስተላልፉ የጤና ጥበቃው ሚኒስትር ባልተገለጸ ምክንያትናዘዴ  እንዳስጣሏቸው ያበሰረው አንቀጹ ነው። ከዚኽ ቀጥሎ ያነበብኩት በዳንኤል ክብረት እይታዎች ላይእሳቱ ከሌለ ጢሱ አይታይምበሚል ርዕስ በዚያው ዕሮብ እለት ያሰፈረው መጣጥፍ ነው፡፡ ዳንኤል፣ ቅዳሜ ደግሞይህ ስም ክቡር ነው” በሚል ርዕስ ጠለቅ ያለ ዘገባ አስነበበን።

እነዚህ ትንተናዎች አያሌ አስተያየቶችን ስበዋል። አብዛኛዎቹ ተችዎች የዚህ ዜና አዎንታ ስሜታቸውን የቱን ያህል እንዳብሰለሰለውና እንዳሳረረው ከአጻጻፋቸው እንረዳለን። ግብረ-ሰዶማዊነት ከባህላችንም፣ ከሃይማኖታዊ እምነታችንም (በተለይ የኦርቶዶክስ ክርስትና) ጋራ የተጻረረ እና በጥብቅ የተከለከለ፤አስጸያፊ ድርጊት እንደሆነ እየደጋገሙ አስፍረውታል። አልፎ አልፎም ወቅታዊው የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግም ግብረ-ሰዶማዊነትን እንደሚከለክል ከነአንቀጹ በመጥቀስ ያስረዱንም አሉበት።

ዳንኤል “ኢትዮጵያ የሃይማኖት ሀገር ናት፡፡ ከ90 በመቶ በላይ የሆነው ሕዝቧ በእምነቱ ግብረ ሰዶምን ይቃወማል ብቻ ሳይሆን ይጸየፋል፡፡ የሀገሪቱ ሕጎችም ግብረ ሰዶማዊነትን በወንጀልነት ይፈርጃሉ፡፡ ከሕዝቡ እምነት ብቻ ሳይሆን ከባህሉ ጋርም የሚጣረስ ጉዳይ ነው፡፡” ብሎ እቅጩን ከነገረን በኋላ ከዚኽ ለጥቆም “ግብረሰዶማዊነትን ካልተቀበላችሁ፣ የግብረሰዶማውያንን መብት ካልደገፋችሁ አንረዳም እያሉ የሚያስፈራሩ ምዕራባውያን ኃያላን አሉ፡፡ ራሳችንን አጥተን የሚመጣ ርዳታ ለቀብር ማስፈጸሚያነት ብቻ የሚውል ነው፡፡ እናም እንዲቀርብን እንንገራቸው፡፡” በማለት የችግሩን መፍትሄ በከፊልም ቢሆን ሲጠቁም፤ ማንነታችንን እንወቅ፣ የሰፊውን ሕዝባችንን እምነትና ባህል የሚያረክሱ፣ የሚበክሉ፣ ባዕዳዊ ልምዶችን በስመ-ሥልጣኔ ወይም እርምጃ ለሣንቲም ብለን እየተቅበልን እራሳችንን አናዋርድ፣ አንግደል፣ አንቅበር እያለን ነው ያለው።

አንዱ ተች ደግሞ ምዕራገ ጸሎት፣ ዲቦ ቅድስት ድንግል ማርያም በምትባለው ገዳም ያሉ አባቶች በየዕለቱ በመላ አገሪቱ ውስጥ የተሰዋውን መስዋዕት የተጸለየውን ጸሎት እንደሚያሳርጉ ሲነግረን፤ እንዲህ ዓይነት ድርጊት የሚፈጸምባት ቅድስት ሃገር በተቃራኒው ርኩስ አስጸያፊ በሆነው በግብረ-ሰዶማዊነትም ስም አብራ መጠራት እንደሌለባት ሲይስታውሰን ሌላው ደግሞ (ስሙን እንኳን ያልነገረን ተቺ) የግል መብት ከሁሉም የበላይ እንደሆነና በግል ውሳኔ/ምርጫ ካቶሊክነት ወይም ኦርቶዶክሳዊነት ወይም እስልምና ወይም ሃይማኖተ-አልባ መሆን እንደምንችል ሁሉ፣ እንደግብረ-ሰዶማዊነትንም ያሉትን ተግባራት በግል መርጠን ማካሄድ መቻል መብታችን ነው ባይ ነው፡፡ ይኼኛው አስተያየት ሰጭ ታዲያ  ይፋ ከተደረጉት አስተያየቶች መኻል በጸረ ግብረ-ሰዶማውያን የተሰነዘሩት አስተያየቶች፣ ከሃይማኖት ወይም ከባህል ወይም ዝም ብሎ የመጥላት መንፈስ ውጭ ሌላ ምንም ዓይነት አስተያየት እንዳላየ ይተነትንና ሃይማኖታዊ የሆኑት ቅራኔዎች ለአማኞች ብቻ የሚሠሩ፤ ባህልን የተመረኮዙት ቅራኔዎች ደግሞ እንደማንኛውም ባህል ከጊዜ ሂደት ጋር እየተለወጡ መምጣት የማይቀርላቸው ናቸው ይለናል።

ታዲያ ይኼንን ሁሉ አንብቤ፤ እንደአብዛኛው ወገኔ እኔም በሀገሬ ላይ ያለኝ ተስፋ እየመነመነ፤ ውስጤ እየተቃጠለ፤ እንደኦርቶዶክሳዊ ክርስትና ተከታይም፣ ወደፈጣሪ አምላኬም ‘እስከመቼ ፊትህን ታዞርብናለህ!’ ብዬ መጮኼም አልቀረም። የመንግሥት መገናኛ ብዙኃንስ በተለየ ስለዚህ የግብረ-ሰዶማውያን እንቅስቃሴም ኾነ ከፍተኛ የኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ ባለ-ሥልጣን የሃይማኖት አባቶች ላይ አደረጉ ስለተባለው ኢ-ዴሞክራሲያዊ የአፈና ተጽዕኖ ምን ብለው ይኾን ብዬ ብፈልግ፣ በሽምግልና በደከሙ ዓይኖቼ ስንፈት አልታይ ብለውኝ ካልኾነ በሰትቀር አንድም ነጥብ ላገኝ አልቻልኩም።

እኔን ታዲያ ወደዚህ ጽሑፍ የገፋፋኝ ይኼ ሁለተኛው አስተያየት ነው። በሃይማኖታዊ መሠረት የሚደነገግም ሆነ በዓለማዊ አስተዳደር በየጊዜው የሚተገበር ሕግ ሥር መሠረቱ የሚመነጨው ከተፈጥሮ ሕግጋትም መኾኑን መዘንጋት የለብንም። ለምሣሌ ያህል ይኼንን ጉዳይ የሚመለከተው የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ ክፍል ሁለት ሲሆን ርዕሱ ‹‹ለተፈጥሮ ባሕርይ ተቃራኒ የሆነ የግብረ ሥጋ ግንኙነቶች›› ነው የሚለው። እንግዲህ በሰገላዊም ኾነ፤ ሃይማኖታዊ አገላለጽ ግብረ-ሰዶማዊነት “የተፈጥሮ ባሕርይ” ነው ብሎ  መሟገት ማለት በፍጡራን ውስጠ አካል፣ እንደ መተንፈስ፣ መመገብ እና የአካልን ብክነቶች የማስወገድ የመሳሰሉ ጠባያት ከንቁ-አዕምሮ ቁጥጥር ውጭ ለመራባት እና ራስን ከማጥፋት ለማዳን አብረውን የተፈጠሩ ግዴታዎች መሆናቸውን መካድ ነው። ሰው የተባለው ፍጡር ከተፈጥሮ ባሕርያቱ አንዱ ከተቃራኒ ፆታ ሰው ጋር ዘሩን የማርባት ግዴታውን ሟሟላት ከንቁ-አዕምሮ ውጭ የሚካሄድ ባሕርይ ነው። ይኼንን ደግሞ በግብረ-ሰዶማዊነት ማሟላት አይቻልም። አይ ግድ የለም! የግል መብት ስለሆነ ይፈቀድ ማለት ደግሞ ከተፈጥሮ ሕግ ጋር በመቃረን የሰው ልጅ ዘር ይጥፋ፤ እንዲጠፋም እናድርግ ማለት ነው።

በልጅነት ዘመኔ ባልንጀሮቼን የማታክትበት፤ እኔም ብሆን አሁን ከበሰልሁ በኋላ መለስ ብዬ ስገመግመው እኔውኑ የሚያሳፍረኝ አንድ ጠባይ ይዤ ነበረ። ደግነቱ እንደማንኛውም የልጅነት ጠባይ የጧት ጤዛ ሆኖ ነው የቀረው።  ለትንፋሻችን የምንጠቀመው ‘ኦክሲጂን’ የተባለው አየር በዓይናችን የማናየው፤ በእጃችን የማንዳስሰው ነገር ሆኖ፤ ዙሪያችንን ከቦ የሚገኝ እና ለመኖር የሚያስፈልጋቸው ፍጡራን ሁሉ የጋራ ንብረት ነው። በጎኑ ደግሞ ይኼን የጋራ ንብረት እኩል የመጠቀም መብት የያንዳንዱ ፍጡር ተፈጥሮአዊ መብት ሲሆን የባልንጀሮቼን ዓይን እስካልጠነቆልሁ ድረስ ዓይናቸው ስር ድረስ ጣቶቼን እያወናጨፍሁ በዓየር ላይ የመጠቀም መብቴን ካላሳመንኋችሁ እያልኩ አታክታቸው ነበረ። እውነትም የሰውን አካል እስካልነካን ድረስ (እንቅስቃሴያቸውን እየገታን እንኳ ቢሆንም) መብቴ በምንለው ነገር ሁሉ ላይ  እንዳሻን የመጠቀም መብት አለን ማለት በዚያ ባልበሰለ፣ ጨቅላ አዕምሮ አስተሳሰብ (በተለይም የጡንቻ ድጋፍ አለው ብለን ካመንን!) ማሳመን ይቻል ይሆናል። ነገር ግን የኔ አስተሳሰብ ጉድለቱ፤ መብት ማለት የሌላውን፤ ሃይማኖታዊም ይኹን ባህላዊ ወይም ተፈጥሮአዊ መብት እስካልነካ ድረስ ብቻ መሆኑን አለመገንዘብ ነበረ። እያንዳንዱ ፍጡር በሰውነቱ ዙሪያ እስከተወሰነ ርቀት ድረስ በዓይን የማይታይ፤ በእጅ የማይዳሰስ “የተፈጥሮ መንፈሱ (life-force) ወይም በባህላዊ ገለጻ፣ ውቃቢው የሚያስፈልገው ቦታ ሲወረርበት አይወድምም መብቱም እንደተነካበት ይቆጠራል።

እንግዲህ ለዚህ መጣጥፍ ያነሳሳኝ ሰው “የግል መብት ከሁሉም የበላይ ስለሆነ፣ እንደግብረ-ሰዶማዊነትንም ያሉትን ተግባራት በግል መርጠን ማካሄድ መቻል መብታችን ነው” ሲል ልክ እኔ በዚያ በርጥብ አስተሳሰቤ “ዓይንህን እስካልነካሁ ድረስ በዓየሩ ላይ ጣቶቼን ማወናጨፍ መብቴ ነው” እል እንደነበረው አይነት እጅግ የተዛባ እና ያልበሰለ አመለካከት ነው። በአሁኑ ጊዜ በየትኛውም ሕብረተ-ሰብ መገበያያ ተብሎ ጥቅም ላይ የሚገኘው በታተመ ወረቀት ወይም ከብረታ ብረት በተሠሩ ሣንቲሞች ነው። እኔም ሆንኩ ይኼ ወንድሜ ‘አይ እኔ መገበያየት የምፈልገው በአሞሌ ጨው ወይም አዝራር ነው” ማለት የግል መምረጥ መብታችን ቢሆንም ከሰው ፍጥረት ጋር እስካለን ድረስ የማይሠራ ባዶ-ቅል ኃሣብ ሆኖ እናገኘዋለን። ከኢትዮጵያ ሕብረተ-ሰብ ጋር ተቃራኒ የሆነ ተግባርንም በዚያ ሕብረተ-ሰብ መኻል የማካሄድ መብቴ ነው ማለትም እንደዚሁ ውዳሴ ከንቱ የኾነ አመለካከት ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከተፈጥሮ ግዴታዎች ተነስቶ በሃይማኖትም፤ በባህልም ሆነ በዘመናዊ አስተዳደር ሕግጋትን መሥርቶ በውዱ ሲተዳደርባቸው  እዚህ የደረሰ ሥልጡን ሕብረተ-ሰብ ነው። በሕብረተ-ሰብም ደረጃ ማሻሻልም ሆነ መለወጥ የሚያስፈልጋቸው ባህሎችም ሆኑ ልምዶች ቢኖሩትም ማንነቱን በማያዛባ እና ሁሉንም ወገን እኩል በሚጠቅም (ለዚያውም ተፈጥሮአዊ ግዴታን በማይቃረን መልኩ) እራሱ በራሱ ይለውጣቸዋል ወይም ያሻሽላቸዋል እንጂ ባዕድ ምዕራባውያን ባስቀመጡት መስፈርት ሊሆን አይችልም።

ይኼ እንግዲህ ‘የግል መብት’ በሚል አጠራር የምንመጻደቅባቸውን አዲስ ፈሊጦችን ሁሉ ያካትታል። አብሮም ልንረዳው የሚያስፈልገው ሌላው አዎንታ ደግሞ፤ በዴሞክራሲ ሥርዓት እንኳ ሕዝቡን የመምራትን ሥልጣን ጨብጠናል የሚሉት መሪዎችም ቢሆኑ የኢትዮጵያ ሕብረተ-ሰብ ተፈጥሮአዊንም ኾነ፤ እምነትን ወይም ባህልን ተመርኩዘው የተመሠረቱትን ሕግጋቱን በስሙ የማስከበር ሥልጣን እንጂ የመደምሰስ ወይም ሲደመሰስ ዝም ብሎ የማየት፤ የመለወጥ፤ የመጣስ ወይም የማስጣስ መብት የላቸውም። በዴሞክራሲ ሥርዓትም ሥልጣንን የጨበጡት ለኢትዮጵያውያን አገልግሎት እንጂ ለምዕራባውያን እያጎነበሱ ክብሩን ለማስገፈፍ እንዳልሆነ በፍጥነት ሊገነዘቡት ይገባቸዋል። አንዳንድ ነገሮች እጅግ አሰቃቂ፤ ነውር እና አይነኬ ናቸውና።

ኅዳር 25 ቀን 2004 ዓ/ም

Friday 13 May 2011

«ተጨናቂው የኢትዮጵያ አንበሳ»



በታኅሣሥ ወር ፲፱፻፶፫ ዓመተ ምሕረት የተከሰተው የነመንግሥቱ ነዋይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የኢትዮጵያን ንጉዛት አናውጦት ካለፈ ዓመት ከሦስት ወር ሆኖታል። ጄኔራል መንግሥቱም በዚያው ምክንያት በስቅላት ከተገደሉ እነሆ ዓመት አለፋቸው። እቴጌ መነንም ከተለዩን ገና ሦስት ወራቸው ብቻ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ብዙ የአፍሪቃ አገሮች ከአውሮፓውያን የቅኝ ግዛት ቀንበር ተላቀው የነፃነት እግራቸውን በዳዴ ለማጠናከር እየተፍጨረጨሩ ነው።

ታዲያ በዚያ ወቅት የአሜሪካው ‘ታይም’ መጽሔት ግንቦት ፳፬ ቀን ፲፱፻፶፬ ዓመተ ምሕረት፤ «ተጨናቂው የኢትዮጵያ አንበሳ» በሚል ርዕስ ያወጣው ዓምድ ስሜቴን በተለያየ መልክ የፈተነ ጽሑፍ ነው። መቸም መራራ ሐቅን እቅጭ አድርገው ሲነግሩት የሚያሽረው ጥቂት ነውና። 

በመግቢያው አንቀጽ ላይ የአዲስ አበባ ሴት ዝሙት አዳሪዎች ማስተወቂያቸው “ቀይ መስቀል” ነበረ። ነገር ግን የዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ማኅበር መዝናናት የሚፈልጉ ብዙ ወንዶች እየተሳሳቱ በየክሊኒኮቼ ዘው እያሉ አስቸገሩኝ በማለቱ፤ እነኚህ ሴቶች ምልክታቸውን ወደ ቀይ መብራት እንዲለውጡ የመንግሥት ድንጋጌ መውጣቱን ያበሥራል። ታዲያ ይሄ ድንጋጌ ሥራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የነኚህ የወንድ መዝናኛ ቤቶች ከአምስት ሺ ወደ ስምንት ሺ ማደጉንና የአካባቢው የመብራት ኃይል ፍጆታም ማሸቀቡን ይዘግባል።

ዛሬ ቢሆን “የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት በእጥፍ አኃዝ ማደጉን የ’ታይም’ ጋዜጠኛ መሰከረ።” ነበር ርዕሰ አንቀጹ የሚለው።

 ‘ታይም’ እድገቱ የወቅቱን ለውጥ እንደሚያረጋግጥ ሲጠቁም፤ ምክንያቱንም ኢትዮጵያን የአፍሪቃ ነጻነት ትግል እምብርት ለማድረግ ንጉሠ ነገሥቱ የሚያደርጉት ጥረት በርዕሰ ከተማዋ በሚካሄዱት ሥፍር-የለሽ ስብሰባዎች ላይ ለመሳተፍ የሚጎርፉት እንግዶች ናቸው ይላል።  [ሌላው ቢቀር፣ ሽርሙጥና ከፍ ያለ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ሆነልን ማለቱ ይሆን? የትም ፍጪው፣ ዱቄቱን አምጪው! ይባል የለ?]

ወደታሪክ መለስ ብሎም «እነኚህ ዘራቸውን ከንጉሥ ሰሎሞንና ከንግሥት ሣባ በመምጣቱ የሚኮሩ
ኢትዮጵያውያን - ለብዙ ምዕት ዓመታት ጥቁር አፍሪቃውያንን “ባሪያ” እያሉ በማንቋሸሽ ኖረዋል።» ነገር ግን የጥቁር አፍሪቃ አገራት ነፃ እየወጡ ድምጻቸውን በዓለም መድረክ ላይ ማሰማት ከጀመሩ በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ፣ ድሮ “ባርያ” እየተባሉ የሚናቁትን አሁን ግን «ተወዳጅ ጥቁር ወንድሞቻችን» በሚል ለአኅጉሩ መሪዎችና ታጋዮች የቅኝ-ግዛትን ሥርዓት በማውገዝ በደብዳቤ መልዕክቶቻቸውን ማብረር ጀመሩ። ካለ በኋላ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሰሞኑን በ ሦስት ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ($3,000,000) በተገነባው አዲሱ የ’አፍሪቃ አዳራሽ’ ውስጥ ተንቀሳቃሹን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅኝ  ግዛት ሸንጎ አባላትን እንደሚያስተናግዱ ይነግረናል። ከካቢኔ ሚኒስትሮቻቸው አንዱ “ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እንደዚህ አይነት መስተንግዶ ለአፍሪቃ አኅጉር መሪነት ያላቸውን ምኞት እንደሚያሳካላቸው ያምናሉ” ይላል ።

ይኸው ኢትዮጵያዊ የካቢኔ ሚኒስቴር «እኛ ከሁሉም የቆየ ነፃነት አለን። በቅርብ ነፃነታቸውን የተቀዳጁትን ወንድሞቻችንን ደግሞ ወደዘመናዊው ዓለም የመምራት ግዴታችንም ቅርሳችንም ነው» ብሏል በሚል ጽሑፉን ያዘጋጀው የመጽሔቱ ቃል አቀባይ ጠቅሶታል። ታዲያ የጽሑፉ ደራሲ ጋዜጠኛ «ይቺ ከዓለም ኋላ ቀር አገሮች መኻል የምትሰለፍ አገር፤ ፓርላማዋ ሥራውም ሆነ ችሎታው የንጉሠ ነገሥቱን ፍጹም ሥልጣን በማኅተም መርገጫ የማጽደቅ ብቻ የሆነባት እና የመገናኛ ብዙሐን ነፃነት የማይከበርባት፤ ሰላዮችና ጆሮ ጠቢዎች በሰፊው የተሠማሩባት ኢትዮጵያ እንኳን ሌላ አገሮችን ወደዘመናዊው ዓለም ለመምራት ቀርቶ፣ እራሷም መንገዱ በየት እንደሆነ አይታውም አታውቅ።» በሚል ከእሳት ማዕበል የበለጠ በሚፋጁ ቃላቶቹ ሸንቁጦናል። የምታቦካው የላት የምትጋግረው አማራት አሉ አባቶቻችን!
ይሄ ብቻ መቼ በቃውና! ያ ብስለት የጎደለው፣ ጉረኛ [እንዲያውም ትዕቢት የተሞላበት ቃላቶች በመሰንዘሩም ‘አሳዳጊ የበደለው ባለጌ’] የካቢኔ ሚኒስቴር በሰነዘራቸው ቃላት መነሻነት ለጋዜጠኛው የስድብ ነጎድጓድ ዳርጎናል። ሞኝና ወረቀት የያዙትን አይለቁም እንደሚባለው ከልጅነቱ ጀምሮ ሲሰማው የቆየውን የስህተት አመለካከት ማረም እንኳ ያልቻለ ትሩማንትሪ!
መቸም በዚህ ጽሑፍ ላይ የሠፈሩትን ነጥቦች እውነተኛነት ላለመቀበል ሳይሆን፤ በባእድ ብዕር መሰደባችን እየከነከነኝ ነው። «ወንጀለኛ በአደባባይ የሚሰቀልበት አገር፣ ከነአካቴው የወህኒ ቤቶችን መጣበብ ለማቃለል እና ለ’እኔን አይተህ ተቀጣ’ም እንዲያመች በእሥራት ፋንታ በአደባባይ መገረፍ በቅርቡ ተፈቅዷል » ይልና፤ ስለሙስናም ሳይተርብ አያልፍም። በዘገባው እንዳሰፈረው ባለ ሥልጣናቱ በሙስና ከመጨማለቃቸው ብዛት ከሚሰበሰበው ቀረጥ ሲሦው ወደመንግሥት ካዝና አይገባም ብሏል።

የመንግሥቱ የአስተዳደር ብዛትና ክብደት ከአገሪቱ ዓመታዊ ወጭ ሁለት ሲሦውን ይበላዋል፤  በሀያ ሚሊዮን የሚገመተው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአገሪቱ ሀብት የሚደርሰው በዓመት በአማካይ አምሥት የአሜሪካ ዶላር እንደሆነ፤ ከመቶ ሕዝብ ዘጠናው መሐይም፤ ሰማንያ በመቶው ደግሞ በጥገኛ ነፍሳት የተጠቃ፤ ገሚሱ የወሲብ በሽታ የተጸናወተው እና አርባ ከምቶ የሚሆኑ ሕጻናት እንደሚሞቱ፤ ወባ በየዓመቱ ሰላሳ ሺ ሰዎችን እንደሚገልና ከመቶ ከብቶች አርባዎቹ በሳምባ ነቀርሳ የተለከፉ እንደሆኑ ይተነትናል።

ኧረ በፈጠረህ ይበቃል! አልኩኝ ፣ አጠገቤ ያለ መስሎኝ!
እሱም «አንዴ ጀምሬዋለሁና በትእግሥት አስጨርሰኝ» የሚለኝ መሰለኝ። ለጥቆም «የነጮች ልምዳዊ ማሳጣት ነው፤ ይሄን ሁሉ የሚያስተነትንህ እያልከኝ አይደል? እሺ የኔንስ እንደዚያ ገምተው። ስብሰባ ላይ ሊሳተፍ የመጣውስ ጥቁር፤ አፍሪቃዊ፤ ሴኔጋላዊስ? ምን እንዳለኝ ታውቃለህ?» ይለኛል። አያችሁ በታሪክ አውሎ ነፋስ እይተውዠገዠገ መጥቶ ልቦናዬን እንዴት እንደሚያስተኝ? ወቸ ጉድ!

ይሄ ሴኔጋላዊ የአዲስ አበባን አራት መቶ ሃምሣ ሺ ነዋሪዎች ድህነት፤ መራቆት እና  የኋላ ቀር ኑሮ ከተገነዘበ በኋላ “የነፃነት ውጤት ይሄ ከሆነ፤ መልሳችሁ ግዙኝ።” ብሎኛል አለ ጸሐፊው። ያ ምስኪን ሴኔጋላዊ ነፃነትን በቀመሰ በሁለት ዓመቱ እንኳንስ እኛን እንደመሪ ሊቆጥር ጭርሹንም የእኛ ኑሮ አቅለሽልሾት ነፃነቴ ይቅርብኝ እስከማለት መድረሱ ለጋዜጠኛው አመለካከት ድጋፍ እንደሰጠውና የዚያም የካቢኔ ሚኒስትር አጉል ድንፋታ ፍሬ-ቢስ እና ውዳሴ ከንቱ መሆኑን በማያሻማ መልክ አረጋግጦታል። ጉድ እኮ ነው!

ተንኮለኛው ዘጋቢማ ምን ዕዳ አለበት? «ይሄ ሁሉ [ኋላ ቀርነት] ለጞብኚ አፍሪቃውያን ምን ዓይነት አሉታዊ ስሜት እንደሚፈጥር የተገነዘቡት ንጉሠ ነገሥት»፣ ይላል አሜሪካዊው፤ «የኢንዱስትሪያዊ ልማት ከመጀመራቸውም ባሻገር ግድቦችን፤ ነዳጅ ማጣሪያ፤ ወደቦችን እና ፋብሪካዎችን ለማሠራት ከምዕራባውያንም ከምሥራቃውያንም ዕርዳታ እየተቀበሉ ነው።» ዳሩ ግን የራሳቸውን ሥልጣን ይቀንሱብኛል ብለው የሚያምኗቸውን የአስተዳደር እና የፓርላማ ማሻሻያ እርምጃዎችን ለመውሰድ አሻፈረኝ እንዳሉም አብሮ አስፍሯል። ከአሥራ ሰባት ወራት በፊት በንጉዛቱ ሥርዓት ላይ ተነስተው የነበሩት ምሑራን እና ተራማጅ ወገኖች፤ ምንም እንኳ የኃይለ ሥላሴ መንግሥት በሹመት፣ በሽልማት ሊደልላቸው ቢሞክርም እንቅስቃሴያቸው አልበረደም። ሆኖም እራሳቸውን በቅጡ ያላደራጁ እና ቀጣዩ የተቃውሞ እርምጃ ምን መሆን እንዳለበት ስላልተስማሙ ጩኸትና ጫጫታቸው አልተተገበረም።

የትንተናውን ድምዳሜ በንጉሠ ነገሥቱ ላይ በማተኮር፤ «የ፷፱ ዓመቱ ሽማግሌ በባለቤታቸው እና አራት ልጆቻቸው ሞት ብቸኛ ቢሆኑም እንኳ ከሃያ ስድስት ዓመታት በፊት በዓለም መንግሥታት ማኅበር መድረክ ላይ በመቆም ያሳዩት የጉልምስና ስሜት አሁንም አልራቃቸውም።» የ፵፭ ዓመት ዕድሜያቸውን የያዙት ልጃቸው አልጋ ወራሽ አስፋ ወሰን ግን ከአባትዬው ይልቅ የተራማጅነት አስተሳሰብ ያላቸው ቢሆኑም ባህሪያቸው ለስላሳ እና ጨፍጋጋ ነው ይልና፣ «የንጉሠ ነገሥቱ ዘውድ ሳይተላለፍ ብዙ የዘገየ እንደሆነ፤ በአሮጌው ሥርዓት ላይ ያለመው መሣሪያ ምላጭ መሳቡ የማይቀር ነው።» ሲል ዘገባውን ደምድሟል። ምከረው ምከረው እንቢ ካለ መከራ ይምከረው እንዲሉ፤ ጃንሆይም አልሰማ ብለው….

በሚቀጥለው የታሪክ አውሎ ነፋስ እስከምንገናኝ፤ የሎንዶኑ ቡልጌ ነኝ!


Wednesday 4 May 2011

የ፸ ዓመት ነፃነት

        ሚያዝያ ፳፯ ቀን አባቶቻችንና እናቶቻችን አርበኞች ግፈኛውን የፋሺስት ኢጣልያ ሠራዊት ድል ያደረጉበት ማስታወሻ አድርገን እናከብረዋለን። በ፳፻፫ ዓመተ ምሕረት፣ ነገ ደግሞ ርዕሰ ከተማችንን በከፊል ተረክበን፣ ሰንደቅ ዓላማችን የተውለበለበበት ሰባኛው ዓመት ማስታወሻ ስለሆነ ለየት ባለ ሁኔታ ለማክበር እንሞክራለን። ከነኛ ጀግኖች አርበኞቻችን መኸል መቸም በጊዜው ብዛት አብዛኛዎቹ ተለይተውን፣ የቀሩት ጥቂት ናቸው።

በዚህ የመታሰቢያ ጽሑፍ  ከዚህ ዕለት ጋር የተያያዙ ሦስት ዐቢይ ነጥቦችን ለማንሳት እፈልጋለሁ። እነዚህም፦

ሀ)      የዚህን ዕለት ‘የነፃነት ቀን’ ወይም ‘የድል በዓል’ መባል ትክክለነቱን፤
ለ)      ለድሉ ወይም ለነፃነቱ ላደረሱን ጥቂት፣ ተራፊ አባቶች እና እናቶች አርበኞቻችን ምን ውለታ ተደርጎላቸዋል?
ሐ)      እኛ ኢትዮጵያውያን ለ ፸ ዓመታት በጃችን ይዘነው የቆየነውን ‘ነፃነት’ እንደምን ተጠቅመንበታል?

ሀ)     የድል በዓል ሚያዝያ ፳፯ ወይስ ኅዳር ፲፱ ?

ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በምዕራብ ኢትዮጵያ ኡም ኢድላ (ኦሜድላ) ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከተከሉበት ጥር ፲፪ ቀን ፲፱፻፴፫ ዓ/ም ጀምሮ በጎጃም እንጃባራ፤ ቡርዬ፣ ደምበጫ፣ ደብረ ማርቆስ አድርገው በእንጦጦ በር አዲስ አበባ እስከገቡ ድረስ፤ በአርበኞቻችን ኃይልና በእንግሊዝ ጦር ኃይሎች እርዳታ የጣሊያንን ኃይል እየደመሰሱ በሚጓዙበት ወቅት በምሥራቅና በደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ የነበሩት አርበኞችና የእንግሊዝ ሠራዊት እንደዚሁ በጅጅጋ፣ ሐረር፣ ድሬዳዋ፣ አዋሽ፣ ናዝሬትና ሞጆ አድርገው፣ ከፊታቸው የሚያጋጥማቸውን የፋሺስት ኃይል እየደመሰሱ ወደርዕሰ ከተማዋ ይገሰግሱ ነበር።

ታዲያ ከነኚህ ሁለት ግንባሮች ቀድሞ ከተማዋን መጋቢት ፳፰ ቀን ፲፱፻፴፫ ዓ.ም ከጣሊያኖች የተረከበው እንግሊዛዊው ጄነራል ዌዘሮል ነበር።[1]  ንጉሠ ነገሥቱ እና ተከታዮቻቸው ከአንድ ወር በኋላ፣ ሚያዝያ ፳፯ ቀን አዲስ አበባን ተረከቡ።

በዚህ ጊዜ በደቡብ-ምዕራብ ኢትዮጵያ፤ ጅማ እስከ ግንቦት ፳፱ ድረስ በሰሜን ኢትዮጵያ ደግሞ ጎንደር እስከ ኅዳር ፲፱ ቀን ፲፱፻፴፬ ዓመተ ምሕረት ድረስ በጣሊያኖች እጅ ነበሩ።

እንግዲህ እንደምንገነዘበው 'ድል ቀን' ሚያዝያ  ፳፯ ቀን የሆነበት ዋናው እና ብቸኛው ምክንያት ንጉሠ ነገሥቱ አዲስ አበባ የገቡበት ዕለት ስለሆነ እንጂ መላዋ አገር ከፋሺስት ቀንበር የተላቀቀችበት ሆኖ አይደለም። ትክክለኛ ሆኖ መከበር ያለበት የጣሊያን ሠራዊት ለመጨረሻ እና ለዘለዓለም ሰንደቅ ዓላማውን ከኢትዮጵያ ምድር ያወረደበት እና ያለምንም ጥርጣሬ መሸነፉን አምኖ ጎንደር ላይ እጁን የሰጠበት ዕለት ኅዳር ፲፱ ቀን  ፲፱፻፴፬ ዓመተ ምሕረት መሆን ይገባዋል። 

ያለበለዚያማ በዚህ በመጨረሻው ግንባር ተሰማርተው ሲጋደሉ የቆዩትን አባቶቻችንን መስዋእትነት መዘንጋት፣ መደምሰስ ይሆንብናል። የእነ  ደጃዝማች ኪዳኔ ወልደመድኅን ደጃዝማች ሀብተ ሥላሴ በላይነህ ደጃዝማች በዛብህ በለው፣ ደጃዝማች ካሣ መሸሻ፣  ደጃዝማች ከበደ ወንድማገኝ፣ ፊታውራሪ ከበደ ካሣ፣ እና የሌሎችም ብዙ አባቶቻችን አፅም ይፋረደናል። ሌሎቹ አርበኞች፣ ስደተኞች ከአምሥት ዓመታት በኋላ ወደየዘመድ አዝማዳቸው፣ ወደየትውልድ አገራቸው ሲመለሱ፣ እነኚህ ግን ትጥቃቸውን ሳያወልቁ፣ ቅማል የወረረውን ጎፈሬያቸውን ሳይቆረጡ ወደሰሜን ዘመቻ ተሰማሩ። የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ከሚያዝያ ፴፫ እስከ ኅዳር ፴፬ ያሉትን ሰባት ወራት የደመሰሰባቸው ይበቃል።

'ድል በዓል' ዕለት መከበር ያለበት ሰንደቅ ዓላማ የተተከለበት ዕለት ከሆነ፣ እንግዲያውስ ኡም ኢድላ (ኦሜድላ) ላይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የትተከለበት ጥር ፲፪  ቀን ይከበራ! አይ፣ አዲስ አበባ ከፋሺስት ኢጣልያ እጅ የተፈለቀቀችበት ዕለት መሆን አለበት የተባለ እንደሆነ ደግሞ፣ እንግሊዛዊው ማጆር ጄኔራል ዌዘሮል ዋና ከተማዋን የተረከበበት መጋቢት ፳፰  ቀን ይሁና! የዚህኛው ቀን ችግር ግን ዌዘሮል ያውለበለበው የብሪታኒያን ሰንደቅ ዓላማ መሆኑ ነው።

እነዚህ ሁሉ የተለያዩ ቀናት እንድ ሚያዝያ ፳፯  'ድል' የሚለውን ቃል ሙሉ በሙሉ አርኪ በሆነ መልድ አያስተጋቡም። ኅዳር ፲፱ ቀን ግን የፋሺስትን ኃይል ከመላዋ ኢትዮጵያ ክልል አሽቀንጥረን አስውጥተን፣ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቅ ዓላማችን በመላው አገራችን የተውለበለበበት፣ ራሳችንን በራሳችን የማስተዳደር መብታችን የተከብርበት ዕለት [የሰባት ዓመቱን የእንግሊዞችን ጣልቃ ገብነት ወደጎን ትተነው] በመሆኑ እውነተኛው "የድል ዕለት" ያደርገዋል።
ለ)     አርበኞች አባቶቻችን እና እናቶቻችን ስለስድስት ዓመት ተጋድሏቸው ምን ውለታ አገኙ?
        
ጠላት ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ አብዛኛዎቹ ተከላካይ ወገኖቻችን ዕድሜያቸው ከአሥራ ስምንት ዓመት እስከ ሃያ አንድ ዓመት ብቻ የነበሩ ወጣቶች ናቸው። አብዛኞቹ፣ የጦር መሪዎቻቸው፣ መኳንንቱ፣ መሣፍንቱ  ከነአካቴውም ንጉሠ ነገሥቱም ሳይቀሩ አጋፍጠዋቸው አገር ጥለው እግሬ አውጪኝ ሲበሩ፤ ሞትም እንኳ ቢመጣ ለጠላት አንገዛም ብለውት፤። ረሀብ ሲቆላቸው፣ ቅማል ደማቸውን ሲመጠምጥ፣ የመርዙ ጋዝ፣ የቦምባርዱ፣ የጥይቱ የተቅማጡ፣ እረ ምኑ-ቅጡ 

መንፈሰ ጠንካራ፣ አልበገር ባይ ባይሆኑማ ኖሮ እነሙሴ ቀስተኛን የመሰሉ ሰላዮች መኻላቸው እየገቡ፤ ‘ንጉሡ ጥሏት ለሄደው አገር ስለምን ትጉላላላችሁ? ኑ ግቡ፤ የኢጣልያ መንግሥት ይሾማችኋል፣ ይሸልማችኋል’ እያሉ አገራቸውን ሊያስከዷችእው ሞክረው አልነበረም?  ያ ትውልድ ግን ‘ለጥቅሜ ብዬ ውድ አገሬን፣ አለኝታዬን፣ መኩሪያዬን አሳልፌ አልሰጥም። ለነፃነቴ ብሞትም ክብሬ የዘለዓለም ነው።’ በሚል ጥብቅ እምነታቸው ተሰቃዩ፣ አጥንታቸውን በየሸንተረሩ ከሰከሱ፣ ደማቸው በየ ሸለቆው ፈሰሰ፤ እንደጥብቅነታቸው እንደ እምነታቸው ታዲያ ያንን መራራ ጠላት ከወሰን ድንበራቸው ለማባረር በቁ።

የዓፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት በነኚህ ኢትዮጵያውያን ደም ተመልሶ ሥልጣኑን ሲጨብጥ፣ እንደባለውለታ መንከባከብ፣ መሾም መሸለም፣ ማክበር ማስከበር ሲኖርበት፤ ከነአካቴው ውለታ ተቀባይነታቸው ቀርቶ እንደውለት መላሽ የትም ወድቀው እንዲቀሩ፣ ስማቸው እንዲጠፋ፣ ሥራ ስጡን ብለው በ’ደጅ ጥናት’ እንዲማቅቁ የሚጥር ሥርዓት ሆነባቸው። በስማቸው የተሠራውን የአራት ኪሎውን ሕንፃ እንኳን ለማስፈቀድ የነበረባቸውን እንግልት ይሄ ጸሐፊ በቅርብ ታዝቦታል። የኢትዮጵያ መንግሥት እነኚህን ባለውለታዎች፣ ሲሆን እስከ ጡረታ ዕድሜያቸው አገራቸውን እንዲያገለግሉ፤ ቢያንስ እንኳ ለዚያ ውለታቸው ክብራቸውን ጠብቆ በእንክብካቤ መጦር ሲገባው ነፍስ አውጪኝ የሸሹትን ስደተኞች ሲሾም ሲሸልም፣ እነኚህን ግን ከኢትዮጵያ ማዕድ ከልክሏቸው ኖረ።

በደርግ ዘመናት ደግሞ ጭርሱንም በትምህርት ቤት እንኳ ከአብዮቱ በፊት የነበረውን ታሪክ ወጣቱ እንዳይማረው ተከለከለ። ትንሽ መተዳደሪያ መሬት የነበራቸው ተነጠቁ። ወገን ለሌላቸው አርበኞች መርጃ ተብሎ የተሠራው የአራት ኪሎ ሕንፃቸው ሳይቀር ተወረሰ። መጦር የነበረባቸው የነፃነታችን ባለቤቶች እየለመኑ መኖር ግዴታ ሆነባቸው።[2]

ባለፉት ሃያ ዓመታትማ ብሶበታል። አንደኛ ቁጥራቸውም እያደር እየመነመነ ነው። ከሁሉም በላይ ግን የአሁኑም መንግሥት የነኚህን ባልውለታዎች ታሪክ ማንቋሸሽና ማጣጠል እንጂ ክብር መስጠትን የማያውቅ፤ ዘመኑ እንኳን ለሰማንያ፣ ዘጠና ዓመት አዛውንት ቀርቶ እየሠራ የሚበላው ወጣት ትውልድ ሊቋቋመው የማይችለው፣ ሽማግሌ ማክበር፣ መርዳት የነበረው የባህላችን ምሰሶ በሥልጣኔ፣ እድገትና እርምጃ ስም ሌት ተቀን በመጥረቢያ ስለት እንደሚከተከት ግንድ ሊወድቅ ምንም ያልቀረው ሆኗል። ታዲያ ለእነኚህ ባለውለታችን አዛውንት ምን ተስፋ አላቸው?

ሐ) የ፸ ዓመት ነፃነታችንን ምን ሠርተንበታል?
ከ፴፫ቱ ድል ጋር አብረው የገቡት እንግሊዞች ምሥጢራዊ ዓላማቸው ፋሺስት ኢጣልያን በቅኝ ገዥነት መተካት ኖሮ በስም የንግሊዝ ቅኝ ግዛት አንባል እንጂ በተግባር ግን እንደመዥገር ተጣብቀውብን ደማችንን ሲመጡ የኖሩባቸውን ሰባት ዓመታት ትተን በቀሩት ፷፫ ዓመታት ላይ ብናተኵር፤ ይሄንን ጥያቄ እንዴት ነው የምንመልሰው?
የዘውዱ ሥርዓት ከስደት እንደተመለሰ ሥልጣኑን በማጠናከር፣ ፈላጭ፣ ቆራጭ ሆኖ ፣የአምሥቱን ዓመታት ፍዳ ረስቶ/አስረስቶ ለሃያ ዓመታት ከገዛ በኋላ፤ የወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ቢደርግበትም የጭቆና ባሕሪውን አባባሰው እንጂ ለሕዝቡ ንቃት እና መሻሻል ምንም ይሄ ነው የሚባል ለውጥ አላመጣለትም። የዚያ የታኅሣሡ ሙከራ ግን በሕዝቡ ልቦና ላይ የጫረው የለውጥ እሳት ከ ፲፫ ዓመታት በኋላ ተፋፍሞ አሽቀንጥሮ ጣለው።
ተከታዩ አብዮት፣ ሕዝቡ እንደተመኘው፣ እንዳለመው የዴሞክራሲያ ውጤትን ሳይሆን የተጎናጸፈው፤ ጭርሹንም ከመቶ ዓመት በላይ ወደኋላ የገፈተረው ሥርዓት ሆነ። የሕዝብን ሉዐላዊነት፣ የሕግን የበላይነት፣ እኩልነትን፣ በኢትዮጵያዊነት ታሪክ ላይ የተመሠረተ ሥልጣኔን የሚሻ ሕዝብ ከነአካቴው ከጨካኞች የባሰ ጨካኝ፤ ከዲያብሎስ የበለጠ አረመኔ የአምባ ገነን ተገዢ አደረገው። በዲሞክራሲያ ፋንታ ለስድብ፣ ለውርደት፣ ለሞት ተዳረገ። የኢትዮጵያዊነት ወኔውን ተሰለበ።
ደሞ ያንን አሰቃቂ እና ፍሬ ቢስ ዘመን ከ፲፯ ዓመታት በኋላ ተገላገልኩ ሲል፤ ለባሰ ሥርዓት ከተዳረገ እነሆ ሀያ ዓመቱ ሆነ። ተለያይቶ የማያቀውን አንድ ሕዝብ በዘር አከፋፍሎ፣ አገርን በጉልበት ለመንጠቅ ለብዙ መቶ ዓመታት ሞክረው ያቃታቸውን ባዕዳውያንን በይፋ እየቆረሰ ‘ኑ ውሰዱልኝ’የሚል፣ የበላዩ ሊሆን የሚገባውን ሰፊውን የኢትዮጵያ ሕዝብ መብቱን ገፎ የሚገዛ የጉድ ጉድ፣ መዓት አናታችን ላይ ተመቻችቶ ቁጭ እንዲል ፈቀድንለት።
ዳግማዊ ምኒልክ የዛሬ መቶ ዓመት፣ ዕለተ ሞታቸው ሲቃረብ፤ ሕዝባቸውን እንዲህ ብለው መክረው ነበር፦

«እናንተ አንድ ልብ ከሆናችሁ በምቀኝነት እርስ በርሳችሁ ተዋግታችሁ ካላለቃችሁ በቀር ኢትዮጵያን አገራችንን ለሌላ ለባዕድ አትሰጧትም፤ ክፉም ነገር አገራችንን አያገኛትም። ነፋስ እንዳይገባባችሁ አገራችሁን በያላችሁበት በርትታችሁ ጠብቁ፤ ወንድሜ ወንድሜ እየተባባላችሁ ተደጋገፉ፤ የኢትዮጵያን ጠላት ተጋግዛችሁ ተድንበር መልሱ። የኢትዮጵያ ጠላት ባንዱ ወገን ትቶ ባንድ ወገን ቢሄድና ድንበር ቢገፋ፤ በኔ ወገን ታልመጣ ምን ቸገረኝ ብላችሁ ዝም አትበሉ፤ ያ ጠላት በመጣበት በኩል ኁላችሁም ሄዳችሁ አንድነት ተጋግዛችሁ ጠላታችሁን መልሱ እስከ እየቤታችሁ እስኪመጣ ዝም ብላችሁ አትቆዩ»
 ይሄ ቃላቸው በታሪክ አውሎ ነፋስ ተምዠግዥጎ እኛም ዦሮ ሲገባ፣ መልእክቱ ለዘመናቸው ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለኛም፤ ለመጪውም ትውልድ እንደሆነ እንገነዘባለን። በዛሬው የመከፋፈል፣ የዘረኛነት እና መንፈሰ ደካማ ሥርዓት ግን ምኒልክ ከነአካቴው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት ተብለው ተወነጀሉ።
በበኩሌ ያንን ሁሉ መሥዋዕትነት፣ ያንን ሁሉ ተጋድሎ አባክነነዋል እላለሁ እንጂ የ፸ ዓመት ነፃነታችንን በአግባቡ ተጠቅመንበትም ለወደፊቱም ትውልድ ቋሚ ነገር ለማሸጋገር በቅተናል አልልም።

የሎንዶኑ ቡልጌ ነኝ
[ሚያዝያ ፳፮ ቀን ፳፻፫ ዓ/ም]





[1] The Abyssinian Campaigns, Issued for the War Office by the Ministry of Information (1942)