Showing posts with label Ethiopia. Show all posts
Showing posts with label Ethiopia. Show all posts

Thursday 27 June 2013

ሚካኤል (ወልቃይቴ) ብሩ እና ዳውቲ-ዋይሊ

ሚካኤል (ወልቃይቴ) ብሩ እና ዳውቲ-ዋይሊ
የብሪታኒያው ዋና መላክተኛና ባልደረባዎቹ አዲስ አበባ ላይ የተደበደቡ ዕለት።

ዚህ ትረካ ደራሲ ከዚህ በፊት “የየዋሖቹ ዘመን” ባልኩት ጽሑፌ መተዋወቃችንን ለማስትወስ ያህል፤ በዕምዬ ምኒልክ ዘመን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በቅሎው እሰው ማሳ ውስጥ ይገባና የአቅሙን ያህል የጤፍ እሸት አጋበሶ ከዋጠ በኋላ የተፈጥሮው ግዳጅ ቢሆንበት፣ በቀረው ሰብል ላይ እየተንከባለለ መዥገር ማላቀቂያ አድርጎ ያወድመዋል። ኦሮምኛ ተናጋሪው የማሳው ባለቤት  ታዲያ የካሣውን አሞሌ ጨው ቢጠይቅ የቋንቋ አለመግባባት ሆነና፤ ከማሳው ጠቅላላ ምርት ግምት በላይ ከአንድ ብር ሁለት ብር፤ ሦስት ብር፣ አራት ብር ቢከፈለው  ጊዜ በቅሎውን እንደልቡ እንዲሰድበት መነገሩን ያጫወተን ሻለቃ ሄንሪ ዳርሊ መሆኑን ከወዲሁ አንባቢ ይገንዘብልኝ!

Monday 24 June 2013

የኢትዮጵያ የአበባ ምርት በአፍጋኒስታን ገበያ አገኘ እንዴ ?

ይመኩ ታምራት (ከሎንዶን)

ሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2005 ዓ/ም

ሐቅ! የአየር መንገዳችን የጭነት ጥያራዎች በግንቦት እና በያዝነው ሰኔ ወራት ወደ አፍጋኒስታን ደፋ ቀና ሲሉ ታይተዋል። (Flight Radar24.com ድረ-ገጽን ይመልከቱ)

ሐቅ! አየር መንገዱ ስድስት የጭነት ጥያራዎችን አሰማርቶ በቋሚ መልክ ወደ አውሮፓ፤ መካከለኛው ምሥራቅ እና እስያ ሸቀጣ
ሸቀጥ ያመላልሳል። ኾኖም አፍጋኒስታን በቋሚነት ከሚበርባቸው አገሮች መኻል ያልተመዘገበች ከመሆኗም ባሻገር በጦርነት ከተዘፈቀች አገር ጋር ምን ዓይነት ንግድ ተጀመሮ ይሆን የሚያስብሉ ሰባት በረራዎች ቀልቤን ሊስቡት ችለዋል።

ሐቅ!  አፍጋኖቹ ያለፉትን ሦስት-አሥርት ያህል ዓመታት ያሳለፉት እርስ በርስ በመፋጀት፤ በመፈራረቅ አገራቸውን የያዙባቸውን የሁለቱን ኃያላን መንግሥታት ወራሪ ሠራዊቶች በመከላከል እና በመኻሉም አክራሪ-ሃይማኖተኝነትን መርኅ በማድረግ ነው። የአገራቸው መልክዓ-ምድር እንደ ኢትዮጵያ ተራራማ ከመኾኑም ባሻገር የገጠሩ ዜጋ አኗኗር የኛውኑ ገጠሬ ጋር ይመሳሰላል። በጎቻቸው እንኳ በላት ምትክ ቂጣሞች ይሁኑ እንጂ የኛውኑ የአዳል ሙክት ነው የሚመስሉት።  ግን ከኋላቸው ሲያስጠ................ሉ!!

Wednesday 19 June 2013

የቡድን ስምንት ወጥ ቀማሽ

«የቡድን ስምንት መሪዎች መለስ ዜናዊን የሚተካ ወጥ ቀማሽ እያፈላለጉ ነው» ተባለ።

ይመኩ ታምራት

ከአዲስ አበባ ዕሮብ ሰኔ ፭ ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ተነስተው ቻይና ከመግባታቸው በፊት ለጢያራቸውም  ለተከታዮቻቸውም እህል ውሀ ለማለት ሳይሆን አይቀርም፤ የባንግላዴሽ ዋና ከተማ ከሚገኘው ‘ሀዝራት ሻሃጃላል ጢያራ ጣቢያ’ አረፍ ብለው ነበር። በማግሥቱ የቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኬቂያንግ ጥያራ ጣቢያ ተገኝተው ተቀበሏቸው። ዓርብ ደግሞ ከአዲሱ የቻይና ፕሬዚደንት ጋር ውይይት አደረጉ። ቅዳሜን እዚያው ውለው አድረው እሑድ ከአገር ወደተነሱበት ቁም ነገር ለመመለስ ወደሎንዶን ‘ስታንስተድ’ ጥይራ ጣቢያ አመሩ። የሎንዶኑ አቀባበል ከቤይጂንጉ የላቀ ይሁን የደበዘዘ የምናውቀው መረጃ የለንም።

Sunday 14 April 2013

“ተፈራ ደገፌ በቫንኩቨር ፀጉር ማስተካከያ ቤት የዘረኝነት መድሎ ተፈጸመብኝ አለ”


ኼንን ዘገባ ይዞ የቀረበው ጋዜጣ “የዕለቱ ዩቢሲ” (The Daily Ubyssey) የሚባለው የ’ብሪቲሽ ኮለምቢያ ዩኒቨርሲቲ’ ልሣን ሲሆን ታሪኩን ያዘለው ዕትም ለንባብ የቀረበው ዓርብ መስከረም ፲፭ ቀን /ም ነበር።  ልክ ነዎት አልተሳሳቱም! አሥራ ዘጠኝ መቶ አርባ ዓመተ ምሕረት፤ የዛሬ ስድሳ ስድስት ዓመት ማለት ነው!

Sunday 3 February 2013

አስፋ ወሰን ኃይለ ሥላሴ - ክፍል ፪


«እሳት በሌለበት ጭስ የለም!» ወይስ «ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ!» ?


ክፍል ላይ በልዑል አልጋ ወራሽ መርዕድ አዝማች አስፋ ወሰን ኃይለ ሥላሴ ስም ተጻፈ የተባለ፤ ሕሊናን የሚረብሹ ነጥቦችን ያዘለ ደብዳቤ ተመልክተናል። በታኅሣሥ ፶፫ቱም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ያተረፉትን፤ እንደሙጫ ስማቸው ላይ ተጣብቆ የቀረውን ሐሜታም ተመልክተናል።

፪ኛው ክፍል ደግሞ የምንዳስሳቸው የብሪታኒያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብት ሰነዶች በተለያዩ ጊዜያት አልጋ ወራሹ ከብሪታኒያ ርዕሰ-ልዑካን እና ከአሜሪካው ርዕሰ-ልዑካን ጋር ያካሄዷቸውን ሰፊ ውይይቶችና በወቅቱ የአገር ፖለቲካ ላይ ለነኚሁ የባዕድ መንግሥታት ወኪሎች የሰጡትን አስተያየት ያካትታል።

Sunday 27 January 2013

አስፋ ወሰን ኃይለ ሥላሴ - ክፍል ፩


(ከድል እስከ ታኅሣሡ ጉሽ)

ቻርድ ግሪንፊልድ የልዑል አልጋ ወራሽ መርዕድ አዝማች አስፋ ወሰን ኃይለ ሥላሴን ሞት ተከትሎ በብሪታንያው ‘ኢንዲፔንደንት’ ጋዜጣ ላይ በጻፉት የሙት መወድስ (ኦቢችዋሪ) ላይ «መስከረም ፲፯ ቀን ፲፱፻፱ / መኳንንቱ እና  የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንቱ በተሰበሰቡበት አቡነ ማቴዎስ የልጅ ኢያሱን መሻር እና መወገዝ ሲያበስሩ፤ ሕፃኑ አስፋ ወሰን በአንቀልባ ታዝሎ ከሁለት አሽከሮች ጋር እንግሊዝ ለጋሲዮን ተደብቆ ነበር።»[1] ይላሉ።

Monday 21 January 2013

ወይዘሮ ዘውዲቱ፤ ራስ ጉግሳ ወሌ እና ቀብራራው አርምብራስተር!



ንደው እመ-ብርሃንን ወገኖቼ፤ የነጮች ጥጋብ ሁሌ እንደገረመኝ ነው!

እውነት ነው በአሥራ ዘጠነኛው እና በከፊልም ቢሆን በሀያኛው መቶ ክፍለ ዘመን፤ በተለይም እንግሊዞቹ እና ፈረንሳይቹ ጉልበተኛ ፈላጭ ቆራጭ ስለነበሩ የንቀታችውን መጠን ግፋ ቢል፤ በአዕምሮ ሚዛን ልንረዳላቸው እንችል ይሆናል። ያውም እኛ ኢትዮጵያውያን እራሳችንን ከሌሎቹ ገለል አድርገን የነጮቹን አስተሳሰብ የተገነዝብልናቸው እንደሆነ ነው።
ወደዋናው ጉዳይ ከመመለሴ በፊት አንድ የሰማሁትን ላካፍላችሁ።  በሃያኛው መቶ ክፍለ-ዘመን አገር ለመጎብኘት (መጎብኘት ሲባል መሰለል ብለው ያንብቡ!!!!) የገባ እንግሊዛዊ ወደአገሩ ለመመለስ በባቡር ከአዲስ አበባ ወደ ጂቡቲ እያመራ ነው።  እንግሊዛዊው እንደለመደው በአንደኛ ደረጃ ክፍል እያነጎደ ነው። የእኛ ሰዎች ግን በገዛ አገራቸው፤ የአንደኛ ደረጃውን ካርኔ ከአቅም በላይ እንዲሆን አድርገውባቸው ይሆናል፤ ብቻ ምን አደከማችሁ አንባብያን! በሦስተኛ ማዕርግ ላይ ነው ከመቶ ወደ ዘጠና ዘጠኝ ነጥብ ስድስት የሚያክሉት ተሣፋሪዎች የተጨቀጨቁት። (ነጥብ ስድስቱ ታዳጊ ወጣት መሆኑ ይሆን? ለነገሩ ግን ይሄ  ዘጠና ዘጠኝ ነጥብ ስድስት የሚሉ አመዛዘን ያኔም ነበር ማለት ነው? ወይስ አዲስነቱ ለሕዝብ ሸንጎ ቆጠራ ነው? )

Thursday 17 January 2013

ሃሪንግቶን ያስገረፋቸው ቀኛዝማች

 ሆኜ አባቴ (ነፍሳቸውን ይማርና) እከሊት/እከሌ ሰደበች/ ብለህ በሷ/በሱ ላይ አታማር፤ አንተ እራስህ ባትፈቅድላቸው ኖሮ አይሰድቡህም ነበር፤ ይሉኝ ነበር። ታዲያ በዚያ ባልበሰለ እና ጨቅላ አመለካከቴ፤ ምን ማለታቸው ነው? መቼ ፈቅጄለት ነው፣ አብሮ-አደጌ እሸቱ ጠንጌ እኔን ብቅል አውራጅብሎ የሰደበኝ? እኒያስ የትምህርት ቤቴ ምክትል ዳይሬክተር፣ አቶ ፋኖሴ ባቡርእያሉ የተሳለቁብኝ፣ እኔ ምን ብዬ አበረታትቻቸው ነው? እሳቸውንስ እንኳ አጭር፣ ደቦልቦል ያሉና በአራት እግራቸው እንጣጥ ለማለት የተዘጋጁ ይመስሉ ስለነበር፣ ዕንቁራሪትእላቸው  ነበር፤ በእኔ ቤት የሰደቡኝን ያህል የመለስኩላቸው ይመስለኝ ነበር። ልዩነቱ ግን እሳቸው በአደባባይ የለጠፉብኝን የእኔ አጸፋ ግን በሕሊናዬ፣ ደፈርም ያልኩ እንደሁ ከባልንጀሮቼ ዦሮ አልፎ አያውቅም ነበር።

ካደግሁ እና ደጉን ከመጥፎ፤ በመጠኑም ቢሆን  መለየት ከቻልኩ በኋላ ነው የአባቴ ቁም ነገር የገባኝ። እውነትም አንድ ሰው ሊሰድብህም፣ ሊንቅህም፣ ሊደፍርህም የሚበረታታው አንተው እራስህ ስለፈቀድክለት መሆኑን አትርሳ። 

ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ብልህ መሪ፤ አደራዳሪ፤ አርቆ-አስተዋይ፤ ትዕግሥተኛ፤ ርኅሩኅ፤ ወ.ዘ.ተ. በሚሉ ቅጽሎች በታሪክ መዝጋቢዎችና በውጭ ዜጎችም በብዛት የተመሰከረላቸው ንጉሠ ነገሥት ከመሆናቸውም ባሻገር፤ በተለይም ቀድመዋቸው ካለፉትም ሆነ ከተከተሏቸው የአገራችን መሪዎች ጋር ሲነጻጸሩ በባህሪያቸውና በአገዛዝ ልታቸው፣ እንዲሁም በተራማጅ አመለካከታቸው ያለጊዜያቸው የኖሩ ታላቅ መሪ እንደነበሩ በብዙ ተመስክሮላቸዋል። ያም ሆኖ ዘመናችን ያፈራቸው አንዳንድ ዋሾዎችና ታሪክን ለመካድ የሚቃጣቸው ወገኖቻችን የዕምዬ ምኒልክን ስም ለማጉደፍ የሚሰነዝሩባቸው ዘለፋ ሰፊውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከማስቆጣት እና ከማነሳሳት በስተቀር ለታሰበው የፖለቲካ ማራመጃ አልበጃቸውም/አይበጃቸውም።

ዛሬ ይሄንን መጣጥፍ ለመጫጫር ያነሳሳኝ ጉዳይ፤ በእንግሊዞቹ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብት ታሪክ ስቆፋፍር 
ሰር ጆን ሌን ሃሪንግቶን
ያገኘሁት፥ የዛሬ መቶ አሥራ-አንድ ዓመት መጋቢት ፲፰ ቀን ፲፰፻፺፬ ዓ/ም የተጻፈ፤ ባለ አሥራ-ሦስት ገጽ ደብዳቤ ሲሆን፤ ደራሲው በወቅቱ በአገራችን የብሪታኒያ መንግሥት የመጀመሪያው ቋሚ ወኪል የነበረው መቶ-ዓለቃ (በኋላ ሰር) ጆን ሌን ሃሪንግቶን ነው። ደብዳቤው የዚህ ቋሚ ወኪል ወርሐዊ ኀተታ ሲሆን አጻጻፉም እንደማስታወሻ ደብተር በየዕለቱ የሞላው ኀተታ ነው። ስለጉዳዩ ባለቤት የቀኛዝማች ማእርግ እንዳላቸው እንጂ ስለማንነታቸው የነገረን ዝርዝር ነገር ባይኖርም፣ (ቀኛዝማቹን ከዚህ ክስተት አራት ዓመታት በኋላ ጎሬ ከተማ ላይ የአውራጃው ምክትል ገዥ ሆነው ያገኛቸው አርኖልድ ሄንሪ ሳቬጅ ላንዶር፣ ስለጉዞው በጻፈው መጽሐፍ ላይ ቀኛዝማች ወልደ ገብርኤል  መሆናቸውን አስፍሯል።)[1] ሃሪንግቶን ስለዛሬው ርዕሴ እንዲህ ይላል። 

          «የዚያ የሰደበኝ ቀኛዝማች ወይዛዝርት ቤተ ዘመድ መጋቢት  ቀን  እሱን ይቅር እንድልላችው ሊለምኑኝ መጥተው ነበር። የነሱ ልመና ግን ምንም ፋይዳ ሊያመጣ አልቻለም። እንደሰማሁት ሰውዬው በመኳንንቱ ዘንድ በጣም የታወቀና ወንድሙም ፊታውራሪ ናቸው ይባላል። ይኼ ማለት እንደውም የበለጠውን ተሳዳቢው ለምሳሌነት መቀጣት አለበት ያሰኘኛል።» ሃሪንግቶን ስድብ ነው የሚለው ምን እንደነበረ፤ መቼ እንደተከሰተ ወይም በምንስ ሁኔታ እንደተከሰተ አይነግረንም። ከአጻጻፉ እንደምንረዳው ግን ለሪፖርት ተቀባዩ ከዚህ በፊት አስረድቶት እንደነበር መገመት እንችላለን።

ሃሪንግቶን ይቀጥልና፣ «ጃንሆይ ነገ [መጋቢት ] ወደ አዲስ ዓለም ከመሄዳቸው በፊት ተቀብለው  አነጋገሩኝ፤ እኔም በዚያ በሰደበኝ ሰውዬ ላይ መቼ እንደሚፈርዱልኝ በመጠየቅ ጉዳዩን አነሳሁባቸው» በሚል ሀረግ ይጀምርና «እሳቸውም፣ ቀኛዝማቹ በሰንሰለት ታሥሮ እንደከረመና አሁንም ንብረቱ ኁሉ እንደሚወረስ፤  እስራቱም በእስላም ቤት እንደሚደረግ ነገሩኝ።»

«በዚህ በተሳዳቢው ላይ እንዲፈርዱልኝና በኔ አስተያየት (ከጥፋቱ ጋር የሚመዛዘነው ፍትሐዊ ቅጣት) የሚገባው ቅጣት በአደባባይ ሲገረፍ ብቻ ነው አልኳቸው።» ይልና «ሰውዬው ከሰደበኝ ዕለት ጀምሮ እስካሁን በእግርና በእጅ ሰንሰለት ታሥሮ እንደከረመ አውቃለሁ። ነገር ግን ትልቅም ሆነ ትንሽ አበሻ የሚያጋጥመው ቅጣት ስለሆነ ለኔ ምንም አልመሰለኝም። በተለይም እስረኛው ባለወገን ከኾነ ሰንሰለቱ አይመቸው እንጂ ቅጣቱ ቀላል ነው። የለም! አበሾቹ እንደ ትልቅ ቅጣት የሚቆጥሩትን የአደባባይ ግርፋት ካልሆነ ምንም ፍላጎቴ አይረካም። የኔም በጉዳዩ ላይ ችክክ ማለት በከተማው ሙሉ ትልቅ ሹክሹክታ መፍጠሩ አይጠረጠርም።  ኾኖም ያን ሰውዬ በአደባባይ ለማስገረፍ ያለኝ ፍላጎት እጅግ ከፍ ያለ ቢሆንም፤ ምናልባት ንጉሠ ነገሥቱ መኳንንቶቻቸውን ላለማስቀየም ሲሉ የኔን ዓላማ ላያሳኩልኝ ይችላሉ ብዬ ፈራለሁ።  ዳሩ ግን ጉዳዩ የመንግሥት ጉዳይ እንዲሆን፣ ወይም የዲፕሎማቲክ ክብር እንዲያገኝ አልፈለግሁም።» ይላል።
ይኽን ይበል እንጂ ግን ለዓለቆቹ ዓይን የተጻፈው ይህ ደብዳቤ የሚያራምደው ኀቅ ይህንኑ አልፈልግም የሚለውን 'የዲፕሎማቲክ ክብር' ነው።

ይኼ ውይይት የስዊሱ ተወላጅና የንጉሠ ነገሥቱ አማካሪ የነበረው ቢትወደድ አልፍሬድ ኢልግ በአስተርጓሚነትም በአማካሪነትም በተገኘበት መሆኑን ሃሪንግቶን ያበሥርና ቀኛዝማቹን በአደባባይ ለማስገረፍ የወጠነውን ዓላማ ለማጠናከርና ለጃንሆይም ወጥመድ ለማጥመድ ሲል ኢልግን፤ 
«ከአንተ እንደተራድሁት የዚህን ሰውዬ መቀጣት መኳንንቱ ተቃውመዋል ብለኸኛል። እኔ ጃንሆይን ሕዝባቸው የማይቀበለውን ምንም ዓይነት ነገር አድርጉልኝ ብዬ አልጠይቅም። የጠይቅሁት ፍትህ ከጃንሆይ ሥልጣን በላይ ከሆነ፤ እሳቸው ይኼንኑ ገልጸው ቢነግሩኝ ጉዳዩን እርግፍ አድርጌ እተወዋለሁ።» ሲለው ኢልግ ክው ብሎ በመደንገጥ «የፈጣሪ ያለህ! ይኼንን ማነው ደፍሮ ለጃንሆይ የሚነግረው አለኝ ይለናል።

«ኢልግ ይሄን ሲለኝ» ሃሪንግቶን ይቀጥላል፤ «እኔ ስለሰውዬው በሰንሰለት መቀብደድ ደንታ የለኝም፤ ምክንያቱም ሁሉም አበሻ ይሄንን ዓይነት ድሎት የሚቀምሰው ነገር ስለሆነ እንደተራ ቅጣት ነው የሚቆጠረው። በአደባባይ መገረፍን ግን ለሌም ትምህርት ስለሚሆን፤ በኔ በኩል የበለጠ ተቀባይነት ይኖረዋል አልኩት» እያለ ያሽሟጥጥ«ንጉሠ ነገሥቱ ታዲያ ለክርስቲያን ሰው ደግሞ ‘እስላም ቤትከመታሠር በላይ የበለጠ ቅጣት የለምቢሉኝም በቀኛዝማቹ ላይ እኔ ምንም ዓይነት የግል ቂም እንደሌለኝና በሱም ላይ እንዲህ ያለ ብርቱ ቅጣት እንደማልፈልግ፤ ሰውዬውም ዕድሉ ሆነና እንደዚህ ዓይነቱን ጥፋት ማጥፋቱ ነው ለአደባባይ ግርፋት የሚያበቃው። ብዬ መለስኩላቸው።» በማለት ይመጻደቃል።

«እኔ የፈለግሁት» ይላል የብሪታኒያው ወኪል፤ የውስጡን ምስጢር ለዘገባ ተቀባዩ ሹክ ሲል፤  «ሌሎች [አበሾች ማለቱ ነው!] ነጭን ሰው፤ አልፎ ተርፎም የመንግሥትን ወኪል ቢሳደቡ በራሳቸው ላይ የሚያመጡትን መዘዝ በውል እንዲያጤኑት ስለሆነ በአደባባይ መገረፉን ነው። ሆኖም ለምሣሌነት ብቻ ሁለት አለንጋ ከቀመሰ በኋላ ግርፊያውን ለማስቆም ወስኛለሁ።»
         
በጉዳዩ ብዙ ከተነጋገሩበት በኋላ ዳግማዊ ምኒልክ በግርፋቱ ተስማምተው «መቸ ይደረግልህ? አንተ ባለህበት እንዲፈጸም» አሉኝ ይላል። ኢልግ አትናገር የተባለውን ከላይ የተገለጸውን ወጥመድ ለምኒልክ ቢነግሯቸው ይሆን በግርፋቱ የተስማሙት?  አሁንም የውስጡን ተንኮል በሚያሳብቁበት ቃላት «ቅጣቱ በገበያው መኻል ቢፈጸም ደስ ይለኝ ነበር፤» ይልና ቀኛዝማቹን ማስገረፉ  ብቻ አልበቃ ብሎት፤ የኢትዮጵያንም ንጉሠ ነገሥት ለማዋረድ/ለማንበርከክ ፍላጎት እንደነበረው በቀጣይ ትንፋሹ ፍልጭታ ሰጥቶናል። «…ነገር ግን ንጉሠ ነገሥቱ ገበያው ላይ ስለማይገኙ የተፈለገውን ውጤት አያስገኝም» ይልና በዚያው በተለመደው እንግሊዛዊ ምሥጥ ባሕሪው «ቅጣቱን የሚመለከተው የሕዝብ ቁጥር፣ እሳቸው ከሌሉ አነስተኛ ስለሚሆን ጃንሆይ እዚያው እግቢ ነገ ጧት ቢሆንስ? ብለው ያቀረቡልኝን ሓሣብ ተቀበልኩ።» በማለት የዕለቱን ውይይት ዘገባ ይደመድማል፡፡

በማግሥቱ ከጧቱ አንድ ሰዓት ላይ ሃሪንግቶን እና ዳፍ የተባለው የሌጋሲዮኑ ባልደረባው እግቢ ሲደርሱ ቢትወደድ ኢልግ እና ሌሎችም  በተገኙበት፤ የዙፋናዊ ፍርድ ቅጣት በሚተገበርበት  ‘እንቁላል ቤት’ ፊት ለፊት ካለው ሥፍራ ላይ ቀኛዝማቹ፣ እጅና እግራቸውን በብረት ሰንሰለት ታሥረው ቀረቡ። ወዲያው ሰንሰለቶቻቸውን ፈቱላቸውና አጋድመው እጅና እግራቸውን በወፍራም ገመድ ሲወጥሯቸው «በሥላሴዎችና በቅዱሳኑ ሁሉ ስም» ምህረት እንዲደረግላቸው ይማጠኑ ነበር። ሃሪንግቶን ታዲያ «ሁለት አለንጋ እንደቀመሰ፤ ከቆምሁበት ከፍተኛ ቦታ ላይ በአስተርጓሚዬ "በቃው! እሥራቱን ተመልክቼ/አመዛዝኜ/ ትቸዋለሁ። ነገር ግን ለሱም ሆነ ለሌሎች፤ የሚያስቡላችሁንና ለነሱም በዚያው ልክ እንድታስቡላቸው የሚፈልጉትን ነጮች ለመሳደብ የሚቃጣቸው ሁሉ ከዚህ ቅጣት ትምህርት እንደሚወስዱ ተስፋ አደርጋለሁ።» ብዬ ተናገርሁ ይላል።

ተመልካቾቹ ሁሉ ቀኛዝማቹ በሁለት አለንጋ ብቻ በመለቀቃቸው ተገርመው እንደነበር ሃሪግቶን ሲያብራራ «ቅጣቱን የሚያካሂደው መኮንን መጥቶ እጄን በመሳም አመሰገነኝ» ይልና የቅጣቱንም መፈጸም ለማብሠር ወደጃንሆይ ቃል ተላከ። እሳቸውም ቢፈታ ትፈቅዳለህ ወይ? ብለው ቢልኩብኝ አዎ ብዬ በላክሁት መላክተኛ የተለመደውን መቶ አለንጋ እንዳይቀጣ በመከልከሌ ምሥጋናቸውን ላኩልኝ ይላል።

ይህን ጉዳይ በዘገባው ላይ ሲደመድም፤ «...በዚህ ቅጣት ላይ ሽንጤን ገትሬ የያዝኩትን ደረቅ አቋም በቁርጥ እንድጥለው ባለመገፋቴ እድለኛ ነኝ።» በሚሉ ቃላት ሲተነትነው ታሪኩን ከላይ ጀምረን በብዙ በተለያዩ ስሜቶች ተመሥጠን ስንከታተል፤ ከአንዴም፣ ሁለቴም ይሄ ነጫጭባ  አገራችንንም ንጉሠ ነገሥታችንንም እንዴት ቢንቅ ነው እምዬ ምኒልክን ምን ቢያቀምሳቸው ነው እስከዚህ እንዲደፍራቸው መፍቀዳቸው?” የመሳሰሉ ጥያቄውችን ስናመላልስ ቆይተን እውነትም ዞር በል! በአገራችን፤ እንኳንስ በዜጋችን ላይ ቀርቶ በእንግዳም ላይ ቢሆን የፍርድን ቅጣትም ሆነ ምህረት የምንሰጠውም እኛ ነን እንጂ አያገባህም ቢሉት ምናባቱ ያመጣ ኖሯል?

ለእኔ በግሌ ይህን መጣጥፍ የከፈትኩበትን የአባቴን የሕይወት መርሕ አስታውሶኛል። እውነትም አንድ ሰው ሊሰድብህም፣ ሊንቅህም፣ ሊደፍርህም የሚበረታታው አንተው እራስህ ስለፈቀድክለት መሆኑን አትርሳ!!

በዚሁ አብረን እየጋለብንበት በሚያዥጎደጉደን የታሪክ አውሎ ነፋስ’ የፍጥነት ማርሽ እናግባና ወደፊት እንምጣ። የሚቀጥለው ማረፊያችን ከስድስት ዓመታት በኋላ፣ ጥቅምት ፲፰ ቀን ፲፱፻ /ም፤ ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ በጊዜው ተጠባባቂ የብሪታኒያ ወኪል ለነበረው ቶማስ ሆህለር (Thomas Beaumont Hohler) የጻፉት ደብዳቤ ነው። ይህ ደብዳቤ በሚጻፍበት ጊዜና ላዘለውም ጉዳይ መፍትሔ በሚሹበት በዚያ ጥቅምት ወር፤ አሁን ሰርየተባለው ጆን ሃሪንግቶን፣ ሚስት ለማግባት ወደአገሩ ሄዶ ነበር።[2]
         
የተገኘው ደብዳቤው ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎመ ሲሆን፣ እኔ ወደአማርኛ መልሼዋለሁ፤
«የንጉሠ ነገሥት ማኅተማችንን አስፍረን፣ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴራችሁ ሰር ጆን ሃሪንግቶንን በተመለከተ ጥቅምት ፲፫ ቀን፣ የጻፍነውን ደብዳቤ በቴሌግራም ለማስተላልፍ ፈቃደኛ እንዳልሆንክ ነግረኸኛል» በሚል ኃይለ-ቃል ይጀምራሉ። «ለብዙ ጊዜ ሁለቱን አገሮቻችንን በወዳጅነት የሚያስተሳስሩ ነገሮችን ስፈልግና ስመኝ ኖሬእለሁ።«ሰር ጆን በሚናገረን ቃላት ሁሉ ጨዋነትንና የሚገባንን ክብር ስለማያሳየን፤ በምትኩ ሌላ ሚኒስቴር እንዲላክልን ፈቃዳችን ነውና ወደመንግሥትህ ይሄንን ማስተላለፍህን በጽሑፍ እንድታረጋግጥልን ይሁን።» የሚል ደብዳቤ ልከውለታል። 

ሆህለር በማግሥቱ የላከላቸው መልስ ታዲያ፦
«ግርማዊ ጃንሆይ! «በትናንትናው ዕለት ሰር ጆንን በተመለከተ ጉዳይ የላኩልኝን ደብዳቤ ስረከብ ከፍ ያለ ክብር ተሰምቶኛል።
«ግርማዊነትዎ በሁለቱ አገርቻችን መኻል የቆየውን ወዳጅነት ለማጠንከር ያለዎትን ምኞት ከልቤ እጋራዋልሁ። ስለሆነም ከግርማዊነትዎ ጥቅም ጋር የሚጻረር እርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኛ አለመሆንን መምረጤን ጃንሆይ እንዲፈቅድልኝ እለምናለሁ። ግርማዊነትዎን እዚህ ውሳኔ ላይ ያደረሱዎትን ምክንያቶች በቃል ያስረዳሁ ስለሆነ፤ ፍጹም ውሳኔ ላይ ከመድረስዎ በፊት በጥንቃቄ እና በጥሞና እንዲያጤኑት እለምናለሁ።»

በሚል ደምድሞ እነነኚህን ሁለት ደብዳቤዎች አባሪ አድርጎ ወደ አገሩ አስተላልፏል።[3] በዚህ ደብዳቤው ላይም ይኼንን እርምጃ እንዲወስዱ የገፋፏቸው የመንግሥታችንም የሃሪንግቶንም ጠላት በሆነው አንዱ የውጭ መንግሥት የተነሳሱት ነጋድራስ ኃይለ ጊዮርጊስ (በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር)፤ ፀሐፊ ትዕዛዝ አፈወርቅ፤ ልጅ በየነ (የቴሌግራፍ ዓለቃ) እና ምናልባትም የገንዘብ ሚኒስትሩ በጅርንድ ሙሉጌታ ናቸው በማለት ለዓለቆቹ ካስረዳ በኋላ የንጉሠ ነገሥቱን ጥያቄ እንዳይቀበሉት ያሳስባል።
          እውነትም ሰር ጆን ሃሪንግቶን አዲስ አሜሪካዊት ሚስቱን ይዞ ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ እስከ ፲፱፻፩ ዓ/ም ከቆየ በኋላ ሥራውን ‘በፈቃዱ’ ለቆ ወጥቷል።

እንግዲህ ጃንህይ ምኒልክ በእኒያ በቀኛዝማች ወልደ ገብርኤል ቹ ጉዳይ ላይ ሥልጣናቸውን ቢያስረግጡ ኖሮ፤ የኋላ የኋላ  ያውም ላይሰሟቸው  “በአነጋገሩ ትህትና የለውም” እና ሌላ ሰው ተኩልኝ ለማለት ባልደረሱ። እስቲ ይታያችሁ በገዛ አገራቸው፤ ይመቸኛል የሚሉትን እንኳን ወኪል ማሾም አለመቻላቸውን፤ የኔ አባት ባስቀመጡት መልኩ ከማየት በስተቀር ሌላ አመለካከት ሊኖረው ይችላል ትላላችሁ?

በተለየ መንገድ ማየት የሚችል አንባቢ ካለ አመለካከቱን ብንካፈለው ይጠቅመናልና። እስከዚያው ድረስ የሕይወቴ መርሖዬ አሁንም፦

 አንድ ሰው ሊሰድብህም፣ ሊንቅህም፣ ሊደፍርህም የሚበረታታው አንተው እራስህ ስለፈቀድክለት መሆኑን አትርሳ!!”

ዋቢ ምንጭ  
P.R.O. F/O  "CONFIDENTIAL PRINT ABYSSINIA" (1902)



[1] Landor, Arnold Henry Savage; ACROSS WIDEST AFRICA (1907; pp 191-195


[2] THE NEW YORK TIMES; “ABYSSINIA ON HONEYMOON”; PUBLISHED OCTOBER 13, 1907
[3] P.R.O [38782 / despatch # 71] Hohler to Gray, 31st October 1907