Friday 13 May 2011

«ተጨናቂው የኢትዮጵያ አንበሳ»



በታኅሣሥ ወር ፲፱፻፶፫ ዓመተ ምሕረት የተከሰተው የነመንግሥቱ ነዋይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የኢትዮጵያን ንጉዛት አናውጦት ካለፈ ዓመት ከሦስት ወር ሆኖታል። ጄኔራል መንግሥቱም በዚያው ምክንያት በስቅላት ከተገደሉ እነሆ ዓመት አለፋቸው። እቴጌ መነንም ከተለዩን ገና ሦስት ወራቸው ብቻ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ብዙ የአፍሪቃ አገሮች ከአውሮፓውያን የቅኝ ግዛት ቀንበር ተላቀው የነፃነት እግራቸውን በዳዴ ለማጠናከር እየተፍጨረጨሩ ነው።

ታዲያ በዚያ ወቅት የአሜሪካው ‘ታይም’ መጽሔት ግንቦት ፳፬ ቀን ፲፱፻፶፬ ዓመተ ምሕረት፤ «ተጨናቂው የኢትዮጵያ አንበሳ» በሚል ርዕስ ያወጣው ዓምድ ስሜቴን በተለያየ መልክ የፈተነ ጽሑፍ ነው። መቸም መራራ ሐቅን እቅጭ አድርገው ሲነግሩት የሚያሽረው ጥቂት ነውና። 

በመግቢያው አንቀጽ ላይ የአዲስ አበባ ሴት ዝሙት አዳሪዎች ማስተወቂያቸው “ቀይ መስቀል” ነበረ። ነገር ግን የዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ማኅበር መዝናናት የሚፈልጉ ብዙ ወንዶች እየተሳሳቱ በየክሊኒኮቼ ዘው እያሉ አስቸገሩኝ በማለቱ፤ እነኚህ ሴቶች ምልክታቸውን ወደ ቀይ መብራት እንዲለውጡ የመንግሥት ድንጋጌ መውጣቱን ያበሥራል። ታዲያ ይሄ ድንጋጌ ሥራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የነኚህ የወንድ መዝናኛ ቤቶች ከአምስት ሺ ወደ ስምንት ሺ ማደጉንና የአካባቢው የመብራት ኃይል ፍጆታም ማሸቀቡን ይዘግባል።

ዛሬ ቢሆን “የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት በእጥፍ አኃዝ ማደጉን የ’ታይም’ ጋዜጠኛ መሰከረ።” ነበር ርዕሰ አንቀጹ የሚለው።

 ‘ታይም’ እድገቱ የወቅቱን ለውጥ እንደሚያረጋግጥ ሲጠቁም፤ ምክንያቱንም ኢትዮጵያን የአፍሪቃ ነጻነት ትግል እምብርት ለማድረግ ንጉሠ ነገሥቱ የሚያደርጉት ጥረት በርዕሰ ከተማዋ በሚካሄዱት ሥፍር-የለሽ ስብሰባዎች ላይ ለመሳተፍ የሚጎርፉት እንግዶች ናቸው ይላል።  [ሌላው ቢቀር፣ ሽርሙጥና ከፍ ያለ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ሆነልን ማለቱ ይሆን? የትም ፍጪው፣ ዱቄቱን አምጪው! ይባል የለ?]

ወደታሪክ መለስ ብሎም «እነኚህ ዘራቸውን ከንጉሥ ሰሎሞንና ከንግሥት ሣባ በመምጣቱ የሚኮሩ
ኢትዮጵያውያን - ለብዙ ምዕት ዓመታት ጥቁር አፍሪቃውያንን “ባሪያ” እያሉ በማንቋሸሽ ኖረዋል።» ነገር ግን የጥቁር አፍሪቃ አገራት ነፃ እየወጡ ድምጻቸውን በዓለም መድረክ ላይ ማሰማት ከጀመሩ በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ፣ ድሮ “ባርያ” እየተባሉ የሚናቁትን አሁን ግን «ተወዳጅ ጥቁር ወንድሞቻችን» በሚል ለአኅጉሩ መሪዎችና ታጋዮች የቅኝ-ግዛትን ሥርዓት በማውገዝ በደብዳቤ መልዕክቶቻቸውን ማብረር ጀመሩ። ካለ በኋላ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሰሞኑን በ ሦስት ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ($3,000,000) በተገነባው አዲሱ የ’አፍሪቃ አዳራሽ’ ውስጥ ተንቀሳቃሹን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅኝ  ግዛት ሸንጎ አባላትን እንደሚያስተናግዱ ይነግረናል። ከካቢኔ ሚኒስትሮቻቸው አንዱ “ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እንደዚህ አይነት መስተንግዶ ለአፍሪቃ አኅጉር መሪነት ያላቸውን ምኞት እንደሚያሳካላቸው ያምናሉ” ይላል ።

ይኸው ኢትዮጵያዊ የካቢኔ ሚኒስቴር «እኛ ከሁሉም የቆየ ነፃነት አለን። በቅርብ ነፃነታቸውን የተቀዳጁትን ወንድሞቻችንን ደግሞ ወደዘመናዊው ዓለም የመምራት ግዴታችንም ቅርሳችንም ነው» ብሏል በሚል ጽሑፉን ያዘጋጀው የመጽሔቱ ቃል አቀባይ ጠቅሶታል። ታዲያ የጽሑፉ ደራሲ ጋዜጠኛ «ይቺ ከዓለም ኋላ ቀር አገሮች መኻል የምትሰለፍ አገር፤ ፓርላማዋ ሥራውም ሆነ ችሎታው የንጉሠ ነገሥቱን ፍጹም ሥልጣን በማኅተም መርገጫ የማጽደቅ ብቻ የሆነባት እና የመገናኛ ብዙሐን ነፃነት የማይከበርባት፤ ሰላዮችና ጆሮ ጠቢዎች በሰፊው የተሠማሩባት ኢትዮጵያ እንኳን ሌላ አገሮችን ወደዘመናዊው ዓለም ለመምራት ቀርቶ፣ እራሷም መንገዱ በየት እንደሆነ አይታውም አታውቅ።» በሚል ከእሳት ማዕበል የበለጠ በሚፋጁ ቃላቶቹ ሸንቁጦናል። የምታቦካው የላት የምትጋግረው አማራት አሉ አባቶቻችን!
ይሄ ብቻ መቼ በቃውና! ያ ብስለት የጎደለው፣ ጉረኛ [እንዲያውም ትዕቢት የተሞላበት ቃላቶች በመሰንዘሩም ‘አሳዳጊ የበደለው ባለጌ’] የካቢኔ ሚኒስቴር በሰነዘራቸው ቃላት መነሻነት ለጋዜጠኛው የስድብ ነጎድጓድ ዳርጎናል። ሞኝና ወረቀት የያዙትን አይለቁም እንደሚባለው ከልጅነቱ ጀምሮ ሲሰማው የቆየውን የስህተት አመለካከት ማረም እንኳ ያልቻለ ትሩማንትሪ!
መቸም በዚህ ጽሑፍ ላይ የሠፈሩትን ነጥቦች እውነተኛነት ላለመቀበል ሳይሆን፤ በባእድ ብዕር መሰደባችን እየከነከነኝ ነው። «ወንጀለኛ በአደባባይ የሚሰቀልበት አገር፣ ከነአካቴው የወህኒ ቤቶችን መጣበብ ለማቃለል እና ለ’እኔን አይተህ ተቀጣ’ም እንዲያመች በእሥራት ፋንታ በአደባባይ መገረፍ በቅርቡ ተፈቅዷል » ይልና፤ ስለሙስናም ሳይተርብ አያልፍም። በዘገባው እንዳሰፈረው ባለ ሥልጣናቱ በሙስና ከመጨማለቃቸው ብዛት ከሚሰበሰበው ቀረጥ ሲሦው ወደመንግሥት ካዝና አይገባም ብሏል።

የመንግሥቱ የአስተዳደር ብዛትና ክብደት ከአገሪቱ ዓመታዊ ወጭ ሁለት ሲሦውን ይበላዋል፤  በሀያ ሚሊዮን የሚገመተው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአገሪቱ ሀብት የሚደርሰው በዓመት በአማካይ አምሥት የአሜሪካ ዶላር እንደሆነ፤ ከመቶ ሕዝብ ዘጠናው መሐይም፤ ሰማንያ በመቶው ደግሞ በጥገኛ ነፍሳት የተጠቃ፤ ገሚሱ የወሲብ በሽታ የተጸናወተው እና አርባ ከምቶ የሚሆኑ ሕጻናት እንደሚሞቱ፤ ወባ በየዓመቱ ሰላሳ ሺ ሰዎችን እንደሚገልና ከመቶ ከብቶች አርባዎቹ በሳምባ ነቀርሳ የተለከፉ እንደሆኑ ይተነትናል።

ኧረ በፈጠረህ ይበቃል! አልኩኝ ፣ አጠገቤ ያለ መስሎኝ!
እሱም «አንዴ ጀምሬዋለሁና በትእግሥት አስጨርሰኝ» የሚለኝ መሰለኝ። ለጥቆም «የነጮች ልምዳዊ ማሳጣት ነው፤ ይሄን ሁሉ የሚያስተነትንህ እያልከኝ አይደል? እሺ የኔንስ እንደዚያ ገምተው። ስብሰባ ላይ ሊሳተፍ የመጣውስ ጥቁር፤ አፍሪቃዊ፤ ሴኔጋላዊስ? ምን እንዳለኝ ታውቃለህ?» ይለኛል። አያችሁ በታሪክ አውሎ ነፋስ እይተውዠገዠገ መጥቶ ልቦናዬን እንዴት እንደሚያስተኝ? ወቸ ጉድ!

ይሄ ሴኔጋላዊ የአዲስ አበባን አራት መቶ ሃምሣ ሺ ነዋሪዎች ድህነት፤ መራቆት እና  የኋላ ቀር ኑሮ ከተገነዘበ በኋላ “የነፃነት ውጤት ይሄ ከሆነ፤ መልሳችሁ ግዙኝ።” ብሎኛል አለ ጸሐፊው። ያ ምስኪን ሴኔጋላዊ ነፃነትን በቀመሰ በሁለት ዓመቱ እንኳንስ እኛን እንደመሪ ሊቆጥር ጭርሹንም የእኛ ኑሮ አቅለሽልሾት ነፃነቴ ይቅርብኝ እስከማለት መድረሱ ለጋዜጠኛው አመለካከት ድጋፍ እንደሰጠውና የዚያም የካቢኔ ሚኒስትር አጉል ድንፋታ ፍሬ-ቢስ እና ውዳሴ ከንቱ መሆኑን በማያሻማ መልክ አረጋግጦታል። ጉድ እኮ ነው!

ተንኮለኛው ዘጋቢማ ምን ዕዳ አለበት? «ይሄ ሁሉ [ኋላ ቀርነት] ለጞብኚ አፍሪቃውያን ምን ዓይነት አሉታዊ ስሜት እንደሚፈጥር የተገነዘቡት ንጉሠ ነገሥት»፣ ይላል አሜሪካዊው፤ «የኢንዱስትሪያዊ ልማት ከመጀመራቸውም ባሻገር ግድቦችን፤ ነዳጅ ማጣሪያ፤ ወደቦችን እና ፋብሪካዎችን ለማሠራት ከምዕራባውያንም ከምሥራቃውያንም ዕርዳታ እየተቀበሉ ነው።» ዳሩ ግን የራሳቸውን ሥልጣን ይቀንሱብኛል ብለው የሚያምኗቸውን የአስተዳደር እና የፓርላማ ማሻሻያ እርምጃዎችን ለመውሰድ አሻፈረኝ እንዳሉም አብሮ አስፍሯል። ከአሥራ ሰባት ወራት በፊት በንጉዛቱ ሥርዓት ላይ ተነስተው የነበሩት ምሑራን እና ተራማጅ ወገኖች፤ ምንም እንኳ የኃይለ ሥላሴ መንግሥት በሹመት፣ በሽልማት ሊደልላቸው ቢሞክርም እንቅስቃሴያቸው አልበረደም። ሆኖም እራሳቸውን በቅጡ ያላደራጁ እና ቀጣዩ የተቃውሞ እርምጃ ምን መሆን እንዳለበት ስላልተስማሙ ጩኸትና ጫጫታቸው አልተተገበረም።

የትንተናውን ድምዳሜ በንጉሠ ነገሥቱ ላይ በማተኮር፤ «የ፷፱ ዓመቱ ሽማግሌ በባለቤታቸው እና አራት ልጆቻቸው ሞት ብቸኛ ቢሆኑም እንኳ ከሃያ ስድስት ዓመታት በፊት በዓለም መንግሥታት ማኅበር መድረክ ላይ በመቆም ያሳዩት የጉልምስና ስሜት አሁንም አልራቃቸውም።» የ፵፭ ዓመት ዕድሜያቸውን የያዙት ልጃቸው አልጋ ወራሽ አስፋ ወሰን ግን ከአባትዬው ይልቅ የተራማጅነት አስተሳሰብ ያላቸው ቢሆኑም ባህሪያቸው ለስላሳ እና ጨፍጋጋ ነው ይልና፣ «የንጉሠ ነገሥቱ ዘውድ ሳይተላለፍ ብዙ የዘገየ እንደሆነ፤ በአሮጌው ሥርዓት ላይ ያለመው መሣሪያ ምላጭ መሳቡ የማይቀር ነው።» ሲል ዘገባውን ደምድሟል። ምከረው ምከረው እንቢ ካለ መከራ ይምከረው እንዲሉ፤ ጃንሆይም አልሰማ ብለው….

በሚቀጥለው የታሪክ አውሎ ነፋስ እስከምንገናኝ፤ የሎንዶኑ ቡልጌ ነኝ!


No comments:

Post a Comment

እርስዎስ ምን ይላሉ?