Wednesday 4 May 2011

የ፸ ዓመት ነፃነት

        ሚያዝያ ፳፯ ቀን አባቶቻችንና እናቶቻችን አርበኞች ግፈኛውን የፋሺስት ኢጣልያ ሠራዊት ድል ያደረጉበት ማስታወሻ አድርገን እናከብረዋለን። በ፳፻፫ ዓመተ ምሕረት፣ ነገ ደግሞ ርዕሰ ከተማችንን በከፊል ተረክበን፣ ሰንደቅ ዓላማችን የተውለበለበበት ሰባኛው ዓመት ማስታወሻ ስለሆነ ለየት ባለ ሁኔታ ለማክበር እንሞክራለን። ከነኛ ጀግኖች አርበኞቻችን መኸል መቸም በጊዜው ብዛት አብዛኛዎቹ ተለይተውን፣ የቀሩት ጥቂት ናቸው።

በዚህ የመታሰቢያ ጽሑፍ  ከዚህ ዕለት ጋር የተያያዙ ሦስት ዐቢይ ነጥቦችን ለማንሳት እፈልጋለሁ። እነዚህም፦

ሀ)      የዚህን ዕለት ‘የነፃነት ቀን’ ወይም ‘የድል በዓል’ መባል ትክክለነቱን፤
ለ)      ለድሉ ወይም ለነፃነቱ ላደረሱን ጥቂት፣ ተራፊ አባቶች እና እናቶች አርበኞቻችን ምን ውለታ ተደርጎላቸዋል?
ሐ)      እኛ ኢትዮጵያውያን ለ ፸ ዓመታት በጃችን ይዘነው የቆየነውን ‘ነፃነት’ እንደምን ተጠቅመንበታል?

ሀ)     የድል በዓል ሚያዝያ ፳፯ ወይስ ኅዳር ፲፱ ?

ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በምዕራብ ኢትዮጵያ ኡም ኢድላ (ኦሜድላ) ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከተከሉበት ጥር ፲፪ ቀን ፲፱፻፴፫ ዓ/ም ጀምሮ በጎጃም እንጃባራ፤ ቡርዬ፣ ደምበጫ፣ ደብረ ማርቆስ አድርገው በእንጦጦ በር አዲስ አበባ እስከገቡ ድረስ፤ በአርበኞቻችን ኃይልና በእንግሊዝ ጦር ኃይሎች እርዳታ የጣሊያንን ኃይል እየደመሰሱ በሚጓዙበት ወቅት በምሥራቅና በደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ የነበሩት አርበኞችና የእንግሊዝ ሠራዊት እንደዚሁ በጅጅጋ፣ ሐረር፣ ድሬዳዋ፣ አዋሽ፣ ናዝሬትና ሞጆ አድርገው፣ ከፊታቸው የሚያጋጥማቸውን የፋሺስት ኃይል እየደመሰሱ ወደርዕሰ ከተማዋ ይገሰግሱ ነበር።

ታዲያ ከነኚህ ሁለት ግንባሮች ቀድሞ ከተማዋን መጋቢት ፳፰ ቀን ፲፱፻፴፫ ዓ.ም ከጣሊያኖች የተረከበው እንግሊዛዊው ጄነራል ዌዘሮል ነበር።[1]  ንጉሠ ነገሥቱ እና ተከታዮቻቸው ከአንድ ወር በኋላ፣ ሚያዝያ ፳፯ ቀን አዲስ አበባን ተረከቡ።

በዚህ ጊዜ በደቡብ-ምዕራብ ኢትዮጵያ፤ ጅማ እስከ ግንቦት ፳፱ ድረስ በሰሜን ኢትዮጵያ ደግሞ ጎንደር እስከ ኅዳር ፲፱ ቀን ፲፱፻፴፬ ዓመተ ምሕረት ድረስ በጣሊያኖች እጅ ነበሩ።

እንግዲህ እንደምንገነዘበው 'ድል ቀን' ሚያዝያ  ፳፯ ቀን የሆነበት ዋናው እና ብቸኛው ምክንያት ንጉሠ ነገሥቱ አዲስ አበባ የገቡበት ዕለት ስለሆነ እንጂ መላዋ አገር ከፋሺስት ቀንበር የተላቀቀችበት ሆኖ አይደለም። ትክክለኛ ሆኖ መከበር ያለበት የጣሊያን ሠራዊት ለመጨረሻ እና ለዘለዓለም ሰንደቅ ዓላማውን ከኢትዮጵያ ምድር ያወረደበት እና ያለምንም ጥርጣሬ መሸነፉን አምኖ ጎንደር ላይ እጁን የሰጠበት ዕለት ኅዳር ፲፱ ቀን  ፲፱፻፴፬ ዓመተ ምሕረት መሆን ይገባዋል። 

ያለበለዚያማ በዚህ በመጨረሻው ግንባር ተሰማርተው ሲጋደሉ የቆዩትን አባቶቻችንን መስዋእትነት መዘንጋት፣ መደምሰስ ይሆንብናል። የእነ  ደጃዝማች ኪዳኔ ወልደመድኅን ደጃዝማች ሀብተ ሥላሴ በላይነህ ደጃዝማች በዛብህ በለው፣ ደጃዝማች ካሣ መሸሻ፣  ደጃዝማች ከበደ ወንድማገኝ፣ ፊታውራሪ ከበደ ካሣ፣ እና የሌሎችም ብዙ አባቶቻችን አፅም ይፋረደናል። ሌሎቹ አርበኞች፣ ስደተኞች ከአምሥት ዓመታት በኋላ ወደየዘመድ አዝማዳቸው፣ ወደየትውልድ አገራቸው ሲመለሱ፣ እነኚህ ግን ትጥቃቸውን ሳያወልቁ፣ ቅማል የወረረውን ጎፈሬያቸውን ሳይቆረጡ ወደሰሜን ዘመቻ ተሰማሩ። የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ከሚያዝያ ፴፫ እስከ ኅዳር ፴፬ ያሉትን ሰባት ወራት የደመሰሰባቸው ይበቃል።

'ድል በዓል' ዕለት መከበር ያለበት ሰንደቅ ዓላማ የተተከለበት ዕለት ከሆነ፣ እንግዲያውስ ኡም ኢድላ (ኦሜድላ) ላይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የትተከለበት ጥር ፲፪  ቀን ይከበራ! አይ፣ አዲስ አበባ ከፋሺስት ኢጣልያ እጅ የተፈለቀቀችበት ዕለት መሆን አለበት የተባለ እንደሆነ ደግሞ፣ እንግሊዛዊው ማጆር ጄኔራል ዌዘሮል ዋና ከተማዋን የተረከበበት መጋቢት ፳፰  ቀን ይሁና! የዚህኛው ቀን ችግር ግን ዌዘሮል ያውለበለበው የብሪታኒያን ሰንደቅ ዓላማ መሆኑ ነው።

እነዚህ ሁሉ የተለያዩ ቀናት እንድ ሚያዝያ ፳፯  'ድል' የሚለውን ቃል ሙሉ በሙሉ አርኪ በሆነ መልድ አያስተጋቡም። ኅዳር ፲፱ ቀን ግን የፋሺስትን ኃይል ከመላዋ ኢትዮጵያ ክልል አሽቀንጥረን አስውጥተን፣ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቅ ዓላማችን በመላው አገራችን የተውለበለበበት፣ ራሳችንን በራሳችን የማስተዳደር መብታችን የተከብርበት ዕለት [የሰባት ዓመቱን የእንግሊዞችን ጣልቃ ገብነት ወደጎን ትተነው] በመሆኑ እውነተኛው "የድል ዕለት" ያደርገዋል።
ለ)     አርበኞች አባቶቻችን እና እናቶቻችን ስለስድስት ዓመት ተጋድሏቸው ምን ውለታ አገኙ?
        
ጠላት ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ አብዛኛዎቹ ተከላካይ ወገኖቻችን ዕድሜያቸው ከአሥራ ስምንት ዓመት እስከ ሃያ አንድ ዓመት ብቻ የነበሩ ወጣቶች ናቸው። አብዛኞቹ፣ የጦር መሪዎቻቸው፣ መኳንንቱ፣ መሣፍንቱ  ከነአካቴውም ንጉሠ ነገሥቱም ሳይቀሩ አጋፍጠዋቸው አገር ጥለው እግሬ አውጪኝ ሲበሩ፤ ሞትም እንኳ ቢመጣ ለጠላት አንገዛም ብለውት፤። ረሀብ ሲቆላቸው፣ ቅማል ደማቸውን ሲመጠምጥ፣ የመርዙ ጋዝ፣ የቦምባርዱ፣ የጥይቱ የተቅማጡ፣ እረ ምኑ-ቅጡ 

መንፈሰ ጠንካራ፣ አልበገር ባይ ባይሆኑማ ኖሮ እነሙሴ ቀስተኛን የመሰሉ ሰላዮች መኻላቸው እየገቡ፤ ‘ንጉሡ ጥሏት ለሄደው አገር ስለምን ትጉላላላችሁ? ኑ ግቡ፤ የኢጣልያ መንግሥት ይሾማችኋል፣ ይሸልማችኋል’ እያሉ አገራቸውን ሊያስከዷችእው ሞክረው አልነበረም?  ያ ትውልድ ግን ‘ለጥቅሜ ብዬ ውድ አገሬን፣ አለኝታዬን፣ መኩሪያዬን አሳልፌ አልሰጥም። ለነፃነቴ ብሞትም ክብሬ የዘለዓለም ነው።’ በሚል ጥብቅ እምነታቸው ተሰቃዩ፣ አጥንታቸውን በየሸንተረሩ ከሰከሱ፣ ደማቸው በየ ሸለቆው ፈሰሰ፤ እንደጥብቅነታቸው እንደ እምነታቸው ታዲያ ያንን መራራ ጠላት ከወሰን ድንበራቸው ለማባረር በቁ።

የዓፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት በነኚህ ኢትዮጵያውያን ደም ተመልሶ ሥልጣኑን ሲጨብጥ፣ እንደባለውለታ መንከባከብ፣ መሾም መሸለም፣ ማክበር ማስከበር ሲኖርበት፤ ከነአካቴው ውለታ ተቀባይነታቸው ቀርቶ እንደውለት መላሽ የትም ወድቀው እንዲቀሩ፣ ስማቸው እንዲጠፋ፣ ሥራ ስጡን ብለው በ’ደጅ ጥናት’ እንዲማቅቁ የሚጥር ሥርዓት ሆነባቸው። በስማቸው የተሠራውን የአራት ኪሎውን ሕንፃ እንኳን ለማስፈቀድ የነበረባቸውን እንግልት ይሄ ጸሐፊ በቅርብ ታዝቦታል። የኢትዮጵያ መንግሥት እነኚህን ባለውለታዎች፣ ሲሆን እስከ ጡረታ ዕድሜያቸው አገራቸውን እንዲያገለግሉ፤ ቢያንስ እንኳ ለዚያ ውለታቸው ክብራቸውን ጠብቆ በእንክብካቤ መጦር ሲገባው ነፍስ አውጪኝ የሸሹትን ስደተኞች ሲሾም ሲሸልም፣ እነኚህን ግን ከኢትዮጵያ ማዕድ ከልክሏቸው ኖረ።

በደርግ ዘመናት ደግሞ ጭርሱንም በትምህርት ቤት እንኳ ከአብዮቱ በፊት የነበረውን ታሪክ ወጣቱ እንዳይማረው ተከለከለ። ትንሽ መተዳደሪያ መሬት የነበራቸው ተነጠቁ። ወገን ለሌላቸው አርበኞች መርጃ ተብሎ የተሠራው የአራት ኪሎ ሕንፃቸው ሳይቀር ተወረሰ። መጦር የነበረባቸው የነፃነታችን ባለቤቶች እየለመኑ መኖር ግዴታ ሆነባቸው።[2]

ባለፉት ሃያ ዓመታትማ ብሶበታል። አንደኛ ቁጥራቸውም እያደር እየመነመነ ነው። ከሁሉም በላይ ግን የአሁኑም መንግሥት የነኚህን ባልውለታዎች ታሪክ ማንቋሸሽና ማጣጠል እንጂ ክብር መስጠትን የማያውቅ፤ ዘመኑ እንኳን ለሰማንያ፣ ዘጠና ዓመት አዛውንት ቀርቶ እየሠራ የሚበላው ወጣት ትውልድ ሊቋቋመው የማይችለው፣ ሽማግሌ ማክበር፣ መርዳት የነበረው የባህላችን ምሰሶ በሥልጣኔ፣ እድገትና እርምጃ ስም ሌት ተቀን በመጥረቢያ ስለት እንደሚከተከት ግንድ ሊወድቅ ምንም ያልቀረው ሆኗል። ታዲያ ለእነኚህ ባለውለታችን አዛውንት ምን ተስፋ አላቸው?

ሐ) የ፸ ዓመት ነፃነታችንን ምን ሠርተንበታል?
ከ፴፫ቱ ድል ጋር አብረው የገቡት እንግሊዞች ምሥጢራዊ ዓላማቸው ፋሺስት ኢጣልያን በቅኝ ገዥነት መተካት ኖሮ በስም የንግሊዝ ቅኝ ግዛት አንባል እንጂ በተግባር ግን እንደመዥገር ተጣብቀውብን ደማችንን ሲመጡ የኖሩባቸውን ሰባት ዓመታት ትተን በቀሩት ፷፫ ዓመታት ላይ ብናተኵር፤ ይሄንን ጥያቄ እንዴት ነው የምንመልሰው?
የዘውዱ ሥርዓት ከስደት እንደተመለሰ ሥልጣኑን በማጠናከር፣ ፈላጭ፣ ቆራጭ ሆኖ ፣የአምሥቱን ዓመታት ፍዳ ረስቶ/አስረስቶ ለሃያ ዓመታት ከገዛ በኋላ፤ የወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ቢደርግበትም የጭቆና ባሕሪውን አባባሰው እንጂ ለሕዝቡ ንቃት እና መሻሻል ምንም ይሄ ነው የሚባል ለውጥ አላመጣለትም። የዚያ የታኅሣሡ ሙከራ ግን በሕዝቡ ልቦና ላይ የጫረው የለውጥ እሳት ከ ፲፫ ዓመታት በኋላ ተፋፍሞ አሽቀንጥሮ ጣለው።
ተከታዩ አብዮት፣ ሕዝቡ እንደተመኘው፣ እንዳለመው የዴሞክራሲያ ውጤትን ሳይሆን የተጎናጸፈው፤ ጭርሹንም ከመቶ ዓመት በላይ ወደኋላ የገፈተረው ሥርዓት ሆነ። የሕዝብን ሉዐላዊነት፣ የሕግን የበላይነት፣ እኩልነትን፣ በኢትዮጵያዊነት ታሪክ ላይ የተመሠረተ ሥልጣኔን የሚሻ ሕዝብ ከነአካቴው ከጨካኞች የባሰ ጨካኝ፤ ከዲያብሎስ የበለጠ አረመኔ የአምባ ገነን ተገዢ አደረገው። በዲሞክራሲያ ፋንታ ለስድብ፣ ለውርደት፣ ለሞት ተዳረገ። የኢትዮጵያዊነት ወኔውን ተሰለበ።
ደሞ ያንን አሰቃቂ እና ፍሬ ቢስ ዘመን ከ፲፯ ዓመታት በኋላ ተገላገልኩ ሲል፤ ለባሰ ሥርዓት ከተዳረገ እነሆ ሀያ ዓመቱ ሆነ። ተለያይቶ የማያቀውን አንድ ሕዝብ በዘር አከፋፍሎ፣ አገርን በጉልበት ለመንጠቅ ለብዙ መቶ ዓመታት ሞክረው ያቃታቸውን ባዕዳውያንን በይፋ እየቆረሰ ‘ኑ ውሰዱልኝ’የሚል፣ የበላዩ ሊሆን የሚገባውን ሰፊውን የኢትዮጵያ ሕዝብ መብቱን ገፎ የሚገዛ የጉድ ጉድ፣ መዓት አናታችን ላይ ተመቻችቶ ቁጭ እንዲል ፈቀድንለት።
ዳግማዊ ምኒልክ የዛሬ መቶ ዓመት፣ ዕለተ ሞታቸው ሲቃረብ፤ ሕዝባቸውን እንዲህ ብለው መክረው ነበር፦

«እናንተ አንድ ልብ ከሆናችሁ በምቀኝነት እርስ በርሳችሁ ተዋግታችሁ ካላለቃችሁ በቀር ኢትዮጵያን አገራችንን ለሌላ ለባዕድ አትሰጧትም፤ ክፉም ነገር አገራችንን አያገኛትም። ነፋስ እንዳይገባባችሁ አገራችሁን በያላችሁበት በርትታችሁ ጠብቁ፤ ወንድሜ ወንድሜ እየተባባላችሁ ተደጋገፉ፤ የኢትዮጵያን ጠላት ተጋግዛችሁ ተድንበር መልሱ። የኢትዮጵያ ጠላት ባንዱ ወገን ትቶ ባንድ ወገን ቢሄድና ድንበር ቢገፋ፤ በኔ ወገን ታልመጣ ምን ቸገረኝ ብላችሁ ዝም አትበሉ፤ ያ ጠላት በመጣበት በኩል ኁላችሁም ሄዳችሁ አንድነት ተጋግዛችሁ ጠላታችሁን መልሱ እስከ እየቤታችሁ እስኪመጣ ዝም ብላችሁ አትቆዩ»
 ይሄ ቃላቸው በታሪክ አውሎ ነፋስ ተምዠግዥጎ እኛም ዦሮ ሲገባ፣ መልእክቱ ለዘመናቸው ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለኛም፤ ለመጪውም ትውልድ እንደሆነ እንገነዘባለን። በዛሬው የመከፋፈል፣ የዘረኛነት እና መንፈሰ ደካማ ሥርዓት ግን ምኒልክ ከነአካቴው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት ተብለው ተወነጀሉ።
በበኩሌ ያንን ሁሉ መሥዋዕትነት፣ ያንን ሁሉ ተጋድሎ አባክነነዋል እላለሁ እንጂ የ፸ ዓመት ነፃነታችንን በአግባቡ ተጠቅመንበትም ለወደፊቱም ትውልድ ቋሚ ነገር ለማሸጋገር በቅተናል አልልም።

የሎንዶኑ ቡልጌ ነኝ
[ሚያዝያ ፳፮ ቀን ፳፻፫ ዓ/ም]





[1] The Abyssinian Campaigns, Issued for the War Office by the Ministry of Information (1942)

2 comments:

  1. ቡልጌው፣
    በጣም የሚያረካ ትንተና ነው። እውነትህ/ሽን ነው እንደ ድል በዓልን የመሰለ ዐቢይ ቀን ማክበር ያለብን ትክክለኛውን ታሪካዊ መሠረት ተከትለን እንጂ መሪዎቻችን ለራሳቸው ዝና ሞገስ ብለው የፈጠሩትን መሆን የለበትም።

    ስለአባቶችና እናቶች አርበኞች እንግልትና የኑሮ ሁኔታ ያሠፈርከው ልቤን በጣም ነው የነካው። ያመለከትከውን ድረ-ገጽ ተመለከትኩት። እዚያ ላይ እርዳታ ለማድረግ ለሚፈልግ አድራሻ አሥፍረዋል እና በዚህ በኩል ብንረዳቸው ጥሩ ይመስለኛል።

    ይመኩ ታምራት

    ReplyDelete
  2. G'evening Bulgew,

    Very interesting and mind-opening article, you wrote. I am impressed. I always thought Miazia 27th was the actual date. I really feel you hit the nail on the head when you were describing the current situation of Ethiopia. I am also certain that your thoughts are shared by many Ethiopians. It pains me when I hear piece of my country is being sold to outsiders. It is outrageous. Keep up the good work.

    You reminded this: I have almost forgotten our numerals - so I have to start sereaching for them.

    Many thanks for sharing your knowledge.

    Yefate

    ReplyDelete

እርስዎስ ምን ይላሉ?