Monday 2 May 2011

የጃንሆይ ወርቅ


በየካቲት ወር የፈነዳው ሥር-ሰደድ ነውጥ የጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተ ወልድን መንግሥት ፈንቅሎ ከጣለ አራተኛ ወሩን ይዟል። የልጅ እንዳልካቸው መኮንን ካቢኔ አገሪቱን የሚያስተዳድረው  መቸም ያው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስም ቢሆንም፣ የሥልጣን ገመዱን የሚያሥር የሚፈታው፤ የሚያጠብቅ የሚያላላው ግን ወታደራዊው ደርግ ነው። አብዮቱ ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ በመላ ኢትዮጵያ ተፋፍሟል።

የአብዮቱን መርሐ-ግብር ተከትሎ የልጅ እንዳልካቸው መንግሥት አዲስ ሕገ መንግሥት የሚያዘጋጅ ሸንጎ እና የቀድሞዎቹንም ሆነ የወቅቱን ባለ ሥልጣናት፤ መኳንንት እና የዘውድ ቤተሰቦችን የአስተዳደር  ወንጀል እና ሙስና የሚያጠናም ሸንጎ ተቋቁሞ በየዕለቱ ብዙዎቹ ለወህኒ እየተዳረጉ ነው። የልጅ እንዳልካቸውም መንግሥት በተራው ሊወድቅ አንድ ወር ያህል ነው የቀረው።

ታዲያ በወቅቱ በኢትዮጵያ የብሪታኒያ አምባሳዶር የነበረው ዊሊ ሞሪስ (Sir Willie Morris, K.C.M.G.)  የየዕለቱን ዜና፤ ከእንደነ ኮሞዶር እስክንድር ደስታ፣ ልዑል ራስ አሥራተ ካሣ እና ደጃዝማች ዘውዴ ገብረ ሥላሴ የሚያገኘውን መረጃዎች፤ ወ.ዘ.ተ. ከራሱ ምርመራና አስተያየት ጋር እያጣመረ ወደሀገሩ የላካቸው እጅግ ብዙ ሰነዶች በብሪታኒያ ብሔራዊ መዝገብ ቤት (Public Records Office) ይገኛሉ።

ከእነኚህ ዶሴዎች መሀል ፤ ‘የኢትዮጵያ ሕዝብ በዘውዱ ሥርዓት ባለሥልጣናትና ንጉሣውያን ቤተሰቦች ተበዝብዟል’ በሚባልበትና  ‘በወሎ ሕዝብ የረሀብ ስቃይ’ ዓለም ባዘነበት በዚያ ቀውጢ ወቅት፤ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ልዩ በረራ ተጭኖ በድብቅ ወደ ሎንዶን ስለተላከ ወርቅ የተጻፉ ትንታኔዎችና ማስታወሻዎች ናቸው።

አምባሳዶር ዊሊ ሞሪስ ፣ ሰኔ ፳፬ ቀን ፲፱፻፷፮ ዓ/ም ወደሎንዶን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በላከው ቴሌግራም (አ/አ ቴሌ 304) ላይ፦

«የኢትዮጵያ አየር መንግድ ድርጅት ውስጥ ካለው ምንጫችን እንደተረዳነው ሰኞ ሰኔ ፲፯ ቀን ፲፱፻፷፮ ዓ/ም  በቤተ መንግሥቱ የግል ኮንትራት፤  አራት መቶ ስልሳ ሰባት  ሣጥኖች ጭኖ ነዳጅ ለመሙላት አቴና ላይ ካረፈ በኋላ ወደሎንዶን ተጉዟል።» ይልና፣ «ጭነቱ በሙሉ ወርቅ እንደሆነ ገምተናል። የዚህን ምንጭ እውነተኛነት ማወቅ ስለምንፈልግ፤ እውን ልዩ በረራ በተባለው ቀን ሎንዶን ገብቶ እንደሆነ፤  ገብቶም ከሆነ በአስተያየታችን የብሔራዊ ባንኩ የተለምዶ ተልዕኮ ስለማይመስለን የጭነቱን ዓይነት እና ተቀባዩ ማን እንደሆነ እንድታረጋግጡ እናሳስባለን።»

ይሄ የአዲስ አበባው ቴሌግራም እንደደረሰ፣ በብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የምሥራቅ አፍሪቃ ክፍል ኃላፊዎች ጉዳዩ እንዲጣራ ያዛሉ። ውጤቱም ከብሪታኒያ የንግድ ሚኒስቴር እና ከጉምሩክ የመነጨ መረጃ ሲሆን የምሥራቅ አፍሪቃ ክፍሉ ፦

፩ኛ) በሰኔ ፲፮  እና ፲፯ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሁለት ልዩ በረራዎችን ፈጽሟል።
ሀ) አንደኛው በዠኔቭ በኩል አድርጎ ሎንዶን ሰኔ ፲፮ ቀን ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ግድም የገባው ሲሆን
ለ) ሁለተኛው ደግሞ ‘የጭነት ብቻ’ በረራ ሲሆን በአቴና በኩል አድርጎ ሎንዶን በማግሥቱ ከጧቱ አንድ  ሰዓት ከሩብ ላይ አርፏል።
፪ኛ) ሁለተኛው በረራ የያዘው ጭነት “ውድ ዕቃ” የሚል መግለጫ የያዘ በመሆኑ በጉምሩክ አልተከፈተምም፣ ቀረጥም ያስከፍላል ተብሎ አልተገመተም። ጭነቱ አምባሳደሩ እንዳለው አራት መቶ ስልሳ ሰባት  ሣጥኖች ብቻ ሳይሆን፣ ፮፻፴፪ ሣጥኖችን ያጠቃለለ ሲሆን ጠቅላላ ሚዛኑ ፲፬  ፯መቶ ፹፱ ኪሎ ነው። ጭነቱ በሙሉ ይሄንኑ ሊያጓጉዝ ለተኮናተረው ኩባንያ ተላልፏል።

በጉምሩክ በኩል ደግሞ የቀረበው ጥቆማ ፦ በአየር ዠበብ ማረፊያው የጉምሩክ ምክትል ሀላፊ፣ በድብቅ ይሄን ጉዳይ ከመረመረ በኋላ፤ የገቡት ሣጥኖች ፮፻፴፪  እንደሆኑና በውስጣቸው ዋጋው በ፳፮ ሚሊዮን ፮፻፴፭ ሺ ፫፻፸፰  የእንግሊዝ ፓውንድ (£26,635,378.25)የተገመተ ያልተጣራ ወርቅ እንደሆነ እና በጠቅላላው ሚዛኑ ፲፬ ሺ ፻፴፬ ኪሎ ከ ፭፻፸፮ ግራም መሆኑን፣  ይሄውም የወርቅ ጭነት የተላከው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ስም ወደእንግሊዝ ብሔራዊ ባንክ እንዲገባ ነው። 

በንግድ ሚኒስቴር [ግምት] ሚዛን እና በጉምሩኩ ሚዛን መኻል የክብደት ቅራኔ መነሳቱን አንባቢ ልብ ይሏል። የጎደለው ፮፻፶፬ ኪሎ ወርቅ ምን ሆኖ ይሆን? የመጀመሪያው ዘገባ ተሳስቶ ነው ወይስ ያልተገለጸ የ ፩ ሚሊዮን ፪፻፴፫ ሺ ፓውንድ (በእንግሊዞቹ ተመን!) (ቀረጥ?/ዝርፊያ?) ተቀንሶ ነው?

የንግድ ሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ “ጭነቱ ‘ውድ ዕቃ’ የሚል መግለጫ በመያዙ ብቻ ጉምሩክ ሳይከፍት/ሳይመረምር፤ የቀረጥም ተመን ሳያሰላ እንዲያው በደፈናው ለአጓጓዡ ወኪል አስረከበ ሲለን ልናምነው እንችላለን? ‘ውድ ዕቃ’ ከማለት ‘የዲፕሎማቲክ ጭነት’ የሚል ነበር ቢለን እንኳ ያለመፈተሹ ባላስገረመንም ነበር። ዞሮ ዞሮ ያልከፈቱትን ጭነት ምንነት ከነ ሚዛኑ እና ከነግምት ዋጋው ሊያውቁ የቻሉበትን ዘዴ አንባቢ  የራሱን ግምትና ትርጉም ሊሰጠው ይችላል።

ሌላው ደግሞ በዚህ ዶሴ ውስጥ በዠኔቭ በኩል ሎንዶን ገባ የተባለው የአየር መንገዱ ያልታሰበ በረራ ጉዳይ መካተቱ ትርጉሙ ምንድነው? ዠኔቭም የአየር መንገዱ ቋሚ መሥመር ስላልነበረ፣ ለምንድነው ወደዠኔቭስ የተላከው? ሌላ የ“ውድ ዕቃ” ጭነት ወደዠኔቭም ትልኮ ይሆን?

ሆኖም  የብሪታኒያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከአዲስ አበባ የተላለፈላቸውን መልዕክት ተከታትለናል ብለው በጊዜው የመሥሪያ ቤቱ ሚኒስትር በነበሩት፤ ጄምስ ካላሃን (በኋላ የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር) ስም ወደ አዲስ አበባው  አምባሳዶር  ይሄንኑ ‘መረጃ’ የተመረኮዘ መልእክት (የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቴሌ 268)[i] ሲያስተላልፉ፣ የምሥራቅ አፍሪቃ ክፍል ባልደረባ፤ ሪቻርድ ጎዝኒ (Sir Richard Hugh Turton Gozney) ግን ምናልባት ወደፊት ለሚነሳ ጥያቄ በሚል ሰኔ ፳፰ ቀን ፲፱፻፷፮ ዓ/ም በጻፈው የመዝገብ ማስታወሻ ላይ:-

«… በሕግ ድንጋጌው መሠረት በብሪታኒያ ክልል ውስጥ ያጓጓዙበትን የሰነድ ቅርጽ ለሁለት ዓመት ማስቀመጥ ግዴታቸው ስለሆነ…» ይልና የአጓጓዡን አድራሻ ከዶሴው ጋር አያይዞ አስቀምጦታል። ይሄ ጉዳይ በዶሴው ላይ እንደገና የሚነሳው በአዲስ አበባው ኤምባሲ የፖለቲካ  ክፍል ኃላፊ, ኢያን መሪ (Iain Murray)  ነሐሴ ፳፰ ቀን ለምሥራቅ አፍሪቃ ክፍል ባስተላለፈውበምስጢር የሚያዝ ሰነድ” ላይ ነው።

በዚህ ሰነድ ላይ፣ በጊዜው ለእንግሊዞቹ [ለአሜሪካኖቹም] በምስጢር ቃል ያቀብላቸው ከነበረው አቶ ሳሙኤል ዓለማየሁ [በአፍሪቃ አንድነት ድርጅት የቅኝ ግዛቶች ጉዳይ ክፍል የኢትዮጵያ ዋና ተወካይ] ጋር የተደረገውን ውይይት በመጥቀስ የቀረበው የኢያን መሪ ዘገባ፦
<<ሳሙኤል የዚያን ወደ እንግሊዝ ብሔራዊ ባንክ የተላከውን የወርቅ ጉዳይ ዛሬም አነሳብኝ። በአብዮተኞች መኻል የተፋፋመ ውይይት እየተካሄደ መሆኑንና የብሪታኒያ መንግሥት ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አጋር ነው እየተባለ ነው። ወርቁን በድብቅ ከአገር ያሸሹት መሆኑን እያወቁ አደራ መቀበላቸው፤  በተለይም በቅርቡ ከ’ቶማስ ደላሩ ኩባንያ’ አዲስ የታተመ የኢትዮጵያ ገንዘብ መላኩ ንጉሠ ነገሥቱ ተቃራኒዎቻቸውን እንዲገዙበት ሆን ብሎ የተላከ ነው።>> እያሉ እንደሆነ የሚወያዩት ነገረኝ ሲል ጽፏል።[ii]

ታዲያ ወዲያው ንጉሠ ነገሥቱ ከሥልጣን ሊወርዱ አንድ ቀን ሲቀር፣ ከአዲስ አበባ በተላከ ደብዳቤ፣ የዚህ የወርቅ ጉዳይ በመላው አዲስ አበባ ይፋ መሆኑንና ብዙ ውዝግብ እያስከተለ መሆኑን ይገልጽና የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሁንም ጠለቅ አድርጎ ጉዳዩን እንዲመረምር፣ በተለይም «በእንግሊዝ ብሔራዊ ባንክ፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ስም የሒሣብ ደብተር አንድ ብቻ ነው? ወይስ ሌሎችም አሉ? ይሄ ወርቅ የገባበት የሒሣብ ደብተርስ በማን ቁጥጥር ስር ነው?» የሚሉትን ጥያቄዎች እንዲያጣሩለትና እንዲያስታውቁት ያሳስባል። ቀጥሎም በአዲስ ተገኘ በሚለው መረጃ መሠረት፣ ወርቁ በመጋቢት ወር ላይ በጊዜው የገንዘብ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ማሞ ታደሰ ‘ባልሆኑ ሰዎች እጅ እንዳይገባ' [ዘውዳዊ ቤተሰቦች ማልታቸው ይሆን?]በሚል ከገንዘብ ሚኒስቴር ካዝና አውጥተው ወደብሔራዊ ባንክ አዛወሩት። በሰኔ ወር በድብቅ ወደእንግሊዝ አገር ሲጫን ይዘውት የሄዱት ምክትል ሚኒስትሩ በጅሮንድ ገዛኸኝ ገብረ-ማርያም እንደሆኑ ይነግረናል።

የዚህ ደብዳቤ ጥያቄዎች የምሥራቅ አፍሪቃ ክፍል ኃላፊዎችን እንደገና አነቃቅቷቸው፣ ለእንግሊዝ ብሔራዊ ባንክ ጥያቄያቸውን አቀረቡ። የባንኩ ተወካይ መስከረም ፲፬ ቀን ፲፱፻፷፯ ዓ/ም በተጻፈ ደብዳቤ መልስ ሲሰጥ፣ እንደዚህ ያለውን በሁለት ብሔራዊ ባንኮች መካከል ያለ የሥራ ይዘት ምሥጢራዊ ጉዳይ መሆኑን፤ አሁንም ስለዚህ ምስጢራዊ ጉዳይ ለመጻፍ የተገደደው በአዲስ አበባ የብሪታኒያ ተልዕኮ አለአግባብ የሚሰነዘሩበትን ጥያቄዎች ለመመከት ይረዳዋል በሚል መሆኑን ካስረገጠ በኋላ የተላከው ያልተጣራ ወርቅ በተለመደ ሥርዓት መሆኑን እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አልፎ አልፎ እንደዚሁ ያልተጣራ ወርቅ እየላከላቸው እነሱ በወኪልነት ወርቁን አጣርተው በጡብ መልክ መልሰው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሒሣብ ደብተር ውስጥ ማስገባት የተለመደ ሥራቸው እንደሆነ በማስረዳት ደምድሞታል።

እንግዲህ የዚህን ወርቅ ጉዳይ በተመለከተ፤ ጸሓፊው ከብሪታኒያ መዝገብ ቤት ያገኘው ይሄው ነው። በዚሁ መዝገብ ቤት ከአሁን በፊትም በጣሊያን ወረራ ጊዜ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ወደስደት ሲጓዙ ጠገራ ብር እና ብዙ ወርቅ ጭነው ስለመሄዳቸው የተጻፉ ሰነዶች አሉ። ዳሩ ግን በመኻላቸው ሰላሳ ስምንት ዓመታት ያለፉ ቢሆንም፤ በተመሳሳይነታቸው እና ለንብረቱ ባለቤት የኢትዮጵያ ሕዝብ ምንም አይነት እርካታ የሚሰጥ እልባት ላይ ያልደረሱ ጉዳዮች ስለሆኑ መቸም ይሄን በሚያነቡ ኢትዮጵያውያን አዕምሮ ውስጥ እጅግ ብዙ ጥያቄዎችን እንደሚጭር አልጠራጠርም። ወርቁ ተመልሶ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኩል ለኢትዮጵያ ጥቅም ውሎ ይሆን? ወይስ እንዲያው ተደባብሶ ቀልጦ የቀረ ጉዳይ ይሆን?

የእንግሊዝ ብሔራዊ ባንክስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ልዩ ልዩ የሒሣብ ደብተሮች አሉት ወይ? ይሄ ወርቅ የገባበትንስ ደብተር የሚቆጣጠረው (ሒሣብ የማስገባት የማስወጣት ሥልጣን) ማነው? በሚል የቀረቡለትን ጥያቄዎች በዝምታ ማለፉ ለምን ይሆን? 
ከዚህ ታሪክስ አንጻር የአሁኒቱ ኢትዮጵያ ምን ተምራበታለች? የሕዝብን ንብረት በስሙ ሲንቀሳቀስ ሕጋዊ እና ግልጽ ለመሆኑ ዋስትናው ምንድነው? ወይስ 'ይሄ ያለፈ፣ ያከተመ ጉዳይ አይመለከተንም' ተብሎ ይታለፋል? ነጮቹ ከዚህ እንደምናየው የሚመለከታቸውንም ሆነ በቀጥታ የማይመለከታቸውንም ቢሆን በጥንቃቄ  በማስቀመጥ የአስተዳደራቸውን ግልጽነት መተማመኛ ዋስትና፤ የዜጎቻቸው የማወቅ መብት  ከመሆኑም በተረፈ ለታሪክ ትምህርትም ሆነ ለማንነታቸው ዋና ምንጭ የሆነ  መዝገብ ቤት አላቸው።

መቸም አንባቢያን፣ ሌላ መረጃም ሆነ ወይም ለተነሱትም/ሊነሱም ለሚችሉ ጥያቄዎች አስተያየት ካለ እንደሚያካፍሉን ተስፋ አደርጋለሁ።

በሌላ ‘የታሪክ አውሎ ነፋስ’ ዓምድ እስከምንገናኝ፤ የሎንዶኑ ቡልጌ ነኝ ሰላም ቆዩ!


ዋቢ ምንጭ፡ P.R.O., FO 31/1661; FO 31/1668



[i] F C O telegram to Addis Ababa #268; 3 July, 1974
[ii] Murray, Iain [AA] to Rosalind MacKechnie [FCO EAD] dated 3rd September, 1974




No comments:

Post a Comment

እርስዎስ ምን ይላሉ?