Monday 21 January 2013

ወይዘሮ ዘውዲቱ፤ ራስ ጉግሳ ወሌ እና ቀብራራው አርምብራስተር!



ንደው እመ-ብርሃንን ወገኖቼ፤ የነጮች ጥጋብ ሁሌ እንደገረመኝ ነው!

እውነት ነው በአሥራ ዘጠነኛው እና በከፊልም ቢሆን በሀያኛው መቶ ክፍለ ዘመን፤ በተለይም እንግሊዞቹ እና ፈረንሳይቹ ጉልበተኛ ፈላጭ ቆራጭ ስለነበሩ የንቀታችውን መጠን ግፋ ቢል፤ በአዕምሮ ሚዛን ልንረዳላቸው እንችል ይሆናል። ያውም እኛ ኢትዮጵያውያን እራሳችንን ከሌሎቹ ገለል አድርገን የነጮቹን አስተሳሰብ የተገነዝብልናቸው እንደሆነ ነው።
ወደዋናው ጉዳይ ከመመለሴ በፊት አንድ የሰማሁትን ላካፍላችሁ።  በሃያኛው መቶ ክፍለ-ዘመን አገር ለመጎብኘት (መጎብኘት ሲባል መሰለል ብለው ያንብቡ!!!!) የገባ እንግሊዛዊ ወደአገሩ ለመመለስ በባቡር ከአዲስ አበባ ወደ ጂቡቲ እያመራ ነው።  እንግሊዛዊው እንደለመደው በአንደኛ ደረጃ ክፍል እያነጎደ ነው። የእኛ ሰዎች ግን በገዛ አገራቸው፤ የአንደኛ ደረጃውን ካርኔ ከአቅም በላይ እንዲሆን አድርገውባቸው ይሆናል፤ ብቻ ምን አደከማችሁ አንባብያን! በሦስተኛ ማዕርግ ላይ ነው ከመቶ ወደ ዘጠና ዘጠኝ ነጥብ ስድስት የሚያክሉት ተሣፋሪዎች የተጨቀጨቁት። (ነጥብ ስድስቱ ታዳጊ ወጣት መሆኑ ይሆን? ለነገሩ ግን ይሄ  ዘጠና ዘጠኝ ነጥብ ስድስት የሚሉ አመዛዘን ያኔም ነበር ማለት ነው? ወይስ አዲስነቱ ለሕዝብ ሸንጎ ቆጠራ ነው? )

 ታዲያ አሉ፤ አንድ ኢትዮጵያዊ አዛውንት ባቡሩን አዋሽ ላይ ይሳፈሩና ወደድሬዳዋ ለማምራት ገብተዋል። በካርኔያቸው መሠረት እዚያው እሦስተኛ ማዕርግ ነው የገቡት። ዳሩ ግን ሦስተኛም ሆነ ሁለተኛ ደረጃውም ላይ መቀመጫ ቢያጡ ወደአንደኛ ማዕርግ ክፍል ሲገቡ ድፍን፤ ያልበሰለ ቆጮ የሚመስል ነጫጭ ብቻ ኖሯል መኪናውን የሞላው። ታዲያ በአድዋ ጦርነት ጣሊያንን ያስቀዘኑት እኒህ አዛውንት አንዱን ጠጋ ብለው በቃሪያ ጥፊ ካጠናገሩት በኋላ፤ “ተነስ! ደሞ እኔ ቆሜ ነው አንተ በርጩማ ላይ የተጎለትከው?” ብለው አስነስተው ጉዞአቸውን ወደድሬ ቀጠሉ ይባላል።  እንግሊዛዊውም “ከኢትዮጵያ በስተቀር በየትም አገር በዘረኝነት ተጨቁኜ አላውቅም” ብሎ መስክሯል ብሎኛል ይሄን ያወጋኝ ወዳጄ።
በነገራችን ላይ አንዳንድ ወገኖቻችን በነጮቹ አባባል ሴንቸሪ የሚለውን ቃል በአጭሩ ‘ክፍለ ዘመን’ እያሉ ይጽፉታል። ‘መቶ’ የሚለው የቁጥር አመልካች ካልገባበት ግን የአምሥትም፤ የአሥርም፤ የሃያም፤ ወዘተ የዘመናት ክምችት ተብሎ ከመተርጎም ምንም የሚከለክለው ነገር የለም። የዓመታቱን የቁጥር መጠን በግዕዙ ‘ምዕት-ዓመት’ እንደምንል!  እንግዲህ የኔ አጻጻፍ ይሄን የተከተለ መሆኑ ይሰመርልኝ እና ወደዋናው ጉዳይ ልግባ።
የዛሬው የታሪክ አውሎ ነፋስ የነፈሰው ከካርቱም ጥር ቀን ፲፱፻ / ተነስቶ በዋድ መዳኒ፣ መፋዛ፣ ገዳሬፍ እና መተማ//ገላባት// አድርጎ ድንበራችንንም፤ ተገን ተራሮቻችንንም አቋርጦ ጣና ሐይቅ አካባቢ የካቲት ፳፱ ቀን ፲፱፻ /  የደረሰ ሲሆን፤ ርዕሱ የሚያተኩረው ግን ከጣና ሐይቅ ሰሜን-ምዕራብ፣ ሰሜን እና ምሥራቅ  ባለው አገር ላይ ነው።
ዕምዬ ምኒልክ ዙፋኑን እና ዘውዱን አደላድለው ከነገሡ እነሆ  አሥራ-ስምንት ዓመት አሳልፈዋል። ትረካችን የሚያተኩርበትን አገር የሚያስተዳድሩት የእቴጌ ጣይቱ ብጡል የወንድም ልጅ ራስ ጉግሳ ወሌ ናቸው። በዘመኑ ይሄ ባለታሪካችን በሰሜናዊ ኢትዮጵያ በተመላለሰበት ዘመናት  ልዩ ልዩ ግዛቶችን ያስተዳድሩ የነበሩት ትላልቅ ሰዎች እነ ራስ-ቢትወደድ መንገሻ አቲከም፤ ደጃዝማች ሥዩም ተክለ ሃይማኖት (በኋላ ልዑል ራስ ኃይሉ) ፤ ደጃዝማች ገሠሠ፤ ደጃዝማች ይመር እና ፊታውራሪ ይመር ፈንታን የመሳሰሉት መኳንንት ነበሩ።
አርምብራስተር ከአበሻ ተወላጇ ሚስቱ ጋር
ባለታሪኩ እንግሊዛዊ ሲሆን በወቅቱ በሱዳን አስተዳደር ውስጥ በተቆጣጣሪነት ተቀጥሮ፣ በደንጎላ፤ ከሰላ እና በስናር ያገለገለ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀደሰ አፈራችንን የረገጠው በ፲፰፻፺፰ ዓ/ም ኃይለ ማርያም የተባለ ኢትዮጵያዊ የሱዳንን ድንበር እየጣሰ አስቸግሮ ኖሮ፣ እሱን ለመያዝ ከተላከው ኃይል ጋር ገብቶ ነው።  ሚስቱም የዓፄ ቴዎድሮስ ሊቀመኳስ የነበረው የዮሐንስ ቤል እና የወይዘሮ ወርቅነሽ አሰፋ ይልማ የልጅ ልጅ ስትሆን ከሚሲዮናዊው ሳልሙለር እና ከወይዘሮ በለጠች ቤል (ሜሪ) የተወለድችው ስቴፋና ሳልሙለር አርምብራስተር ነበረች። ቻርልስ ሂዩበርት አርምብራስተር ከዚች ሴት ጋር በመጋባቱም ሊሆን ይችላል ወይም በሌላ ምክንያት፤ አማርኛ እና የአበሻን ባህል የሚያውቅ በመሆኑ በአስተርጓሚነትም ከመሥራቱ ባሻገር በሦስት ጥራዝ የተዘጋጀውን  “INITIA AMHARICA ፡ An introduction to spoken Amharic”  በ፲፱፻፪ ዓ/ም አሳትሟል።
ራስ ጉግሳን፤ በወቅቱ የሠላሳ ዓመት ጎልማሳ፤ በመልካቸው ትንሽ ሴታ-ሴት የሚመስሉ፤ የደም ግባታቸው ወደ ቢጫነት የሚያመዝን እና እንክራዳድማ ፀጉር ያላቸው ሰው እንደነብሩ ከአርምብራስተር ዘገባ እንረዳለን። ጠባያቸውንም ጨዋና ተስማሚ እንደሆነም ይገልጽና እንደሕጻን ያልበሰለ አመለካከትና ወላዋይነት፤ ለስላሳ አቋም እንደነበራቸውም ሳይገልጽ አላለፈም።
ሚስታቸውን ወይዘሮ ዘውዲቱን ደግሞ፤ ቢያንስ የአስር ዓመት ዕድሜ ብልጫ እንደነበራቸው ይነግረንና (ዘውዲቱ ግን በዚህ ጊዜ የሠላሳ-ሁለት ዓመት ኮረዳ እንደነበሩ ልብ ይሏል!) ባልና ሚስት የተለያየ ቤት እንዳላቸው፤ እንዲሁም ወይዘሮ ዘውዲቱ የራሳቸው መኳንንት እና ሹማምንት እንደነበራቸው ያስረዳናል። በአርምብራስተርም  ግምት ሴትዮዋ ከባላቸው የበለጡ ብልኅ፤ መንፈሰ ጠንካራ እና ሚዛናዊ እንደነበሩም ሳይገነዘብ አላለፈም። 
እንግዲህ ራስ ጉግሳ ግዛት ውስጥ እንደገባ ከደብረ ታቦር ቤታቸው ሁለት ማይል ያህል ሲቀረው መላክተኛ ልኮ ይጠባበቅ ጀመር። ታዲያ ወዲያውኑ ሃምሣ የሚሆኑ፣ ‘ከዚህም ከዚያም የተውጣጡ’ ብረት አንጋቾች በበታች ሹም እየተመሩ ወደእርሱ ሲመጡ ሲያይ አለመደሰቱን ሲገልጽን “ራስ ጉግሳ እራሳቸው መጥተው ሊቀበሉኝ ይገባ ነበር።” ይልና «የእንግዳቸውን ማንነት ሳያውቁ አልቀሩምና፤ ቢያንስ እንኳን ደብረ ታቦር መኖራቸውን በቅድሚያ የማውቀውን ደጃዝማች መሸሻን ወይም ፊታውራሪ ቡሰሪን መላክ ነበረባቸው።» በማለት ስለልበ ሙሉነቱ  ከወዲሁ ፍንጭ ይሰጠናል።
ደብረ ታቦርን ‘የተለመደ የአበሻ መንደር’ በሚል እጅግ በጣም ንቋታል። ራስ ጉግሳ ግቢ ሲገባማ ባሰበት። ለማረፊያው ተብሎ የተዘጋጀለት ቤት የአንድ ቀኛዝማች ቤት መሆኑን ሲረዳ፣ «በሦስተኛ ወይም በአራተኛ ደረጃ ላለ ተራ ሹም የሚስማማ ቤትን መቀበል [ለኔ ክብር] ተገቢ አይሆንም ነበር። ስለዚህ ወደራስ ጉግሳ “የተዘጋጀው ሥፍራ ለብሪታኒያ ሹም የማይስማማ ነው” የሚል መልዕክት ላኩና የሚያመች የድንኳን መትከያ ሥፍራ ፍለጋ ሄድኩ።» አለና፤ ቀብራሬው!
በማግስቱ፣ በቀጠሮው መሠረት ሱዳናዊ ዘበኞቹን አስከትሎ ወደራስ ጉግሳ ቤት ያመራል።  እግቢው ደጃፍ ሲደርስ ፊታውራሪ ቡሰሪ ተቀብለውት እንግባ ቢሉት፤ «ራስ ጉግሳ መጥተው ሲቀበሉኝ ደስ እያለኝ እገባለሁ» ስላላቸው ፊታውራሪው እየሮጡ ሄደው እየሮጡ ይመለሱና፤ «ራስ ወጥተው ቢቀበሉህ ደስ ይላቸው ነበር። ነገር ግን በድንገት ስለታመሙ አልቻሉም» የሚል ዜና ኖሯል ይዘው የተመለሱት። ይሄኔ ራስ ጉግሳ፤ የወሌ ልጅ አልጋቸው ላይ ጉብ ብለው፣ “የማነው ነጫጭባ ደሞ! እሱ ይምጣና እጅ ይንሳ እንጂ፤ እኔ እበራፍ ወጥቼ እንዳጎነብስለት ነው የከጀለው? ያውም በቤቴ፤ በግዛቴ” እያሉ አካኪ ዘራፍ ለማለት ሲቃጣቸው ይታዩኛል። አንባቢ ሆይ! አይታዩህም?
አርምብራስተር እንደሆነ ገና ከሱዳን ሳይነሳ ‘እነኚህን አበሾች ለፈረንጅ ክብር ማሳየት እንዳለባቸውና የነሱን የበታችነት፤  ምን ጊዜም ቢሆን እኛ ነጮች ሊሰገድልን እንደሚገባን አስተምራቸዋለሁ ብሎ ስለነበር እራሱን አሳምኖ የመጣው፤ አሁን ደጃፉ ላይ ቆሞ የሚነገረውን ምክንያት አላመነውም። ሆኖም የሽንፈት እንዳይመስልበት ሳይገባ ወደድንኳኑ ከመመለሱ በፊት፣ “ስለ ድንገተኛ ሕመማቸው አዝናለሁ። አሁን የሚያስፈልጋቸው ሐኪም እንጂ እንግዳ ባለ ሥልጣን አይደለምና ‘እግዚአብሔር ይማርዎ’ በሉልኝ” ብሎ ተመለሰ።  የዲፕሎማቲክ ፍጥጫ! ማለት ይሄ ነው።
«ጀምበር ልትጠልቅ ስትዳረስ» ይላል አርምብራስተር «ደጃዝማች መሸሻ እና ፊታውራሪ ቡሰሪ አድርሱ የተባሉትን ደብዳቤ ይዘው እሰፈሬ መጡ።» ደብዳቤው የተላከው ከወይዘሮ ዘውዲቱ ነበር።  እንግዲህ የኔ ግምት፣ ራስ ጉግሳ ፈረንጁ ከበር ተመለሰ ሲሏቸው የጠበቁትን ሁኔታ ሳይሆን ይህ ክስተት ጃንሆይ ምኒልክን ያስቆጣብኛል በሚል ተደናግጠው ወደሚስታቸው ይሮጡና የሚቀጥለውን ደብዳቤ እንዲጽፉ የለመኑ ይመስላል። አንባቢ ምን ትላለህ?  ደብዳቤው የሚከተለው ነው፦
«ተላከ ከልዕልት ዘውዲቱ፥ ወለቱ ለዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ፣ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ፤
«ይድረስ ለእንግሊዝ መንግሥት ጂንናር፤ (ጄኔራል ለማለት ይሆን?)
«እንደምን ሰንብተሃል? እኔ እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነኝ። የንጉሠ ነገሥቱ ልጅ፣ ደጃዝማች ወሰን ሰገድ** ሞቶ ኀዘን ላይ ነኝ። መምጣትህን ስሰማ ከመመለስህ በፊት እንገናኛለን ብዬ ነበር። አሁን ከበር መመልስህን ሰማሁ። 
«ራስ እግራቸውን አሟቸው አንድ አምሥት ቀናት ሆናቸው። ነገ በማለዳ ብትመጣ ኅመማቸውን ታየዋለህ፤ እኔ እና አንተም እንገናኛለን፤ በመንግሥትህና በኛም መሃል ወዳጅነት ይሆናል።
«ይሄን ደብዳቤ የላኩብህ በእናቴ ወንድም፣ በተከበሩ አጎቴ እጅ ነው።
«ሚያዝያ ፱ ቀን ፲፱፻ ዓመተ ምሕረት በደብረ ታብር ከተማ ተጻፈ»

ጥጋበኛው እንግዳችን ታዲያ ለዚህ ደብዳቤ መልሱን “ማታውኑ ጻፍኩላቸው” ይለናል። ደብዳቤውም ከተገቢው ሰላምታ በኋላ እንዲህ የሚል ነበር።
«የእሜቴ ደብዳቤ ደርሶኛል። እንደምን ሰንብተሃል? ብለው የጻፉት፣ በርስዎ ግምት ለብሪታኒያ ባለ-ሥልጣን ተገቢ አጻጻፍ ይመስልውታልን? መምጣቱን ነገ በማለዳ እመጣለሁ። ነገር ግን ራስ ውጭ መጥተው ካልተቀበሉኝ የማልገባ መሆኔን ይወቁት። ይሄ የግል ኩራት ሳይሆን የመጣሁት በመንግሥት ጉዳይ ስለሆነና ጉዞዬም በብሪታኒያ መንግሥት እና በንጉሠ ነገሥቱ መኻል የተወሰነ/የተመቻቸ በመሆኑ ነው።»

ጧት ምን ይከሰት ይሆን? ደጃዝማች መሸሻ እና ፊታውራሪ ቡሰሪ ከአርምብራስተር ጋር አብረው ዊስኪ እና ኩመል ሲቀመቅሙ አምሽተዋል። እንደአርምብራስተር ትረካ ብዙ ነገሮች እያነሱ ሲጫወቱ ቢያመሹም እሱ ነው ተገቢ አቋም የያዘው ወይስ ራስ ጉግሳ በሚለው ላይ “ብዙ ከተሟገትን በኋላ የኔ አቋም ትክክል መሆኑን ስላመኑ ጧት ጠሐይ ሳትወጣ ብመጣ በሸክምም ቢሆን ራስን አውጥተን እናገናኝሃለን አሉኝ” ይለናል። እግረ መንገዱንም የአበሾችን ብሒል እና አስተሳሰብ ይገባኛል ማለቱ በውሉ እንዲሰመርለት ይመስላል፤ ጠሓይ ሳትወጣ ማለታቸው “ቡዳ እንዳይበላቸው” ማለታቸው ነው በማለት ተርጉሞት ያልፋል።
ለማንኛውም እነዚህን ሁለት አዛውንት “ሞቅ ይበላቸው እንጂ አልሰከሩም” ይልና የሚከተለውን፣ ለራስ ጉግሳ የጻፈውን ደብዳቤ አስይዞ ሸኛቸው።

«ነገ ማለዳ እመጣለሁ። ወጥተው ካልተቀበሉኝ ግን እንደማልገባ እና ወደ ማኅደረ ማርያም ጉዞዬን እቀጥላለሁ። በንጉሠ ነገሥቱ ትዕዛዝ መሠረት መንገድ መሪ እንዲልኩልኝ በትህትና አሳስብዎታለሁ።»

በማግሥቱ የሰፈሩን ጓዝ እንዲጭኑ አዞ ወደ ራስ ጉግሳ ግቢ “ጠሓይ ሳትወጣ” ደረሰ። ዳሩ ግን ተፈርቶ የነበረው “የሰው ዓይን” ቀድሞት ግቢው በገባው ሕዝብ “ይርመሰመሳል”። ከብዙ ወዲያ ወዲህ በኋላ ራስ ጉግሳ በቅሎአቸው ላይ ተቀምጠው ሲመጡ “ጤናማ ይመስላሉ፣ ነገር ግን የረብሻ ገጽታ አለባቸው” «ከበርጩማዬ ብድግ ብዬ ሰላምታ ሰጠኋቸውና እጅ ለጅ ከተጨባበጥን በኋላ ፈረሴ ላይ ወጣሁና አብረን ወደግቢ ገባን። አዳራሻቸው ውስጥ ስንቀመጥ ወደሰፈሬ መላክተኛ ልኬ ጭነቱን እንዲያወርዱና ድንኳኑንም እንዲተክሉ ትዕዛዝ አስተላለፍኩ።» ይላል ደራሲው፣ በማሸነፉ የተሰማውን ደስታ መደበቅ አቅቶት።  
            መግቢያ ውይይታቸው፣ ባይገርመንም በራስ ጉግሳ ኅመም ላይ ያተኮረ ነበር።  አርምብራስተር ታዲያ የሽሙጫ ኀዘን ተውኔቱን ከገለጸላቸው በኋላ በወቅቱ ለቁርጥማትና የጡንቻ ውጥረት ጥሩ መድሃኒት ነው ተብሎ በሰፊው በብሪታኒያ የሽያጭ ግፊት ይደረግለት የነበረውን “የኤሊማን የፈረስ ቅባት” እና ወዶኮሎኝ ላክሁላቸው ሲል የጀመረኝ ሳቅ አሁንም ይሄንን ስጭር ጉንጮቼን በዕንባ እያራሰው ነው።  የአንባቢንም የጥርሶች ወገብ እንዳይሰብር መጸለዬ አይቀርምና አይዞን!
            ከዚህ በኋላ አርምብራስተር እና ራስ ጉግሳ ደህና እንደተግባቡ ያበሥርና የወይዘሮ ዘውዲቱን ደብዳቤ ጉዳይ እንደገና ያነሳዋል። አሁን ታዲያ ግልጽ በሆነ ቋንቋ «ማንኛውም አውሮፓዊ፤ በተለይም በመንግሥት ባልደረባነት ወይም ሥልጣን በመያዙ የሚመጣ አውሮፓዊ በምንም አኳኋን (ከአንቱታ በስተቀር) በእንደዚህ ዓይነት እንዲጠቀስ መፍቀድ የለበትም። እንዲያውም ለራሱ የነጭ ዘር ክብር ሲል አጠራሩ እንዲስተካከል ማድረግ ግዴታው ነው።» ይልና «የወይዘሮ ዘውዲቱ ደብዳቤ የሳቸው ቃል ቢሆንም በፀሐፊ እጅ የተዘጋጀ መሆኑን አውቃለሁ ነገር ግን አጻጻፉና ያዘለውን መልዕክት ብዙዎቹ መኳንንትና ሹማምንት  የሰሙት በመሆኑ ማለፍ አልቻልኩም።» ነው የሚለው።
            የሆነ ሆኖ ከራስ ጉግሳ ጋር የጀመረውን ውይይት ሲጨርስ ወደወይዘሮ ዘውዲቱ አዳራሽ ተወሰደና «እኔ ስለደብዳቤው ማንሳት አልፈለግሁም ነበር። ዳሩ ግን ወይዘሮ ዘውዲቱ እራሳቸው አነሱብኝና አዲስ አበባ ብዙ ፈረንጆችን እንደሚያውቁና በወዳጅነት መንፈስ አንተ እያሉ እንደሚጠሯቸው ነገሩኝ። እኔ ግን እሜቴ ከቅርብ ወዳጅችዎ ጋር በዚህ ዓይነት ይነጋገሩ ይሆናል፤ በአገራችሁ ግን ለአገልጋዮቻችሁ ትዕዛዝ ስትሰጡም አንተ/አንቺ እያላችሁ መሆኑን አውቃለሁ። ደብዳቤዎን በላኩልኝ ወቅት እኔና እርስዎ አንተዋወቅም፣ ወዳጆችም ልንባል አንችልም። አልኳቸው። በደብዳቤውም ላይ ‘አንተ’ ያስባለኝ  የወዳጅነት መንፈስ ቀርቶ አሁን ስንነጋገር አንቱ እያሉ ነበር የሚያወጉኝ»
            ወደሰፈሩ ከተመለሰ በኋላ ከወይዘሮ ዘውዲቱ የተላከ ጥልፍ እና ደብዳቤ ይደርሰዋል። ደብዳቤው ግን ሁኔታውን አስተካክዬዋለሁ ብሎ በአመነበት ሳይሆን እንደበፊተኛው ‘አንተ’ የሚል ነበር። ጎሽ የኔ እመቤት! አንጀቴን አራሱልኛ። እሱ ብሎ አንቱ!
«ወደአገርህ ይዘኸው እንድትሄድ ይሄንን ጥልፍ ሰድጀልሃለሁ።» የሚል ደብዳቤ ነው የተላከለት።አርምብራስተር ወደሱዳን ከተመለሰ በኋላ ይሄንን ጥልፍ አስገምቶ ዋጋው ፬ የግብጽ ፓውንድ እንደሆነና ይሄንኑ ሒሣብ ለመንግሥት ገቢ አድርጎ ጥልፉን እንዲያስቀረው ፈቃድ ይጠይቃል።  እግረ መንገዱንም የሱዳን መንግሥት ለራስ ጉግሳ  ፶ የግብጽ ፓውንድ፤ ለወይዘሮ ዘውዲቱ ደግም  ፵ የግብጽ ፓውንድ የሚያወጡ ገጸ በረከቶች እንዲላኩ አሳስቧል።
ቆሽቱ ያረረው አርምብራስተር ታዲያ ከራስ ጉግሳ ጋር በቀጣዩ ግንኙነቱ «ደብዳቤውንና ጥለቱን አሳየኋቸውና በክቡርነታቸው ፈቃድ ጥለቱን እወስደዋለሁ፣ በዚህ መልክ የተጻፈ ደብዳቤ ግን ወደመንግሥቴ ይዤ ልሄድ አልችልም ብላቸው» ይልና ለእኔ “የአራዳ ቀደዳ” በሚመስል ዓይነት «ራስ ጉግሳ ብዕር እና ቀለም አስመጡና ደብዳቤውን ለማረም ሞከሩ። ዳሩ ግን በአማርኛ የተጻፈን ደብዳቤ በዚህ ዓይነት ለማረም መሞከር ግሦቹን እና የተውላጠ-ስሞችን በሙሉ ማስተካከልን  ስለሚጠይቅ፤ ወይ የተስተካከለ ደብዳቤ ይጻፍ አለበለዚያ ጥልፉ ይመለስ ብዬ አቋሜን ስላጠበቅሁ፤ ወይዘሮ ዘውዲቱ የተስተካከለ ደብዳቤ አጽፈው ላኩልኝ።» በማለት ይደመድማል።
            ከዚህ በኋላ ራስ ጉግሳ ከአውራጃቸው ድንበር እስከ አባይ ዳር ድረስ አሸኝተውት እሱ ወደ ጎጃም ወደራስ መንገሻ አቲከም እና ደጃዝማች ሥዩም ግዛት አመራ። ስለነሱ ደግሞ ያስገባውን ኀተታ በሌላ ጊዜ እናያዋለን።
እስከዚያው በጥሞና ስለተከታተሉት እያመሰገንኩ፤ ከታሪኩ የምንጨምቃቸው አንዳንድ ትምህርታዊ ቁም ነገሮችን እንደምናገኝበት አልጠራጠርም።
** ደጃዝማች ወሰን ሰገድ ወዳጆ ጎበና የምኒልክ ልጅ የወይዘሮ ሸዋረጋ ልጅ ሲሆን መጋቢት 20 ቀን 1900 ዓ/ም ነው የሞተው።
ዋቢ ምንጭ
P.R.O. FO 401/11; [34155/ Enc. # 221]; Mr. Armbruster to Major Phipps ; Report of Visit of Abyssinia – 1908

No comments:

Post a Comment

እርስዎስ ምን ይላሉ?