Sunday 27 January 2013

አስፋ ወሰን ኃይለ ሥላሴ - ክፍል ፩


(ከድል እስከ ታኅሣሡ ጉሽ)

ቻርድ ግሪንፊልድ የልዑል አልጋ ወራሽ መርዕድ አዝማች አስፋ ወሰን ኃይለ ሥላሴን ሞት ተከትሎ በብሪታንያው ‘ኢንዲፔንደንት’ ጋዜጣ ላይ በጻፉት የሙት መወድስ (ኦቢችዋሪ) ላይ «መስከረም ፲፯ ቀን ፲፱፻፱ / መኳንንቱ እና  የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንቱ በተሰበሰቡበት አቡነ ማቴዎስ የልጅ ኢያሱን መሻር እና መወገዝ ሲያበስሩ፤ ሕፃኑ አስፋ ወሰን በአንቀልባ ታዝሎ ከሁለት አሽከሮች ጋር እንግሊዝ ለጋሲዮን ተደብቆ ነበር።»[1] ይላሉ።



አስፋ ወሰን በ፲፱፻፷፭ / ሌሊቱን በደም ቋጠሮ ምት በታመሙ ማግሥት፣ ጥር ቀን በአስቸኳይ በእንግሊዝ የጦር ጥያራ  ወደ ሎንዶን ለሕክምና እንደወጡ ወደአገራቸው በሕይወት ሳይመለሱ ቀርተዋል። አጋጣሚውንም በመጠቀም በዚህ ጦማር አማካይነት ላስታውሳቸው እወዳለሁ።
ስለ መርዕድ አዝማች አስፋ ወሰን ኃይለ ሥላሴ ማንነት እና እንቅስቃሴ ብዙ ሊጻፍ የሚገባው ቢኖርም፤ እስካሁን የቀረቡልን ቢያንስ ተቆጥበው የተንጠባጠቡ፤ በደፈናው ግን ሚዛናዊነት የጎደላቸውና በጎ ገጽታን ብቻ ለማሳየት ተመርጠው የቀረቡ ጽሑፎች ናቸው ቢባል ከእውነታው አይርቅም። ለምሣሌ እንደነ ሪቻርድ ግሪንፊልድን የመሰሉ ምሁራን የተዉልን ዘገባዎች «በአርባዎቹ አሥርት ዓመታት ለውጥ አውሎ ነፋስየአፍሪካን አኅጉር በሚጠራርግበት ወቅት፤ ምናልባት እሳቸው [አስፋ ወሰን] ሳያውቁ፤ ስማቸው ከብዙ የተቃዋሞ ሹክሹክታዎች ጋር በመያያዝ ይነሳ ነበር።» በሚል አስቀምጠውታል። የኚህን ሰው ሙሉ ገጽታ እና ለኢትዮጵያ ያበረከቱትንም ሆነ አደናቀፉ የሚባሉበትን አስተዋጽዖ፣ ሚዛናዊና እውነት-አዘል በሆነ የትምህርት ማራመጃ ምርምር የተመረኮዘ የጥናት ውጤት ሊቀርብልን ይገባል።

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ግን ይሄንን እጥረት ለሟሟላት ሳይሆን፤ ቢያንስ ከብሪታንያ ምንጭ የተገኙትን እና ከዚህ በፊት ያላየናቸውን፤ ምናልባትም የባለታሪኩን ደካማ ጎን የሚያሳዩ ጥቂት መረጃዎችን ለአንባብያን ለማካፈል ሲሆን፤ ከዚህ ባሻገር ግን በአሜሪካ፤ በኢጣልያ፤ በጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ባሉበት አገራት የሚገኙ ቤተ መዛግብትን በመመርመር የሚያገኙትን መረጃ እንዲያካፍሉን ለማበረታታና ስለአልጋ ወራሹ ታሪክ በሰፊውና በሙሉው ለመጻፍ ለሚፈልግም ወገን ሊያገለግሉ የሚችሉ እይታዎችን ለማቅረብ ነው። የዚህ ጽሑፍ ምንጮችና ጠቃሚ መረጃዎች በብሪታንያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብት የተገኙ ሲሆኑ ከአዲስ አበባው ተልዕኮዋቸው በምስጢር የተላኩ ዘገባዎች፤ ወርኀዊና ዓመታዊ ሰነዶች፤ እንዲሁም አልጋ ወራሹ እራሳቸው በሌጋሲዮኑም ሆነ በመኖሪያ ቤታቸው ለርዕሰ ተልዕኮው (አምባሳደር) የሰጧቸውን ምስጢራዊ ‘ቃለ-ምልልስ’ ያካትታሉ። እነዚህንም ምስጢራዊ ሰነዶች በምንመረምርበት ጊዜ በአገር ውስጥ ስለአልጋወራሹ (በተለይም በአባታቸው እይታ) ይነዙ የነበሩትን ሐሜታዎች፤ “እሳት በሌለበት ጭስ የለም” እንደሚባለው የአዎንታ ገጽ ሊሰጡት የሚችሉ እንደሆኑ እንገነዘባለን።

በቀዳሚነት የተገኘው የሰነድ ማኅደር[2] የሚያተኩረው በወቅቱ ከጠላት ወረራ በኋላ፤ ጥር ፳፫ ቀን ፲፱፻፴፬ / አዲስ አበባ ላይ የተፈረመውበብሪታኒያ ንጉዛት እና በኢትዮጵያ መኻል የተመሠረተ ውል እና የወታደራዊ ስምምነት(Agreement and Military Convention Between the United Kingdom and Ethiopia) በተግባር ላይ የዋለበት ዘመን ሲሆን፣ በዚሁ ውል አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (ሀ)[3] መሠረት በደሴ የወሎና የበጌምድር ጠቅላይ አገረ-ገዥ መሥሪያ ቤት፣ የአልጋወራሹ አማካሪ ከተባለው ሻምበል ቻርልስ ፉት-ጌይትስኪል ወደ ብሪታኒያው ርዕሰ-ልዑካን የተላከ ምሥጢራዊ ደብዳቤ  መነሻው ነው። ታዲያ የዚህ ሰው ደብዳቤ ጥር ፳፫ ቀን ፲፱፻፴፭ / የተጻፈ ሲሆን በመግቢያው አንቀጽ ላይ አልጋ ወራሹ ጻፍ ባሉት መሠረት እንደሆነ ይገልጽና ጉዳዩንጥብቅ ምሥጢር እና የግል ጉዳይየሆነ ማመልከቻ ነው ይላል።

ፉት-ጌይትስኪል እንዲጽፍ የታዘዘው ደብዳቤ ላይ የአስፋ ወሰን የማመልከቻቸው መንስዔ በሚል፦

() የወቅቱን ጠቅላይ ግዛታዊም ሆነ አገር-አቀፍ አስተዳደር በትክክል እየተሠራ እንዳልሆነና እንዲያውም ለብዙ ዘመናት የተስተካከለ እንደማይሆን

() የማስተዳደሪያ ገንዘብ እጥረት እንዳለና በሚገኝበትም ጊዜ ወደየግዛቶቹ ማከፋፈል  ትልቅ ፈተና መሆንን

() የገንዘብ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ዋናው እንቅፋት እንደሆነ

() የሚኒስትሮቹ ምክር ቤት የጠቅላይ ግዛቶችን የገንዘብ ምድብ ያለማስተላለፍ ችግር እንደሆኑ ከገለጸ በኋላ አልጋ ወራሹ መፍትሄ ብለው ያቀረቧቸውን ሁለት ነጥቦች በተራ ያቀርባቸዋል። እነዚህም፦
1) ለተወሰነ ጊዜ ከአገር ውጭ ሆነው ወይም በብሪታኒያ ፈቃድ ካርቱምንና ሰፊውን የሱዳን ግዛት በመኪና እንዲጎበኙ፥ አለበለዚያም

2) ከዋናው የኢትይጵያ ብሔራዊ ሠራዊት የተውጣጡ እና በብሪታንያ መንግሥት የታጠቁ ሦስት በጦሊዮኖች፣ በሳቸው አዝማችነት ወደሰፊው የሁለተኛ ዓለም ጦርነት ግንባር እንዲሰለፉ ሲሆን፤ ፉት-ጌይትስኪል የአልጋ ወራሹ ምርጫ ጦርነቱ ላይ መሳተፍ እንደሆነ በደብዳቤው ገልጿል።

ታዲያ ይሄ አማራጭ የተወደደበትን ምክንያት ሲተነትን፣ የራሱ አመለካከት ይሁን ወይም አሁንም የአስፋ ወሰንን አስተሳሰብ የሚያንጸባርቅ እንደሆነ ግልጽ ባይሆንም፤ከዘመቻው ሲመለሱ በሕዝቡ ዓይን ከአሁኑ የበለጠ ዝናን እንደሚያተርፉ እና ይሄም ወደፊት አገሪቱን ለመቆጣጠርና ለማስተዳደር ይረዳቸዋል።ይላል። የአልጋ ወራሹ ምርጫ ብሎ የጠቀሳቸው የሠራዊቱ ክፍሎች የሁለተኛና አምስተኛ ክፍለ ጦር እንዲሁም “የወሎ ባንዳ” ብለው እንግሊዞቹ የሠየሟቸው የወሎ አርበኞችን ነው።

ፉት-ጌይትስኪል ለማንኛውም አልጋ ወራሹ በአሁኑ ጊዜ እያጋጠማቸው ባለው ቅራኔ ምክንያት ለሕዝባቸው ምንም መሥራት ባለመቻላቸው ለተወሰነ ጊዜ ከአገር ወጥቶ 'መሰደድን' የመረጡ እንደሆነ ያበሥርና በድጋሚ ይሄ ደብዳቤው በጥብቅ ምሥጢር እንዲያዝ አሳስቦ፤ አስፋ ወሰን የብሪታኒያው ርዕሰ-ልዑካን በወዳጅነቱ እንዲረዳቸው መጠየቃቸውን ያመለክታል። 

ከሁሉም በላይ የሚያስደንቀውና የሚያስደነግጠው ግን የዚህ ደብዳቤ መደምደሚያ አንቀጽ ላይ ያሰፈረው አረፍተ ነገር ሲሆን'፤  «ልዑልነታቸው፤ የአገሪቱ አስተዳደር ከሃያ እስከ ሃያ-አምሥት  ዓመታት በብሪታኒያ እጅ ካልሆነ ምንም ተስፋ የላትም።» እንዳሉትና እሱም በወቅቱ ይሄ የማይቻል መሆኑን ገልጬላቸዋለሁ ባይ ነው።
ታዲያ የውቅቱ የብሪታኒያ ርዕሰ-ልዑካን የነበረው ሮበርት ሃው (Sir Robert G. Howe, G.B.E., K.C.M.G.) ይሄንን የፉት-ጌይትስኪልን ደብዳቤ ወደብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሲልክ አባሪ አድርጎ በላከው ደብዳቤ ላይ የአልጋ ወራሹ አማካሪ ደብዳቤውን ለሱ መጻፍ እንዳልነበረበት ይገልጽና በእንደዚህ ዓይነት ታላቅ የአገር ውስጥ እና የዘውድ ውርስ መርኅ ላይ ከንጉሠ ነገሥቱ  ተጠይቆ ካልሆነ በቀር ጣልቃ መግባት እንደማይችል ይገልጻል። የአልጋ ወራሹንም አገር ጥሎ መሄድ መንስዔው ከአባታቸው ጋር የነበረውና ለእንግሊዞቹ ምሥጢር ያልነበረው አለመግባባት ይሆን የሚል ጥርጣሬ እንዳለው ይገልጻል። የብሪታኒያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለ-ሥልጣናትም በደብዳቤዎቹ ላይ ያላቸውን አመለካከት ሲገልጹ ጉዳዩ ለአምባሳዶሩ "በቃል የሚተላለፍ እንጂ በጽሑፍ መደረጉ ስህተት" እንደሆነ ይገልጹና "ምንም ዓይነት እርምጃ" እንደማያስፈልግ ከመደምደማቸው በፊት "በአስፋ ወሰን እና በአባታቸው መኻል ግጭት የተለመደ" መሆኑን ሳይዘግቡ አላለፉም

እንግዲህ የአልጋ ወራሹ ወደጦርነት ግንባር የመላክ ፍላጎት እና ልመና ክሽፍ መሆኑን ብናውቅም በወቅቱ ምን ዓይነት እንቅፋት ቢገጥማቸው ኖሯል እንደዚህ ዓይነቱን የክብሪት ጨዋታ የመረጡት? ወይስ ይሄ ክስተት የሰውየውን ‘ደካማነት’ የሚያመላክት ይሆናልን? በአርቆ አስተዋይነትስ ሚዛን እንዴት ልንመዝናቸው እንደሚገባን ያመላክት ይሆን? የአስተዳደር እና የመሪነት ብቁነታቸውንስ? እንግሊዞቹ ለራሳቸው ጥቅም ማራመጃ ብለው የፈጠሩት ሐሰተኛ ሐተታ ነው ለማለት ባያዳግትም እንኳ፤ ከፈጠሩትስ በኋላ ላለመጠቀም ለምን ወሰኑ? የሚለውን ቁልፍ ጥያቄ ስለሚያስከትል በኔ አስተያየት “እሳት በሌለበት ጭስ አይኖርም” እንደሚባለው ደብዳቤውን ያመነጩት አልጋ ወራሹ ናቸው ወደሚለው አዘነብላለሁ። የሆነ ሆኖ ጠለቅ ያለ ጥናት እና ምርምር የሚጠይቅ ምዕራፍ እንደሆነ ጥርጥር ሊኖር አይችልም።

የታኅሣሡ ግርግር

ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ እና በወንድሙ ገርማሜ ነዋይ ተጠንስሶ  ማክሰኞ ታኅሣሥ  ቀን ፲፱፻፶፫ / የፈነዳው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በዚያው ዕለትእቴጌ ታመዋልና ወደ ቤተ መንግሥቱ ይምጡበሚል ሰበብ አልጋ ወራሹንም ሆነ አዲስ አበባ የነበሩትን መሳፍንት፤ መኳንንት፤ ሚኒስቴሮች፤ መኮንኖችና ከፍተኛ ባለ-ሥልጣናትን ሰብስበው በማጎር ተጀመረ።  በማግሥቱም በገርማሜ ንዋይ፣ በሌተና ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁና ባልደረቦቻቸው የተዘጋጀ ንግግር አልጋ ወራሹ ለሰፊው የኢትይጵያ ሕዝብ በራዲዮ እንዲያስተላልፉ ተደረገ። ይሄ ንግግር ምናልባትም ሕዝቡ የአልጋ ወራሹን ድምጽ ለመጀመሪያም ለመጨረሻም ጊዜ የሰማበት እንደሆነ ይገመታል። ሆኖም የራዲዮ ገለጻው አልጋ ወራሹ መንግሥት በቆረጠላቸው ደመወዝ እየተዳደሩ ለሕገ መንግሥት የሚገዙ ንጉሥ ሆነው እንደሚያገለግሉ እራሳቸው ለሕዝቡ በራዲዮ አስተላልፉ።[4]
   
አሥራ አምስት እስረኞች እና በርካታ ወታደሮች ሕይወታቸውን ያጡበት ይህ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ዓርብ ታኅሣሥ ቀን በክሽፈት ከተገባደደ በኋላ በማግሥቱ ቅዳሜ ንጉሠ ነገሥቱ አዲስ አበባ ሲገቡ አልጋ ወራሹ ድንጋይ ተሸክመው እግራቸው ላይ እንደወደቁና ንጉሠ ነገሥቱም በልጃቸው ላይ ከፍ ያለ ኀዘን ተሰምቷቸውይቅር ብለንሃል፤ እንረሳሃለንምብለዋቸው እንደነበር በርካታ ዘጋቢዎች ይጠቅሳሉ። ሪቻርድ ግሪኒልድ ንጉሠ ነገሥቱ አልጋ ወራሹን ለፍርድ ማቅረብ አርቆ አሳቢነት የጎደለው ምርጫ መሆኑን በመገንዘብ ቢተውትም እንኳ ምን ተብሎ እንደነበር ለማወቅና ፍንጭ ለማግኘት ሲሉ በምሥጢር የተቀዱትን የፍርድ ቤት ቴፖች በማዳመጥ ብዙ ሰዓታትን ያሳልፉ ነበር ብለዋል።

በወቅቱ በኢትዮጵያ የብሪታንያ መንግሥት ርዕሰ-ልዑካን የነበሩት ዴኒስ ራይት (Sir Denis A.H. Wright, G.C.M.G) በዓመታዊ ዘገባቸው ላይ «የንጉሠ ነገሥቱ ቅርብ አገልጋዮች ሲገደሉ፤ አንዳንድ ታማኝ መኮንኖች ደግሞ ከሃዲነታቸው ተመስክሯል። የአልጋ ወራሹም ያልተረጋገጠ አቋም ንጉሠ ነገሥቱ በሞቱ ጊዜ ሥልጣኑን ለመረከብ ያላቸውን ብቃት የበለጠ ጥርጣሬ ውስጥ ከማስገባቱም ባሻገር የሰሎሞናዊውን የዘር መሥመር ቀጣይነትንም ጭምር ጥርጣሬ ውስጥ ይከታል»[5] በሚል ማጠቃለያ ዘግበውታል።

እንግዲህ በዚህ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ላይ የአስፋ ወሰን ኃይለ ሥላሴ ድርሻ ምን ነበር? የሚለውን አንገብጋቢ ጥያቄ ስንመለከት በሰፊው የተናፈሰውና በይፋዊ የተዘገበው ‘ታሪክ’፤ አመጸኞቹ መጀመሪያ የእናታቸውን ‘ድንገተኛ ሕመም’ ምክንያት በማድረግ በቁጥጥር ሥር ካዋሏቸው በኋላ በመሣሪያ በማስገደድ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በራዲዮ የተላለፈውን መልዕክት እንዲያነቡ አድርገዋቸዋል የሚለው ነው። ዳሩ ግን፤ “ከጠንሳሾቹ አንዱ ብሎም የሙከራው መሪ እሳቸው ነበሩ”፤ “አመጸኞቹ ዓላማቸውን ካስረዷቸው በኋላ ይሄንኑ በመደገፍ ያለምንም ማስገደድ መልዕክቱን አስተላልፈዋል”፤ “ሙከራውን የጠነሰሰው የአሜሪካው ሲ. አይ. ኤ. ሲሆን የአመጹን መሪዎችና ይሄንኑ ‘የስለላ ድርጅት’ በምስጢር ያገናኟቸው አስፋ ወሰን ናቸው”፤ እነዚህን የመሳሰሉ አስተያየቶች አብረው ሲራገቡ የቆዩ ሐሜታዎች ከመሆናቸውም ባሻገር በልዩ ልዩ አገራት ቤተ መዛግብት እና በአገር ውስጥም የሚገኙ ማስረጃዎች በንተጠባጠቡ ቁጥር የሚነሳ መሆኑ አያጠራጥርም።

(በክፍል ይቀጥላል)



[1] ሪቻርድ ግሪንፊልድ፤ የሙት መወድስ (ኦቢቹዋሪ)”አስፋ ወሰን ኃይለ ሥላሴ ኢንዲፔንደንት ጋዜጣ (፲፱፻፺ /
http://www.independent.co.uk/news/people/obituary-crown-prince-asfa-wossen-haile-sellassie-1285476.html
[2] P.R.O.; FO 371/35626, Internal situation (1943)
[3] Agreement and Military Convention Between the United Kingdom and Ethiopia, Addis Ababa, January 31, 1942; page 3
[4] ውክፔዲያ contributors. የታኅሣሥ ግርግር [Internet]. ውክፔዲያ, ; 2013 ጃንዩ. 25, 10:33 UTC [cited 2013 ጃንዩ. 26]. Available from:http://am.wikipedia.org/w/index.php?title=%E1%8B%A8%E1%89%B3%E1%8A%85%E1%88%A3%E1%88%A5_%E1%8C%8D%E1%88%AD%E1%8C%8D%E1%88%AD&oldid=287991.
 [5] P.R.O., FO 371/154836; Denis A.H. Wright;  Annual Report from Ethiopia for 1960

No comments:

Post a Comment

እርስዎስ ምን ይላሉ?