Sunday 3 February 2013

አስፋ ወሰን ኃይለ ሥላሴ - ክፍል ፪


«እሳት በሌለበት ጭስ የለም!» ወይስ «ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ!» ?


ክፍል ላይ በልዑል አልጋ ወራሽ መርዕድ አዝማች አስፋ ወሰን ኃይለ ሥላሴ ስም ተጻፈ የተባለ፤ ሕሊናን የሚረብሹ ነጥቦችን ያዘለ ደብዳቤ ተመልክተናል። በታኅሣሥ ፶፫ቱም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ያተረፉትን፤ እንደሙጫ ስማቸው ላይ ተጣብቆ የቀረውን ሐሜታም ተመልክተናል።

፪ኛው ክፍል ደግሞ የምንዳስሳቸው የብሪታኒያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብት ሰነዶች በተለያዩ ጊዜያት አልጋ ወራሹ ከብሪታኒያ ርዕሰ-ልዑካን እና ከአሜሪካው ርዕሰ-ልዑካን ጋር ያካሄዷቸውን ሰፊ ውይይቶችና በወቅቱ የአገር ፖለቲካ ላይ ለነኚሁ የባዕድ መንግሥታት ወኪሎች የሰጡትን አስተያየት ያካትታል።

 
እና ፷ዎቹ አሥርት ዓመታት

/ ጆን ስፔንሰር “Ethiopia at Bay” በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ስለ አልጋ ወራሹ ካሠፈሯቸው ጥቂት አስተያየቶች «ኃይለ ሥላሴ ሁለተኛ ወንድ ልጃቸውን ልዑል መኮንንን የበለጠ ማቅረባቸው ምንም አያስገርምም። ከማውቃቸው ኢትዮጵያውያን ባለ-ሥልጣናት ሁሉ በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ አቋም ከመውሰድ በመቆጠብ፤  አልጋ ወራሽ አስፋ ወሰንን የሚስተካከላቸው የለም።» ይሉና እንደውም የ፶፫ቱ ግርግር ቀንደኞች እሳቸውን ለመሪነት የመረጡበት ምክንያት «የታወቀው የአስፋ ወሰን ደካማ ባህሪ እንደፈለጉት ለውጡን ለማራመድ ነፃነት እንደሚሰጣቸው በመገመት ነው።»[1]

ይሄ አስተያየት በገሃድ የሚታየውን የአስፋ ወሰንን ገጽታ የሚያንጸባርቅና በሕዝቡ ምልከታ ጎልቶ እንዲታይ በሌሎችም ታሪክ ዘጋቢዎችና ምሁራን ሲጠናከር የቆየ ነው። ሆኖም፤ የዚህ ጦማር አቀናባሪ የደረሰባቸው ምሥጢራዊ ሰነዶች የሚያመላክቱት ይሄንን የሚቃረንና አልጋ ወራሹ፤ ቢያንስ ከገሃዳዊ ምልከታ የተሰወረ ባህሪ እንደነበራቸው፤ ምናልባትም የአባታቸው ዝንባሌም ወደታናሽዬው የመሆኑ ምክንያት ይሄው ከተመልካች የተሰወረ፥ ለአባታቸው ግን ግልጽ የሆነና እምነት ሊያሳድሩበት ያልቻሉት ባህሪያቸው እንደነበረ ነው።

በቀዳሚነት የምንከተላቸው ሰንዶች በተጻፉበት ወቅት፤ አገሪቱ ታኅሣሡ ግርግር ገና እያገገመች ሳለ፤ ከግርግሩ መሪዎች መኻል በሕይወት የተረፉት ጄነራል መንግሥቱ ነዋይ ለፍርድ ቀርበው በተወሰነባቸው ፍርድ መሠረት መጋቢት ፳፩ ቀን ፲፱፻፶፫ / በስቅላት ተቅጥተዋል። በግርግሩ የተገደሉትንም ከፍተኛ ባለ-ሥልጣናት የሚተኩ አዲስ ሚኒስትሮችም እየተሾሙ ገና በሥራ ልምምድ ላይ ይገኛሉ።

ጄኔራል መንግሥቱ በተክለ ሃይማኖት አደባባይ በተሰቀሉበት ዕለት አምባሳዶር ዴቪድ ራይት ከግርግሩ በኋላ በተከተሉት ሦስት ወራት ውስጥ በአገሪቱ ስለነበረው አለመረጋጋት እናመሠረታዊ ለውጥይመጣል በሚል ጉጉት  በንጉሠ ነገሥቱ ላይ ጫናዎች ከበርካታ አቅጣጫዎች አስጨንቀዋቸው እንደከረሙ በሰፊው የሚተነትንምሥጢራዊሰነድ ልከዋል[2] አምባሳዶሩ በዚህ ረዥም ሰነድ ላይ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት የቀረቡት እጩዎች ልዑል ራስ ዕምሩ ኃይለ ሥላሴና በወቅቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ አክሊሉ ሀብተወልድ መሆናቸውን ከገለጹ በኋላ የአልጋ ወራሹን አስተያየት አንቀጽ ላይ ባስቀመጡት አንድ አረፍተ ነገር፤ መጋቢት ፲፭ ቀን በሁለቱ መኻል የተካሄደውን ውይይት በመጥቀስ «ሊመጣ የሚችለውን ሁከት ለማስወገድ፣ ብቸኛው መፍትኄ ራስ ዕምሩን መሾም ነው።»ካሉ በኋላ አክሊሉ ቢሾሙ «እንደሚያሳዝናቸው ነገሩኝ» በሚል አስቀምጠውታል። ሆኖም እንግዲህ አስፋ ወሰን ያልፈለጓቸው አክሊሉ ሀብተወልድ ይሄ ደብዳቤ በተጻፈ ማግሥት፣ መጋቢት ፳፪ ቀን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ።

            አስደንጋጩና እጅግ ጠቃሚ መረጃ ያዘለው ክፍል ግን የዚሁ ደብዳቤ ፲፬ኛው አንቀጽ ሲሆን፤ አምባሳዶሩ ከተለያዩ ምንጮች በሰበሰቧቸው መረጃዎችና ከአልጋ ወራሹ ጋር መጋቢት ፲፭ ቀን ያካሄዱትን ውይይት መሠረት በማድረግ የደረሱበትን ድምዳሜ የሚያመለክት ነው። ከተቃዋሚዎቹ ቡድኖችተራማጅ እና አሻሻይ ቡድንየሚሉት ወገን ላቀደው ግፊት ስኬታማነት የቤተ-ክርስቲያንንም ሆነ የሕዝቡን ተቀባይነት ለማግኘት የአንድነት አርማ በሆነው የሰሎሞናዊ ዘር የሚመራ መሆኑን ማሳየት ስለሚያስፈልገው አልጋ ወራሹን ከጎኑ ማሰለፍ ወሳኝ መሆኑን ተገንዝበዋል ይሉናል። ቀጥለውም አነጋገርኳቸው የሚሏቸው (ስማቸውን ግን ያልገለጹልንን) የሕዝብ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር በመጥቀስ «አልጋ ወራሹ መልካም ሕገ-መንግሥታዊ ንጉሥ ይወጣቸዋል» አሉኝ ይላሉ።

ከአልጋ ወራሹ ጋርም ያካሄዱትን ውይይት በመጥቀስ የብሪታኒያው ርዕሰ-ልዑካን፤ ዴቪድ ራይት «ከወታደራዊም ከሲቪል የተቃዋሚ መሪዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት እንዳላቸው» ይሰማኛል ይሉና «መሪዎቹም እሳቸውንየአንድነት ዓርማለማድረግ ባላቸው ኃሳብ ላይ ተቃውሞ እንደሌላቸው ግልጽ ነው።» ሲሉ አስፍረውታል።

በዚሁ አንቀጽ ላይ ዴቪድ ራይት፤  አስፋ ወሰን «በ፲፱፻፴፱ /  እሳቸውን አንግሦ መንግሥት ለመቀየር ተነስቶ የነበረው የተቃዋሚ ቡድን መሪ እንደነበሩ እናውቃለን» የሚለውን አስደናቂ አረፍተ ነገር አስቀምጠዋል። ቀጥለውም በአምባሳዶሩ ግምት አልጋ ወራሹ ተመሳሳይ ዕድል በቅርቡ ወደሳቸው እንደሚመጣ የሚታያቸው ይመስለኛል ነው የሚሉት።

ተከታዩ ደብዳቤ[3] ከአዲስ አበባው ሌጋሲዮን፥ ቆንስል ሚካኤል ጆይ (Michael G.L. Joy) ሐምሌ ፳፫ ቀን ፲፱፻፶፫ / የላከው ሲሆን  ቆንስላው ለዘገባው ማዕከላዊ ጉዳይ ያደረገው፥ አሁንም ያልረገበውን ለውጥ ግፊትሲሆን፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ ጄኔራል መርዕድ መንገሻ እና የአገር ግዛት ሚኒስትሩ ጄኔራል አቢይ አበበ ንጉሠ ነገሥቱን በዚህ ጉዳይ ላይ ጠንክረው እየገፉ እንደሆነ ሲጽፍ ከሁለት ወራት በፊት አልጋ ወራሹ ለአምባሳዶሩ በነገሯቸው መሠረት በወቅቱ ጀርመን አገር ሄደው የነበሩት ራስ-ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው ሲመለሱ፥ አልጋ ወራሹ፣ ራስ ዕምሩ፣ አቡነ ባስልዮስ እና ራስ-ቢትወደድ መኮንን በኅብረት ንጉሠ ነገሥቱን ለማነጋገር መወሰናቸውን ገልጸው ነበር። ታዲያ በዚህ ደብዳቤ ቆንስሉ አልጋ ወራሽን ከሁለት ሣምንት በፊት አነጋግሯቸው እንደነበረና የተባለውም ውይይት እንደተካሄደ፤ ዳሩ ግን በአስፋ ወሰን ግምት አባታቸው ምንም ዓይነት ለውጥ እንደማያደርጉ መፍራታቸውን ዘግቧል። 

የሦስተኛው ደብዳቤ[4]  ደራሲም ከላይ የተጠቀሰው ቆንስላ ሲሆን፤ በዚህኛው ደብዳቤ ያቀረበው ሐተታ የአሜሪካው ርዕሰ-ልዑካን[5] ያካፈለውን ከአልጋ ወራሹ ጋር ያደረገውን ምሥጢራዊ ውይይት ነው። ውይይቱ የተካሄደው ነሐሴ ቀን ፲፱፻፶፫ / ነበር።  ሚካኤል ጆይ በመግቢያ አንቀጹ ላይ የአሜሪካኖቹንም እምነት ለመጠበቅ ብቻ ሳይሆን አልጋ ወራሹ፤ ልክ ከአሥርና አሥራ-አምሥት ዓመታት በፊት እንዳደርጉት፤ አሁንም እንደገና በአባታቸው ላይእየዶለቱስለሚመስል ደብዳቤው የሾለከ እንደሆነ ለሳቸውም ውድመት ከመሆኑ ባሻገር፣ ለብሪታኒያ ተልዕኮም አቋም እንዲሁ አደገኛ ስለሚሆንበጥብቅ ምሥጢርእንዲጠበቅ በማሳሰብ ይጀምራል።

በሁለተኛው አንቀጽ ላይ አልጋ ወራሹ አባታቸውን «የደከሙ ሽማግሌ ስልሆኑ በወቅቱ የፖለቲካ ክስተት ላይ ጠንካራ አቋም ሊይዙ አይችሉም» አሉ በሚል ይጀምረዋል። እንደ አስፋ ወሰን ትንታኔ ሁለት ወገኖች አሉ። የመጀመሪያው ልጅ ሚካኤል ዕምሩ አቶ ሐዲስ ዓለማየሁን ደጃዝማች ዘውዴ ገብረሥላሴን እና በፍትሕ ሚኒስቴር የደጃዝማቹ ምክትል ሚኒስትርን (ስሙ ያልተገለጸ)ያካተተ የወጣት ተራማጆች ቡድን ነው። አልጋ ወራሹ ይሄ ሰው በቡድኑ ውስጥ ታላቅ ሚና ያለው ነው ብለዋል ይላል። ሁለተኛው ቡድን ደግሞ ወታደራዊ ሲሆን ጄኔራል መርዕድ መንገሻን፣ ጄኔራል ከበደ ገብሬን እና ጄኔራል ኢሳይስ ገብረ ሥላሴን ያካትታል።

            አልጋ ወራሹ ከነኚህ ሰዎች ጋር በቡድንም ለየብቻቸውም እንደሚገናኟቸው እና ሁለቱን ወገኖች አንድ ለማድረግ እየጣሩ እንደሆነ ለአምባሳዶሩ መግለጻቸውን ያረጋግጥና ወጣቶቹ ሥልጣንን እጃቸው ለማስግባት መወሰድ ያለባቸው አስፈላጊ እርምጃዎች ላይ ከማተኮር ይልቅ የሥርዓቱ ደካማ ጎኖች ላይ በማተኮራቸው እንደሚያበሳጯቸው ገልጸው፤ «የንጉሠ ነገሥቱ መወገድ እና አዋጅ ማወጅ» የመጀመሪያ ሥራዎች ይሁኑ እንጂ የጉዳዩ መግቢያ ብቻ ናቸው ብለዋል። ሁለተኛው ወታደራዊው ቡድን ሽብር እንደሚከተል ከግንዛቤ ያስገቡት ነገር በመሆኑና የሕግ እና ሥርዓት ጠባቂ እንደመሆናቸው መጠን፤ ይሄንኑ የማስከበር ግዴታ እንዳለባቸው ከግምት ውስጥ አስገብተዋል። በአስፋ ወሰን አስተያየት  ግን ወታደሮቹ አዲስ አበባን እና አስመራን መቆጣጠር ይቻሉ እንጂ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ተወዳጅነት ስለሌላቸው ቅንጅቱን ሊሰነጣጥር ስለሚችል በወታደሮች ብቻ የሚካሄድን እንቅስቃሴ እንደማይፈልጉት ለአሜሪካው አምባሳዶር ነግረዋችዋል።  

የብሪታንያው ቆንስላ  ከአሜሪካው ርዕሰ-ልዑካን  አገኘሁ ያላቸውን እነኚህን ነጥቦች ካሠፈረ በኋላ የራሱን አስተያየት ሲያሰፍር፦

()       አልጋ ወራሹ የብሪታንያው ርዕሰ-ልዑካን ለእረፍት ከመሄዳቸው በፊት ከነበራቸው አቋም አሁን የበለጠ ገቢራዊ እንደሆኑ ከተገነዘበ በኋላ፣ ሁለቱን ወገኖች ለማጣመር እየጣሩ መሆኑን መግለጻቸው ይሄንኑ ገቢራዊነት የሚያረጋግጥ ነው። ዳሩ ግንበእሳት እየተጫወቱ ነውይላል።

()       የአሜሪካው አምባሳዶር ያስተወሷቸውን ስሞች ደገሙልኝ እንጂ ሌሎችም ሊኖሩ ይችላሉ ይልና ጄኔራል መርዕድ እና ጄኔራል አቢይ እየተራራቁ የመጡ ይመስላል ምክንያቱም ጄኔራል መርዕድ እንደ አልጋ ወራሹ አስተሳሰብ ወታደራዊ ሙከራ እንቅፋት እንደሚገጥመው ስለተገነዘቡ የበለጠ ወገን-አልባ አቋም በመያዛቸው ሌሎች ጄኔራሎችን ለማቅረብ የቻሉ ይመስላል ይላል።

()      በሱ ግምት የወጣቱ ቡድን ምንም ፋይዳ የሚያመጣ እንደማይሆን ይገልጽና ከመካከላቸው ውስጥ መሪ የሚሆን አባል ያለ እንደማይመስለው ይዘግባል።

ሚካኤል ጆይ ሐተታውን ሲደመድም፤ አልጋ ወራሹ እነኚህን ቡድኖች ለማጋጠም የሚያስቸግራቸው እንደሆነና ምናልባትም ንጉሠ ነገሥቱ የዚህን ሴራ ጥንሰሳ ሳይደርሱበት እንዳልቀሩ ይገምታል። ሆኖም ባመቻቸው ጊዜ ሴረኞቹን ማጋለጥ ስለሚችሉ አድፍጠው እየተጠባበቁ ይሆናል ይላል።

እውነትም ንጉሠ ነገሥቱ በጉዳዩ ደርሰውበት ሊሆን ይችላል፤ ቆንስል ሚካኤል ጆይ በነሐሴ ፳፭ ቀን ፲፱፻፶፫ / ያበረረው ቴሌግራም[6] እንደሚያሳየው ነሐሴ ፲፪ እና ነሐሴ ፳፫ ቀን ብዙ ሰዎች እንደታሰሩና ይህ ቴሌግራም በተላከ ማግሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከካፒታሊስቱና ሶሻሊስቱ ጎራ ውጭ የሆኑ የገለልተኛ አገሮች ማኅበር የመጀመሪያ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ወደቤልግራድ እንደሚነሱና አልጋ ወራሹንም አስከትለው ለመሄድ እንደቆረጡ ያበሥራል።

አራተኛው ሰነድ[7] መጋቢት ፳፪ ቀን ፲፱፻፶፭ / የተጻፈ ሲሆን፤ ደራሲው  አምባሳደሩ ሮበርት ራሰል ናቸው።ምሥጢራዊ እና በጥንቃቄ የሚጠበቅበሚል ማስጠንቀቂያ የተወሰነው ይህ ደብዳቤ በአልጋ ወራሹ ቤት ለብሪታንያዋ ንግሥት አጎት ልጅ (የግሎስተር ልዑል ሚካኤል)በተዘጋጀ የራት ግብዣ ሰበብ አስፋ ወሰን እና ሮበርት ራሰል በምሥጢር ያካሄዱትን ከሁለት ሰዓት በላይ የፈጀ ውይይት የሚዘግብ ነው።

ውይይታቸው በብዙ ርዕሶች ላይ ያተኮረ ቢሆንም፤ አልጋ ወራሹ በቅርቡ አዲስ አበባ ላይ ተካሂዶ የነበረውን ስብሰባ እና ንጉሠ ነገሥቱ እያደር ያፈሩት ዓለም አቀፋዊ ዝና የአቋማቸውን ትክክለኝነት እያደር የሚጠናክርላቸው ስለሆነ ምንም ዓይነት ለውጥ ላለማምጣት ያላቸውን አቋም ያጠናክረዋል። ሆኖም፤ ይላሉ አልጋ ወራሽ፣ የአዲሶቹን አፍሪቃውያን የእኩልነታዊ ነፃነት (liberal) የሚመለከቱት እና በቅርቡ ክዳኑ የተጠረቀምባቸው የተቃውሞ ኃይሎች አዲስ ትንፋሽ ስለሚያገኙ የንጉሠ ነገሥቱ አቋም መዳከሙ አይቀርም ይላሉ።

አምባሳዶሩ በአድናቆት አዳመጥኩ ካሏቸው አንዱ ስለ ታኅሣሥ ፶፫ቱ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከር ሲሆን፤ አልጋ ሚዛናዊ በሆነ አመለካከት፤ ያለምንም ስሜት «ልክ ከውጭ ሆኖ ወደውስጥ እንደሚመለከት የውጭ ጋዜጠኛ እንጂ በእውነቱ ግን እንደጉዳዩ ባለቤትነታቸውና የክስተቱ እምብርት በመሆናቸው ብዙ ውዝግብ እንዳስከተሉ ዋና ተዋናይ አልነበረም።» ይላሉ

ታዲያ በአስፋ ወሰን አመለካከት «ጠንሳሾቹ ሰፊ ድጋፍም ሆነ የፖለቲካ ድርጅት ከኋላቸው አልነበረም፤ ሆኖም ትልቅ የፖለቲካ አስተሳሰብ እና ሕገ መንግሥታዊ ምኞትን የወከሉ ነበሩ። የመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ የተሳካ ቢሆን ኖሮ፤ በአገሪቱ በፖለቲካ የነቃውን የአገሪቱን አካል ፍላጎት ይሟላ ነበር» ባይ ናቸው። አምባሳዶሩ ታዲያ በዚያ ዓመጽ የእሳቸው ሚና ምን እንደነበር ለመጠየቅ የነበራቸውን ከፍተኛ ውስጣዊ ግፊት «እንደምን ብዬ አስታገስኩት» ብለው ዘግበዋል።

ከዚህ የተከተለው ጉዳይ አምባሳዶሩ «እኔ ሳላነሳባቸው እራሳቸው በቅርቡ አባታቸው ዘንድ ቀርቦ ስለነበረው ተልዕኮ ያወጉኝ ጀመር» ሲሉ ይጀምሩና፤ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንቱ ልዑል ደጃዝማች አስራተ ካሣ፤ የመከላከያ ሚኒስትሩ ጄኔራል መርዕድ መንገሻ እና የኤርትራ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴው ጄኔራል አቢይ አበበ በአንድነት ሆነው፤ ሚኒስትሮቹ ሥልጣን እንዲለቀቅላቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማው የተመረጠ እንዲሆን እና ፓርላማው እራሱ ሕገ መንግሥታዊ እና ሕግ የማወጅ ሥልጣን እንዲሰጠው የሚሉ ጥያቄዎችን ይዘው ሲቀርቡ፤ መጀመሪያ ንጉሠ ነገሥቱ ለንደዚህ ዓይነት ግፊት በመዳረጋቸው በጣም ተቆጥተው እንደነበር ይናገሩና ጥያቄዎቹን በጥሞና ከተመለከቷቸው በኋላ ግን ወደነሱ አቋም እየቀረቡ መምጣት ጀምረው ነበር ብልዋል።

እንግዲህ እንደምናውቀው ንጉሠ ነገሥቱ እነዚህን ተጠየቁ የተባሏቸውን ሦስት መሠረታዊ ጥያቄዎች ሳይመልሱ ለሦስት ዓመታት ካዘገዩ በኋላ፤ ምንም እንኳን ምክንያቱ በነዚሁ ባለፉት ሦስት ዓመታት በአፍሪቃ አኅጉር አሥር የተሳኩ መፈንቅለ መንግሥት መካሄዳቸውን በመንገንዘብ ሊሆን ቢችልም፤ መጋቢት ፲፫ ቀን ፲፱፻፶፰ / በቴሌቪዥን ያስተላለፉት ንግግር  ላይ ወደፊት ሚኒስትሮችን የሚመርጠውና የሚያሾመው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሆንና የሚኒስትሮቹም ምክር ቤት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ እንደሚሆን ይፋ አደረጉ። ፓርላማውን ግን ሕገ መንግሥታዊ እንዲሆን፤  ሕግ የማወጅ ሥልጣን እንዲሰጠው እና የአስተዳደሩ ተጠያቂነት ለፓርላማው እንዲሆን የቀረቡትን ጥያቄዎች ንጉሠ ነገሥቱ «ፓርላማው ለዚህ የሚያበቃ ብሥለት ገና የለውም» በሚል ምክንያት ሳይለወጥ እንዲቆይ ወሰኑ። ይሄንን የአባታቸውን ደረቅ አቋም ለብሪታኒያው አምባሳዶር ያወገዙት አልጋ ወራሽ እርምጃው ለወደፊቱ የሳቸው የሕገ መንግሥታዊ የዘውድ መንግሥት የተመቸ እንደሚሆንም ነግረዋቸዋል። 

ይሄንኑም እርምጃ የሚያረጋግጥና ሕጋዊ መሠረት የሚሰጠው አዋጅ ሐምሌ ቀን ፲፱፻፶፰ / ነጋሪት ጋዜጣ ትእዛዝ ቁጥር ፵፮/፲፱፻፶፰  (የ፲፱፻፶፰ / የሚኒስትሮች ሥልጣንና ተግባር (ማሻሻያ ቁጥር ) ትእዛዝ ) በሚል ይፋ ሆነ።

በዚህ ጊዜ ግን ከአምሣ-ሦስቱ ሙከራ ጀምሮ ለውጥን በተመለከተ  ንጉሠ ነገሥቱን አጥብቀው ይገፋሉ ከሚባሉት ሦስት ሰዎች መኻል፣ጄኔራል መርዕድ መንገሻ በሞት ተለይተዋል፤ ደጃዝማች አስራተ ካሣም ልዑል ራስ ተብለው በኤርትራ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ ሆነዋል። ብቻቸውን የቀሩት ጄነራል አቢይ አበበ ነበሩ።

እንግዲህ መርዕድ አዝማች አስፋ ወሰን ኃይለ ሥላሴ፤ በብዙ ዘመናት ያዳበሩትንና በገሃድ የሚታየውን ለስላሳ፤ ዓይናፋር፤ ወላዋይ ባህሪያቸውን ሳይለውጡ የአባታቸው ፍቅር የራቃቸው ስለሆኑም የሰፊውን ሕዝብ ኀዘኔታ ተጎናጽፈው ሲኖሩ ባላታወቀ ሁኔታና የሰው እጅ ይኖርበታል የሚል ሐሜታ ባልራቀው ምክንያት ጥር ፲፱ ቀን ፲፱፻፷፭ / በደም ቋጠሮ ምት ታመው በማግሥቱ በአስቸኳይ በእንግሊዝ የጦር አየር ዠበብ ተሣፍረው ለሕክምና ወደ እንግሊዝ አገር ተወሰዱ። ያን ዕለት የኢትዮጵያን ምድር በሕይወት እንደለቀቁ ቀርተው በስደት ላይ እያሉ ሞት ቀድሟቸዋል።  ኢትዮጵያም እሳቸው በወጡ በዓመቱ የአብዮት አገር ስትሆንና አባታቸውም ከዙፋኑ ሲወርዱ፤ ዕድሜ ልካቸውን የጓጉለትን እና ምናልባትም አባትና ልጅን እስከዘላለሙ ያቆራረጣቸው የሁለቱም የሥልጣን ጥም ሳይረካላቸው ቀርተዋል።



[1] Spencer, John H; “Ethiopia at Bay: A Personal Account of the Haile Selassie Years”; Tsehai Publishers (January 1, 2006)
[2] P.R.O.: VA 1015/17 Wright, D.A.; “Turn of Events in Ethiopia”; Wright to Earl of Home; A.A. Despatch No 13 (1016); (March 30, 1961)
[3] P.R.O.,[VA1015/37]; M.G.L. Joy - AA to John G.S. Beith - NEAD, FO (August 5, 1961)
[4] P.R.O.,[VA1015/39/G]; M.G.L. Joy – AA to John G.S. Beith – NEAD, FO(August 19, 1961)
[5] Arthur L. Richards, a former United States Ambassador to Ethiopia (June 24, 1960 - November 25, 1962)    http://www.nytimes.com/1991/02/26/obituaries/arthur-l-richards-diplomat-83.html 
[6] P.R.O.; [VA1015/40] Cypher No. 455; Joy – AA to FO (August 30, 1961)
[7] P.R.O.; [VA1941/7]; Russell to Earl of Home; AA Despatch No. 43 (1016/63) of July 31, 1963

1 comment:

  1. Wow! Never knew. Interesting story. Will read back post and learn more. Good Job!

    Kimemen.

    ReplyDelete

እርስዎስ ምን ይላሉ?