Thursday 27 June 2013

ሚካኤል (ወልቃይቴ) ብሩ እና ዳውቲ-ዋይሊ

ሚካኤል (ወልቃይቴ) ብሩ እና ዳውቲ-ዋይሊ
የብሪታኒያው ዋና መላክተኛና ባልደረባዎቹ አዲስ አበባ ላይ የተደበደቡ ዕለት።

ዚህ ትረካ ደራሲ ከዚህ በፊት “የየዋሖቹ ዘመን” ባልኩት ጽሑፌ መተዋወቃችንን ለማስትወስ ያህል፤ በዕምዬ ምኒልክ ዘመን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በቅሎው እሰው ማሳ ውስጥ ይገባና የአቅሙን ያህል የጤፍ እሸት አጋበሶ ከዋጠ በኋላ የተፈጥሮው ግዳጅ ቢሆንበት፣ በቀረው ሰብል ላይ እየተንከባለለ መዥገር ማላቀቂያ አድርጎ ያወድመዋል። ኦሮምኛ ተናጋሪው የማሳው ባለቤት  ታዲያ የካሣውን አሞሌ ጨው ቢጠይቅ የቋንቋ አለመግባባት ሆነና፤ ከማሳው ጠቅላላ ምርት ግምት በላይ ከአንድ ብር ሁለት ብር፤ ሦስት ብር፣ አራት ብር ቢከፈለው  ጊዜ በቅሎውን እንደልቡ እንዲሰድበት መነገሩን ያጫወተን ሻለቃ ሄንሪ ዳርሊ መሆኑን ከወዲሁ አንባቢ ይገንዘብልኝ!


የዛሬውም ዘገባ በዚያው 'ባሪያዎችና የዝሆን ጥርስ' (Slaves & Ivory (1926)) ብሎ በሠየመው መጽሐፉ ላይ ያሰፈረው ሌላው አስቂኝ ነው። ታዲያ ይኼ ዘገባ የአንድ ኢትዮጵያዊና የአንድ እንግሊዛዊ ሰውን ታሪክ በአጭሩ ለመዳሰስ እንድሞክር ረድቶኛል።


ሻለቃ ዳርሊ በዚህ መጽሐፉ ትቶልን ያለፈው የዛሬው አስቂኝ ሁኔታ የተዘገበው ከምኒልክ ሕልፈት በኋላ (በህመማቸውም ጊዜ ሊሆንም ይችላል!) የልጅ ኢያሱ ዘመነ ሥልጣን መግቢያው ላይ ሲሆን ለብዙ ዘመናትም የብሪታኒያ ዋና መላክተኛ የነበረው ሰር ጆን ሌን ሃሪንግቶን —ቀኛዝማች ወልደ ገብርኤልን ሰደቡኝ ብሎ ያሥገረፋቸው መኾኑን አንባቢ ልብ ይሏል — በሁለተኛው ዋና መላክተኛ ሰር ዊልፍረድ ቴሲገር ከተተካ በኋላ መሆኑ ነው። ታዲያ በዳርሊ መጽሐፍ ገጽ 114 እና 115 ላይ የሚገለጽልን፤ አዲሱ መንግሥት የምኒልክን መኳንንት እያገለለ እንደሆነና ከነዚህም መኻል ሽማግሌው ራስ-ቢትወደድ መንገሻ አቲከም አንዱ እንደነበሩ ነው።

ዳርሊ አሽከሮቹን እና ንብረቱን ወደተወበት ወደማጂ ለመሄድ ከብሪታኒያው ሌጋሲዮን ፈቃድ እየተጠባበቀ አዲስ አበባ በከረመበት ወቅት ካየዃቸውና ከሰማዃቸው ከሚላቸው አንዳንድ ነገሮች፡—
«ከዕለታት አንድ ቀን ራስ መንገሻ አቲከም ባንክ መጥተው ሻይ ቡና ተብለው ሲጫወቱ ከዋሉ በኋላ ሲመሻሽ አሽከሮቻቸውን አስከትለው ወደቤታቸው ሲያመሩ አየሁ።» የሚለን ዳርሊ «በማግሥቱ ከግቢያቸው በትልቅ አጀብ እሬሣ ወደመቃብር ሲወሰድ አይቼ የሟችን ማንነት ሳጠያይቅ ለብዙ ጊዜ ታመው የነበሩት ራስ መንገሻ እንደሆኑ ተረዳሁ» ይላል። ኾኖም ሞቱ የተባለው በማጅራት ገትር (cerebral meningitis) ቢሆንም የዳርሊ ድምዳሜ ራስ ቢትወደድ ለፈጣን ሞት የተዳረጉት በሻይ ቡና ተመርዘው ነው የሚል ነው።

በዚሁ ወቅት ለብዙ ዘመናት በብሪታኒያ ሌጋሲዮን በአስተርጓሚነት ተቀጥሮ ይሠራ የነበረ አበሻ «የአገሪቱን ንግድ ጨብጠው ይቆጣጠሩ ከነበሩት የቦምቤይ ባንያኖች ጋር አጠራጣሪ ግንኙነት አለው ተብሎ ከሥራው እንዲባረር ተደረገ» ይልና የዳርሊ ዘገባ፣ «ይሄ ሰው በብሪታኒያዎቹ ተቀጥሮ ለብዙ ዘመናት ያገለገለ ስለነበር ከሥራ በመባረሩ እጅግ በጣም ተበሳጨ። ታዲያ በሌጋሲዮኑ ግቢ ይኖር የነበረው ይሄ አስተርጓሚ ቤቱን የለቀቀ ምሽት ተከታዮቹ (አሽከሮቹ) በጣም ሰከሩና ግቢውን መበጥበጥ ጀመሩ።» በሚል የጠቡን ምንጭና ሂደት ካበሰረን በኋላ፣ ዳርሊ ቀጥሎ «ከጥቂት ጊዜ በኋላ የተንኮል ድርጊት ለማካሄድ የተነሳሱት ሰካራሞች የዋና መላክተኛውን ቅጥር ግቢ ጥሰው ይገቡና ቆንስላውንና ምክትሉን አናት አናታቸውን በዱላ ውርጅብኝ ቀጥቅጠው  ዘረሯቸው።» ይለናል። «ጡንቸኛውና ኃይለኛው ዋና መላክተኛ ግን አምሥቱን በቡጢ በመዝረር ከጉዳት ሊድን ችሏል።» ይላል ሻለቃው። «‘ስለተከበረው የራስ መከላከያ ጥበብ’ (the noble art of self-defence ይለዋል —ቦክስ ማለቱ ነው) ምንም የማያውቁት አበሾች ወሬው ሲሰማ የዋናውን መላክተኛ ጀግንነት እጅግ በጣም አደነቁ።» ብሎ አስፍሮታል።

እንግዲህ ይሄንን ዘገባ ሳነብ ሁኔታው እንደመድረክ ትዕይንት እየታየኝ ያስቀኛል። በዓይነ ልቦናዬ የሚታየኝ  ታዲያ ያንን አስተርጓሚ ከሥራው ሲያባርሩት ደሞዙንም ሆነ ማናቸውንም ክፍያውን (ወጭም፣ ካሣራም ሊሆን ይችላል) ሰጥተው
ነው። እሱም በተራው የራሱን ተከታዮችና አሽከሮች እንዲሁ ሂሣባቸውን ሳይሰጥ አልቀረም። ምናልባት በዓመት የሚያገኙትን በአንድ ጊዜ ሲቀበሉ የማርያ ጠሬዛውን ክብደት ለማቅለል ከአንዷ የሾላ ሠፈር 'ሞኝ አንግሥ' ማንቆርቆሪያ ቤት ጎራ ብለው ሲቀመቅሙ ውለዋል። ታዲያ “ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል” እንደሚባለው ለጋሲዮኑ ግቢ  ሲደርሱ “የዕለት እንጅራችንን ያሳጣን” ነው ብለው ያመኑትን ቆንስላ፣ ሻለቃ (በኋላ ሌፍተናንት-ኮሎነል) ቻርልስ ዳውቲ-ዋይሊን ሲያገኙት የእንክርዳድ እንፋሎት እና የአጋም ሥር ሽመል ባዋሳቸው ጊዜያዊ ልበ-ሙሉነት አናት አናቱን ይቀጠቅጣሉ። ይሄኔ ሊደርሱለት የመጡት ምክትሉና አለቃው ግብ-ግቡን ተቀላቅለው አንዱ ሲቸነፍ ሌላው በቡጢ አፍንጫቸውን እያስነጠሰ፣ ዓይናቸውን እያሳበጠ፣ ጥርሳቸውን እያወላለቀ ዘረራቸውና ድሉ ላልሰከሩት ነጮች ሆነ። ጉድ እኮ ነው!

            ይሄንን ትዕይንት በአዕምሮዬ ሳመላልስ የጥርሴ ወገብ እስከሚንቀጠቀጥና ሆዴን እስከሚያመኝ ከሳቅሁ በኋላ ዋና ዋና ተዋንያኑ እነማን ነበሩ ወደሚለው ጥያቄ ማምራቴ አልቀረም። አንባቢም የዚሁኑ መልስ ለማግኘት ጉጉት እንደያዘሽ/ህ ተስፋ በማድረግ እስኪ ወደዚያው እናምራ።

ከልዩ ልዩ የታሪክ ዘገባዎች እንደምንገነዘበው በሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን በብሪታኒያው ሌጋሲዮን በአስተርጓሚነት ተቀጥረው ከሚያገለግሉት ሰዎች መኻል የአንድ ኢትዮጵያዊ ሰው ስም — ሻለቃው ባይነግረንም — በታሪክ አውሎ ነፋስ እየትምዠገዥገ ብቅ ይልልናል። ይሄ ሰው አባቱም በመቅደላ ዘመቻ ጊዜ ናፒዬርን በአስተርጓሚነት ካገለገሉት  አንዱ የነበሩት እና በማልታ የተማሩት የአቶ ብሩ (ወልቃይቴው) ጴጥሮስ ልጅ አቶ ሚካኤል ብሩ ነው።  ከመቅደላ እስረኞች አንዱ የነበሩት ሚሲዮናዊው አቶ ዋልድማየር በቤይሩት በመሠረቱት ኢየሱሳዊ ትምህርት ቤት ነበር ሚካኤል (ወልቃይቴው)  ብሩ የተማረው።

አባትዬው በዓፄ ዮሐንስም ዘመን ውል ለመፈራረም የመጣውን አድሚራል ሂዊት በአስተርጓሚነት እንዳገለገሉ ከመዘገቡም ባሻገር በምጽዋ የዓፄ ዮሐንስ ወኪል ሆነው ሲሠሩ ምስንጅር (ሙንዚንገር) ይዞ እንደገረፋቸው ንጉሠ ነገሥቱ በአደን የእንግሊዝ የፖለቲካ ሹም ለነበረው ጄኔራል ሽናይደር በጻፉት ደብዳቤ ላይ ተዘግቧል።[1]

አቶ ሚካኤልን በአስተርጓሚነት የቀጠረው በኢትዮጵያ የብሪታኒያ የመጀመሪያው ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴና ወኪል የነበረው ሌፍተናንት ኮሎኔል ጆን ሌን ሃሪንግቶን ሲሆን፤  ሁለቱ መጀመሪያ የተዋወቁት አደን ላይ ነበር። ሃሪንግቶን ወደኢትዮጵያ ከመላኩ በፊት በአደን የብሪታኒያ ወኪል የነበረ ጊዜ በአስተርጓሚነት ቀጥሮት ነበር። በኋላም በአዲስ አበባው ሌጋሲዮን በዚሁ ሥራ መድቦት ሲያገለግል ቆይቷል።  ነሐሴ ፫ ቀን ፲፰፻፺፬ ዓመተ ምሕረት በተከናወነውም የንጉሥ ኤድዋርድ ሰባተኛ የንግሥ በዓል ላይ ለመሳተፍ ወደሎንዶን ያመሩትን ልዑል ራስ መኮንንን አጅበው ሁለቱም ብሪታኒያ መጥተው ነበር።

በዚሁ በሎንዶኑ ቆይታው ጊዜ በብሪታኒያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሎርድ ላንድስዳውን ፍላጎትታማኝና ታታሪ
ራስ መኮንን በሎንዶን - ሃሪንግቶን ከራስ መኮንን በስተቀኝ የተቀመጠው ሲሆን ሚካኤል ብሩ ደግሞ ከቆሙት ከግራ ሁለተኛው ነው
ለተባለው አስተርጓሚ፤ እንዲሁም በቅርቡ በኢትዮጵያና የብሪታኒያ ሱዳን መንግሥታት መኻል ለተፈረመው የድንበር ስምምነትትልቅ አስተዋጽዖላስመዘገበው እና በአዲስ አበባው ሌጋሲዮን በየወሩ አሥራ-ሦስት የእንግሊዝ ፓውንድ ደሞዝ ከመኖሪያ ቤት ጋር ለሚከፈለው አቶ ሚካኤል ብሩ የሃምሣ ፓውንድ ጉርሻ እንዲሰጥ የሚያመለክት ደብዳቤ በሎንዶኑ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብት ይገኛል።[2]

እንግዲህ ከላይ እንደተገነዘብነው ሰር ጆን ሌን ሃሪንግቶን እና ባልደረቦቹ የሥራ ጊዜያቸውን ፈጽመው በሌሎች ባለ-ሥልጣናት ሲተኩ በአዲስ አበባው የብሪታኒያ ሌጋሲዮን ለብዙ ዘመናት ሲያገለግል የቆየው አቶ ሚካኤል ብሩ ለነዚህ ለመጤዎቹ አገር አለማማጅና ወደኋላም የ’መቀመጫቸው ቁስል’ ሊሆንባቸው እንደሚችል መገመት ይቻላል። ታዲያ የበላይነታቸውንም ማስረገጫ፤  እከካቸውንም ማስታገሻ የሚሆናቸው መፍትሔ ሚካኤል ብሩን በወንጀል ሰበብ ቀርፎ መጣል ሊሆን እንደሚችልም መገንዘብ አያዳግትም። ቆፍጣናው አበሻ ታዲያ ያለጦርነት እጁን አይሰጥምና የሰፈሩን ዱርዬ ሁላ አረቄ ከጋተ በኋላ ፍልሚያውን ከፈቱ ባይ ነኝ።

የሁለተኛው ተዋናይም የሕይወት ታሪክ ውስብስብ እና ምሥጢራዊ ሊሆን የቻለበትን ምክንያት ሁለትና ሁለት ሲደመር አራት ይሆናል (አምስት ከሆነ ተረት ተረት ብቻ ነው የሚሆነውና!) የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስ ለሚችል የታሪክ
ሌፍተናንት ኮሎኔል) ቻርልስ ሆታም ሞንታግዩ ዳውቲ-ዋይሊ
ተመራማሪ ቀልብ የሚስብ ጉዳይ  ይሆናል። ይሄ ሰው በወቅቱ ሻለቃ (በኋላ ሌፍተናንት ኮሎኔል) ቻርልስ ሆታም ሞንታግዩ ዳውቲ-ዋይሊ ይባላል። ለአዲስ አበባው ሌጋሲዮን ዋናው መላክተኛ (ሻምበል ዊልፍረድ ጊልበርት ቴሲገር) ነሐሴ ፳፮ ቀን ፲፱፻፩ ዓ/ም ከተሾመ በኋላ በሦስተኛው ወር ዳውቲ-ዋይሊ ደግሞ ቆንስላ ሆኖ በሥሩ እንዲያገለግል በብሪታኒያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተሾመው ኅዳር ፳፪ ቀን ፲፱፻፪ ዓ/ም ነበር።[3] 

ስለዳውቲ-ዋይሊ ከሚገርሙት ሐቆች የመጀመሪያው፤ ዋይሊ የሚለውን የስሙ ቅጽል በታኅሣሥ ወር ፲፰፻፺፮ በሕግ የወረሰው ሲሆን ከስድስት ወር በፊት ያገባት የሚስቱ የቤተ-ሰብ ስም ነው። እንግዲህ እንደአውሮፓውያን ተለምዶ ሚስት የባሏን የቤተ-ሰብ ስም ትወርሳለች እንጂ ባል የሚስትን ስም የመወርስ (በተለይም በአሥራ-ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን)ጉዳይ ያልተለመደ ሁኔታ ነው።
በመስከረም ወር ፲፰፻፺፱ ዓ/ም ኮኒያ በሚባለው የቱርክ ጠቅላይ ግዛት የብሪታኒያ ወታደራዊ ቆንስላ ሆኖ ተሹሞ በሚሠራበት ወቅት ገርትሩድ ቤል የተባለችን የሥነ-ቅርስ ባለሙያ (archaeologist) ሴት ወሽሞ ምሥጢራዊ  የፍቅር ደብዳቤዎች ይለዋወጡ እንደነበር ተዘግቧል። ከዚህ ምድቡ በኋላ ነው እንግዲህ ወደአዲስ አበባ በቆንስላነት ተሹሞ የሄደው።

አዲስ አበባ ለሦስት ዓመታት ከቆየ በኋላ ከሚስቱ ጋር ወደቁስጥንጥንያ ተዛውሮ በቱርኮች ወገን የቀይ መስቀል ዲሬክቶር ሆኖ በመጀመሪያው የባልካን ጦርነት ላይ አገልግሎ በዓመቱ በ፲፱፻፭ ዓ/ም እንደገና ወደአዲስ አበባ ተመለሰ። እዚያው ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ ለመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወደቱርክ በተመለሰ በሦስተኛው ወር፤ ሚያዝያ ፲፰ ቀን ፲፱፻፯ ዓ/ም በውጊያ ላይ ሞቶ እዚያው ተቀብሯል።

ከላይ እንደተዘገበው ዊልፍረድ ጊልበርት ቴሲገር  የብሪታኒያ ዋና መላክተኛ ሆኖ የተሾመው ነሐሴ ፳፮ ቀን ፲፱፻፩ ዓ/ም ሲሆን ከአሥራ አንድ ቀናት በፊት ነሐሴ  ፲፭ ቀን ያገባትን ሚስቱን ካተሊን ሜሪ ቪገርስን ይዞ አዲስ አበባ የገባው በታኅሣሥ ወር ፲፱፻፪ ዓ/ም ነበር። የመጀመሪያ ልጃቸው ዊልፍረድ ፓትሪክ ቴሲገር ግንቦት ፳፮ ቀን ፲፱፻፪ ዓ/ም፤ ተከታዩ ልጃቸው ብራያን-ፒርሰን ደግሞ መስከረም ፳፫ ቀን ፲፱፻፬ ዓ/ም እዚያው አዲስ አበባ ለጋሲዮን ነው የተወለዱት።[4]

ሁለተኛው አስገራሚ ነገር ታዲያ ብራያን-ፒርሰን መስከረም ፲፮ ቀን ፲፱፻፳፮ ዓ/ም ቴሲገር የተባለውን  የቤተ-ሰብ ስሙን በሕግ አስለውጦ ብራያን-ፒርሰን ዳውቲ-ዋይሊ መባሉ ነው።[5] በተወለደ ሃያ-ሁለት ዓመቱ፤ የስሙ ባለቤት ቻርልስ ሆታም ሞንታግዩ ዳውቲ-ዋይሊ በሞተ በአሥራ-ዘጠኝ ዓመቱ እና አባቱ ዊልፍረድ ጊልበርት ቴሲገር በሞተ በአሥራ-አራት ዓመቱ ስሙን ሊለውጥ የበቃው በምን ምክንያት ይሆን ? ሃያ-አንድ ዓመት እስኪሞላው ድረስ ስሙን በፈቃዱ ለመለወጥ ሕግ እንደማይፍቅድለት ብንገነዘብም፣ ለመለወጥ ያነሳሳው ምክንያት ግን አስገራሚና ያልተገለጸ ታሪክ ነው። የዚህን ምሥጢር መልስ ሳሰላስልም ታዲያ ቻርልስ ሆታም ሞንታግዩ ዳውቲ-ዋይሊ  ይሄ ልጅ የተወለደ ጊዜ ለምን ተነስቶ ወደቱርክ ሄደ ? እንዴትስ የቱርኮች የቀይ መስቀል ዲሬክቶር ለመሆን በቃ ? እናቱ ባሏ ዊልፍረድ ጊልበርት ቴሲገር ከሞተ ከአሥራ-አንድ ዓመት በኋላ ሁለተኛ ባሏን በ፲፱፻፳፬ ዓ/ም አግብታለች።  ምናልባት ከባሏና ዋና የብሪታንያ መላክተኛ ከነበረው የተደበቀ የቤተ-ሰብ ምሥጢር ልጇ ብራያን-ፒርሰን ለአቅመ አዳም ሲደርስ ገልጻለት ይሆን ? ወይስ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ነው ?




[1] Rubenson, Sven; ACTA ÆTHIOPICA, VOL III: Internal Rivalries & Foreign Threats 1869-1879; Addis Ababa University Press (2000); page 128
[2] PRO; FO 01/40; FO to Treasury dated July 31st, 1902; Abyssinia (Diplomatic, Consular, Comercial & Treaty) 1902
[3] THE LONDON GAZETTE No. 28339, (FEBRUARY 15, 1910);  page 1124

[4] Maitland, Alexander; Wilfred Thesiger: A Life in Pictures; Harper Collins Publishers (2004); page 11

[5] THE LONDON GAZETTE,[33982] 29 SEPTEMBER, 1933 Page 6323

No comments:

Post a Comment

እርስዎስ ምን ይላሉ?