Wednesday 19 June 2013

የቡድን ስምንት ወጥ ቀማሽ

«የቡድን ስምንት መሪዎች መለስ ዜናዊን የሚተካ ወጥ ቀማሽ እያፈላለጉ ነው» ተባለ።

ይመኩ ታምራት

ከአዲስ አበባ ዕሮብ ሰኔ ፭ ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ተነስተው ቻይና ከመግባታቸው በፊት ለጢያራቸውም  ለተከታዮቻቸውም እህል ውሀ ለማለት ሳይሆን አይቀርም፤ የባንግላዴሽ ዋና ከተማ ከሚገኘው ‘ሀዝራት ሻሃጃላል ጢያራ ጣቢያ’ አረፍ ብለው ነበር። በማግሥቱ የቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኬቂያንግ ጥያራ ጣቢያ ተገኝተው ተቀበሏቸው። ዓርብ ደግሞ ከአዲሱ የቻይና ፕሬዚደንት ጋር ውይይት አደረጉ። ቅዳሜን እዚያው ውለው አድረው እሑድ ከአገር ወደተነሱበት ቁም ነገር ለመመለስ ወደሎንዶን ‘ስታንስተድ’ ጥይራ ጣቢያ አመሩ። የሎንዶኑ አቀባበል ከቤይጂንጉ የላቀ ይሁን የደበዘዘ የምናውቀው መረጃ የለንም።


በነገራችን ላይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤ የጉዞዎ ዓላማ ግልጽ ላልሆነለትም ለተገለጸለትም ዜጋ እንኳን ቢሆን ከሰማይ-ጋሪዎ ሲወርዱ እና በክብር እንግዳነት አቀባበል ሲደረግልዎ ኮትዎ (እንደአገሬ ሰው ከክተቱበት ድብኝት ውስጥ ያወጡት ይመስል)  ላልጠፋ መተኮሻ፤ እንደዚያ ተጨማዶ መታየቱ አሳፍሮናልና ያወጣውን ያውጣ (ግዴለም እንከፍላለን እሺ!) ትንሽ ባለንፋሎት ካውያ ይገዛና ለወደፊቱ ሽክ ብለው አስተናጋጆችዎን ሰላም ይበሉ!ዞሮ ዞሮ ለኛው ክብር ነውና። ያለመታደል ሆነና ነው እንጂ አስተዋይ አማካሪ ቢኖርማ እዚያው ቻይና ውስጥ ካውያው ለኛም ቀለል በሚል በትንሽ ዋጋ ይገኝ ነበር። ይልቁንም ለቻይናዎቹ ሹክ ቢባል ኖሮማ በስጦታ መልክ ልርስዎ ብቻ ሳይሆን ለያንዳንዱ ተከታይ ትሰጥ ነበር። (አሃ! ለካ ደሞ የአገር ቤት ፓርላማ ስጦታ ማስመዝገብ የሚሉ ፋይዳ አምጥቷል አሉ! ወይ የኔ ነገር፣ ጉድ ላደርግዎ ኖሯል።)

ታዲያ ወደሎንዶን ያመሩት ለካ የቡድን ስምንት ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ/ወይስ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ቋሚ ሥራ ለመሥራት ኖሯል። የአሜሪካው ፕሬዚደንት እንደው የጨዋ ወግ ሆነባቸውና ጠጋ ብለው ሰላም ቢሏቸው የገጠማቸውን ፍዳ ፎቶው በሚገባ ያስተጋባዋል።

አቶ ኃይለ ማርያም ከታሪክ በመነሳት ነው የኦባማን ጆሮ ለመቀብደድ የሞከሩት።

«የዛሬን አያርገውና» በማለት ጀመሩ፤ «ጥንታዊት በሆነችው ባለታሪኳ አገሬ፤ የንጉሡን ወጥ የሚቀምሰው ሎሌ በተራው ዜጋ ታዝኖለት፤ በተንኮለኛ መሳፍንቱ ተጠልቶ፤ በአድር-ባይ መኳንንቱ ተመስግኖ የሚኖርና አንዳንዴም ውቃቢው የሸሸው ዕለት ከንጉሡ ቀድሞ አፉ ያስገባው ወጥ አንጀቱ ሳይደርስ ጉሮሮውን እንቅ አርጎ ዘግቶ፤ ከቁጥጥሩ ያለፈ አረፋ ዘፍቆት ተንፈራፍሮ የተሰናበተ እንደሆነም በድኑን አንስቶ ስድስት ክንድ ጉድጓድ ውስጥ የሚወሽቀው ወገን ማግኘቱም አጠራጣሪ ነበር።» ብለው ሲጀምሩ ኦባማ ጉዳዩ ስላልገባቸው ግራ ግብት እንዳላቸው የተገነዘቡት አቶ ኃይለ ማርያም ቀጠል አረጉና፣ «የቡድን ስምንትንም ጽንሰ-ኃሣብ ለዓለም ያበረከተችው ኢትዮጵያ ነበረች!» የሚል ዱብ-ዕዳ ጣል አደረጉ።

ኦባማ ታዲያ በሆዳቸው፤ “አይ አሁንስ አበዛብኝ” የሚላቸውን ስሜት እንደሸሸጉ አረፍት-ነገሩ ግን በዋዛ እንዳይታለፍ፤ «ክቡርነትዎ የቡድን ስምንት ጽንሰ-ኃሣብ መሥራች ኢትዮጵያ ነች ሲሉ፣ እንዴት እንደሆነ ቢያብራሩልኝ!» በሚል ትኅትና በተላበስ  ሹፈት ጠየቁ።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ታዲያ፣ መበረታቻው ተገኝቶ ነው?  «ክቡር ፕሬዚደንት!  መቸም የአገሬ ዋና መሪዎች ንጉሠ ነገሥት ይባሉ እንደነበር ከታሪክ እንደሚገነዘቡት ጥርጣሬ የለኝም። ታዲያ ይኼንን መጠሪያ ያገኙት የጎጃም ንጉሥ፤ የሺዋ ንጉሥ፤ የከፋ ነጉሥ፤ የአዳል ንጉሥ፤ የባህር ነጋሽ፤ የወላይታ ንጉሥ እና የወሎ ንጉሥ በውስጣቸው ሆነው ይገብሩላቸው ስለነበረ ነው። ንጉሠ ነገሥቱ ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ እነኚህን ንጉሦች ወደርዕሰ ከተማው ይጠራና የመላ አገሪቱን የፖለቲካዊ፣ የምጣኔ ሃብት እና የሃይማኖታዊ ይዘቶች ያማክር ነበር። እግረ መንገዱንም የበላይነቱን ግብር (ወይም ቀረጥ) ይቀበላቸው ነበር።» በሚል የኦባማን ቀልብ ከሳቡ በኋላ ማብራሪያቸውን ቀጠሉ።

«ለምሣሌ» አሉ አቶ ኃይለ ማርያም፤ «በምጣኔ ሃብት ረገድ የሁሉም መገበያያ የነበረውን የጠገራ ብር ምንዛሬ በአሞሌ ጨው እና በጥይት መጠኑን ተወያይተው ይተምኑ ነበር። (በአሁኑ ጊዜ ባርተሮኖሚክስ እንዲሉ!)» «በአሥራ-ዘጠነኛው መቶ ክፍለ-ዘመን ታዲያ አገር ለመዳሰስና በምሥጢርም ለማቦጫጨቅ (ለመቦጫጨቅም) ይገቡ ከነበሩት አውሮፓውያን መኻል አንዳንዶቹ የዚህን የኢትዮጵያ ሰባት ንጉሦች እና የዓለቃቸውን ዓመታዊ ስብሰባ አመሠራረት፣ ሂደት፣ አጀንዳ፣ ውሳኔ፣ ትግበራ፣ ወዘተ በጥልቀት ካጠኑ በኋላ ሃሣቡን በመቀማት የራሳቸው አድርገውት ይሄው እስካሁኑ ዘመናችን ድረስ ሊዘልቅ ችሏል።» በማለት ተንተን አድርገው አስረዱ።

ኦባማ ታዲያ አቶ ኃይለማርያም ስለ ቡድን ስምንት አመጣጥ ስለሰጧቸው ትምህርት ካመሰገኑ በኋላ፤ ሰባቱን መሪዎች አማክረው ከምሣ በኋላ ያላቸው ጊዜ የሚፈቅድ ከሆነ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እራሳቸው ስብሰባው ላይ ቀርበው እንዲያስረዱ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ቃል ገቡ። ሆኖም ከስብሰባው በኋላ መሪዎቹ በጋራ ካወጡት መግለጫ እንደተረዳነው፣ የሩሲያው ፑቲን በሶርያ ላይ ይወሰድ የተባለውን እርምጃ በብርቱ በመቃወም ያቀረቡት ግትር አቋማቸው ምክንያት ሌላ የውይይት ርዕስ ለማቅረብ አለመቻሉን ተገንዝበነዋል። ፑቲን ደግ አደረጉ! ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ጊዜውና መድረኩ ተሰጥቷቸው ቢሆን ኖሮ ስለአሥራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን ታሪክ ገብተው ሲቀባጥሩ መሣቂያ ሊሆኑ አልነበር ?

ፕሬዚደንቱ በመቀጠል፣ «እውነትም ከኢትዮጵያ የተወሰደ ጽንሰ-ኃሣብ ከሆነ መላው አፍሪቃ እንዲያውቀው በአፍሪቃ ኅብረት ሊቀመንበርነትዎ የማስተማር እርምጃ እንደሚወስዱ እገምታለሁ፤» አሉና «ግን ቅድም ለምንድነው ስለ ወጥ ቀማሽ ባህላችሁ የጀመሩት?» ብለው ሲጠይቁ፤ አቶ ኃይለማርያም፣ የአስተማሪያቸውን የአጉል ብልጠት ባህሪ “እንደ መርኅ እንቀጥላለን!” በሚለው መፈከር ይመስላል «እሱንማ» አሉ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ «እዚህ ስብሰባ ላይ እንድገኝ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ካሜሮን ጥሪ ሲደርሰኝ፤ እንደአፍሪቃ ኅብረት ሊቀ መንበርነቴ እንጂ ክቡር፣ ብጹዕ የኔታዬ በተካኑበት ታላቅ ሞያ ለመመረቅ በመባተሌ ሆኖ አላገኘሁትም። ማለትም እሳቸው የናንተን የተከበራችሁ የቡድን ስምንት እና የታናናሾቻችሁን የአሥራ-ሁለቱን መሪዎችን ደኅንነትና ሕይወት ለመታደግ አምና ካምፕ ዴቪድ ከናንተ አስቀድመው የቀመሱላችሁ የግብዣ ወጥ ክፉኛ አሳምሟቸው ለስድስት ክንድ ጉድጓድ እንደዳረጋቸው እየታወቀ “አበበ ገላው የሚባል ስደተኛ ጋዜጠኛ በዓለም ፊት ሲጮህባቸው ቀልባቸውን ገፎ ድንጋጤው ለሞት ዳረጋቸው” የሚል ወሬ እንዲናፈስ አደረጋችሁ። እኛም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን በስንት ተጋድሎ ያገኙትን “የዓለም ዋና ወጥ ቀማሽ” ማዕርጋቸውን ከአገራችን እንዳይነጠቅ እሳቸው የጀመሩትን ሁሉ፤ ራዕያቸውን፤ ህልማቸውንም ሆነ ሁለንተናቸውን (ከጉድጓዱ በቀር!) ለመፈጸም ዝግጁ ነን እያልን ከናንተ ባልተሰወረ የዲፕሎማቲክ ቋንቋ ስንለፍፍ መክረማችን ሥልጣኑ ወደኔ ደቀ-መዝሙራቸው ይሸጋገራል በሚል ነበር።» ሲሉ እንባ እየተናነቃቸው አማረው አመለከቱ።

«እስኪ እግዚአብሔር ያሳይዎ ክቡር ፕሬዚደንት» በማለት አቶ ኃይለ ማርያም ቀጠሉ። «ቅድም እንደገለጽኩልዎት እኛ ለታላላቅ መሪዎች ወጥ ቀማሽ እንደሚያስፈልጋቸው የደረስንበት ከሦስት ሺ ዓመት በፊት ነው። ባለፉትም ሦስት ሺ ዓመታት ተለምዷችን ለመሪ ጥፋት የተቀመመ ወጥ አሽተን እንኳ መለየት የሚያስችል ተሠፍሮ የማያልቅ ዕውቀት ከአባት ወደልጁ ሲወርድ ሲዋረድ የቆየ እሴት ያካበትን ለመሆናችን የኔታዬ (ዝንጋታ ባይጫናቸው ኖሮ!) ዋና ምስክር ናቸው። እኔም ብሆን ከሳቸው የተማርኩት ብቻ ሳይሆን እንደአቅሜ የወረስኩትም ዕውቀት አለኝ። እንደሳቸውም የናንተን የኃያላን መሪዎችን ደኅንነት ለመታደግ ሕይወቴን አሳልፌ ለመስጠትም ዝግጁ መሆኔን ለክቡርነትዎ ላረጋግጥ እወዳለሁ!» በማለት ግልጽ በሆነ መልክ (ኦባማ የሃይለማርያም የስካንዲናቪያ እንግሊዝኛ ትንሽ ቢያስቸግራቸውም) ዓላማቸውን ለመግለጽ ሞከሩ።

ኦባማ ቀበል አረጉና «እና ያሳሰበዎ የአፍሪቃ ኅብረት ሊቀመንበርነቱን ጨርሰው በጊዜ ገደቡ ፍጻሜ ሲያስረክቡ ለወደፊት የቡድን ስምንትም ሆነ የቡድን ሃያ ስብሰባዎች ላይ ማን ወጥ ይቀምስላቸዋል ብለው ነው? » አሉ ፕሬዚደንቱ፣ የምሳ እረፍት ሰዓት እየተገባደደ በመሆኑ ለመመለስ ቸኮል በማለት። «እንዲያው ለነገሩ እኔኮ ይሄንን ዕድል ወስደው ስለቻይና ጉዞዎ፤ ስለሕዳሴ ግድባችሁ፤ የዓለም ባንክ ዓመታዊ እድገታችሁን ዝቅ አድርጎ ስለመገመቱ፤ ስለአፍሪቃ ኅብረት፤ ወይም ስለ ኬንያው ፕሬዚደንት ፍርድ ቤት መቅረብ እና ስለመሳሰሉ ዐበይት ጉዳዮች ያነጋግሩኛል ብዬ ገምቼ ነበር።» በማለት ስሜታቸውን ሳይደብቁ ነው የገለጹላቸው።

«አዩ ክቡር ፕሬዚደንት» አሉ አቶ ኃይለማርያም «የኔ ሥልጣን እና የፖለቲካ ሕይወት የባለራዕዩ ታላቁ መሪያችንን ዕቅድ ያለምንም ማወላወል ሳይበከል፣ ሳይበረዝ፣ እንደወረደ ከግብ ለማግባት ነው። ታዲያ የታላቁ መሪ አንዱና ዐቢይ የነበረው ኃላፊነታቸው በቡድን ስምንት እና ሃያ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት የዓለም ኃያላን አገራት መሪዎች በምግብ እንዳይመረዙ መጠባበቅ ነበር። እኔም ታዲያ የሳቸውን ራዕይ ግብ ለማድረስ የምችለው በናንተ ድጋፍና በጎ ፈቃድ ይሄንን ሥራ በቋሚነት ስመደብ ነው። አዲሱንም የቻይና ፕሬዚደንት አማክሬያቸው በዚህ ጉዳይ እንደሚደግፉኝ፤ እንደውም “አንተ ከሌለህ ቡድን ሃያ ስብሰባ ላይ ድርሽም አልል” ብለውኛል።» በማለት እቅጩን አበሰሩ።

ኦባማ ወደስብሰባቸው እንዲመለሱ ረዳቶቻቸው ስለጠሯቸው «አማካሪዎቼንና ሌሎቹንም መሪዎች አነጋግሬ የወጥ ቀማሹን ሥራ ጉዳይ እናስታውቅዎታለን » ብለው ፈትለክ አሉ። ይሄንን አስገራሚ ውይይት አዳራሹ ውስጥ ለታደሙት እና አፋቸውን ከፍተው ለሚያዳምጧቸው ጓደኞቻቸው ሲያካፍሉ  ነው አጅሬ ፑቲን ዕድሉን በመጠቀም በሶሪያ ላይ ይወሰድ የተባለውን እርምጃ ሊያረሳሱ የቻሉት። (የሶርያ ታጋዮች በዚህ ነገር ቂም ይዘውብን ለጥቃት እንዳንዳረግ አንድዬ ብቻ ይጠብቀን። አሜን!)


በበራ ቁጥር ኢ.ቲ.ኤች 8701 የተመዘገበው የአቶ ኃይለማርያም ጥያራ ከስታንስተድ ተነስቶ በካይሮ በኩል አዲስ አበባ ሲገባ በዐባይ ግድብ ላይ የተሰማሩት መማክርት በሙሉ ወደዚህ የቡድን ስምንት/ሃያ ጉዳይ ላይ ተዛውረው በጥሞና እንዲመክሩና ነሐሴ 30 ቀን ከሚካሄደው የቡድን ሃያ ስብሰባ በፊት ውጤታማነትን የሚያስገኝ የተጠናከረ ስልት እንዲያቀርቡ ያስፈልጋል። እስከዚያው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችንም በምግብ ውስጥ ሊገቡ የሚችሉትን አጥፊ መርዞችና መድኃኒቶችን የመለየት ልምምዳቸውን ይግፉበት እንላለን።

No comments:

Post a Comment

እርስዎስ ምን ይላሉ?