Monday 24 June 2013

የኢትዮጵያ የአበባ ምርት በአፍጋኒስታን ገበያ አገኘ እንዴ ?

ይመኩ ታምራት (ከሎንዶን)

ሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2005 ዓ/ም

ሐቅ! የአየር መንገዳችን የጭነት ጥያራዎች በግንቦት እና በያዝነው ሰኔ ወራት ወደ አፍጋኒስታን ደፋ ቀና ሲሉ ታይተዋል። (Flight Radar24.com ድረ-ገጽን ይመልከቱ)

ሐቅ! አየር መንገዱ ስድስት የጭነት ጥያራዎችን አሰማርቶ በቋሚ መልክ ወደ አውሮፓ፤ መካከለኛው ምሥራቅ እና እስያ ሸቀጣ
ሸቀጥ ያመላልሳል። ኾኖም አፍጋኒስታን በቋሚነት ከሚበርባቸው አገሮች መኻል ያልተመዘገበች ከመሆኗም ባሻገር በጦርነት ከተዘፈቀች አገር ጋር ምን ዓይነት ንግድ ተጀመሮ ይሆን የሚያስብሉ ሰባት በረራዎች ቀልቤን ሊስቡት ችለዋል።

ሐቅ!  አፍጋኖቹ ያለፉትን ሦስት-አሥርት ያህል ዓመታት ያሳለፉት እርስ በርስ በመፋጀት፤ በመፈራረቅ አገራቸውን የያዙባቸውን የሁለቱን ኃያላን መንግሥታት ወራሪ ሠራዊቶች በመከላከል እና በመኻሉም አክራሪ-ሃይማኖተኝነትን መርኅ በማድረግ ነው። የአገራቸው መልክዓ-ምድር እንደ ኢትዮጵያ ተራራማ ከመኾኑም ባሻገር የገጠሩ ዜጋ አኗኗር የኛውኑ ገጠሬ ጋር ይመሳሰላል። በጎቻቸው እንኳ በላት ምትክ ቂጣሞች ይሁኑ እንጂ የኛውኑ የአዳል ሙክት ነው የሚመስሉት።  ግን ከኋላቸው ሲያስጠ................ሉ!!


እንግዲህ ለዚህ መጣጥፍ መነሻ የሆነኝ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ልዩ የጭነት በረራዎች በግንቦት ወር አራት (የመጀመሪያው በረራ ግንቦት 14 ቀን 2005 ዓ/ም ነበር) ጊዜ እና በያዝነው የሰኔ ወር ደግሞ ሦስት ተመሳሳይ በረራዎች (ወሩ ገና ስላላለቀ ሌሎችም ሊኖሩ ይችላሉ!) የአሜሪካ ሠራዊት የሚጠቀምበትን የካንዳሃር ጥያራ ጣቢያ ሲጠቀሙ መገንዘቤ ነው። ለአሜሪካ ሠራዊት የቀንድ ከብት ጭነው ይኾን እንዴ ? አይ ግዴላችሁም አበባ መሆን አለበት! ግን አንዱ በረራ ከሊዬዥ ቤልጂግ ተነስቶ ካንዳሃር ካረፈ በኋላ መልሱን በሆንግ ኮንግ በኩል ሲያደርግ ነዋ የታየው። ስለዚህ ጭነቱ አበባ ቢሆን ኖሮ ከአዲስ አበባ፣ ሊዬዥ፤ ከሊዬዥ ዱባይ፤ ከዱባይ ካንዳሃር እስከሚገባ አበባው የሚጠወልግ እና የኪሣራ ኪሣራ ነው የሚሆነው።
ወይ ከአፍጋኒስታን እነኛን የአዳል ሙክት የሚመስሉትን በጎች መንግሥታችን ሸምቶልን ይሆናላ! አይ፣ ወይ የሁዳዴ ወይ የረመዳን
ጾም መፍቻ ወቅት ቢሆን ኖሮ በግ ተሸምቶልን ነው ለማለት ይቻል ይሆን ነበር። በግንቦትና በሰኔ ወራት ግን አይመስልም። ቢሆንም እንኳ እነኚህ በጎች ለሽምጥ ውጊያ ፈንጂ በቂጣቸው ወሽቀው ይዞራሉ የሚል ስጋት ስላለ፣ እያንዳንዳቸው በደኅንነትና ጥበቃ መሣሪያ፤ መጀመሪያ እተሠማሩበት ሜዳ ላይ፣ ለሁለተኛ ጊዜ ጥያራ ጣቢያው ቅጥር ግቢ ሲደርሱ፣ ለሦስተኛ ጊዜ ደግሞ ጥያራው ላይ ሲጫኑ መፈተሽ ስላለባቸው፤ እንደኔ እንደኔ ጾማችንን በጎመን ብንፈታ ይሻለናል ባይ ነኝ። 

እሺ! አየር መንገዳችን ሠራተኞቹን በጭነት አውሮፕላን እያጓጓዘ የዓመት እረፍታችውን በራሱ ወጭ አፍጋኒስታን ወስዶ ማዝናናት ጀመረ እንዴ ? እንደዚያ ከሆነ ጎረቤት አገር ኬንያ እየወሰደ ቢያዝናናቸው ወጭው አይቀልለትም ኖሯል ? ደግሞስ ጦርነት እሚካሄድበት አገር ወስዶ ለአደጋ ቢያጋልጣቸው የዋስትና ሽፋኑ አይከሽፍበትም ? አይ ምክንያቱ ይኼም ሊሆን አይችልም። በነገራችን ላይ ምንም ጭኖ ወይም ለመጫን ይሁን አፍጋኒስታን የሄደው በሽብር መኻል ጥያራው የተንኮል አደጋ ቢደርስበት የአየር መንገዱ ዋስትና ይሸፍነው ይኾን ?

ታዲያ በሰባት ጠብድያ የጭነት ጥያራዎች የተጓጓዘው ምንድነው እንበል ? ምነው ዴሞክራሲ እና ግልጽነት በሰፈነበት አገር ተወልደን በሆነ ኖሮ? አየር መንገዳችን በየአንዳንዱ በረራው  ከየት ተነስቶ ወዴት፤ ምን ጭኖ እንደሚንቀሳቀስ፤ ጥያራዎቹን ስንገዛ ያባከንነው ገንዘባችን ለኛው ትርፍ እየተሰራበት መሆን አለመሆኑን እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎቻችንን የመጠየቅ ብቻ ሳይሆን አጥጋቢ መልስ የማግኘት መብትም ይኖረን ነበር።

ቆይ ቆይ! የአሜሪካ ሠራዊት ከአፍጋኒስታን የመውጣት ዝግጅቱን እያጧጧፈ ነው የሚል ትንተና አንብቤ የለም እንዴ? አዎ! ሠራዊቱ ቁሳቁሱን አጠቃሎ እ.አ.አ. 2014 መጨረሻ በፊት እንዲወጣ በተወሰነው መሠረት የጊዜ ገደቡ ከመድረሱ በፊት ለማገባደድ ዝግጅቱን እያመቻቸ ይገኛል። የተከማቸውን የጦር መሣሪያ በያይነቱ፤ የመመላለሻ መኪናዎች፤ የተቀበረም ኾነ በሽምጥ የተነጣጠረ ፈንጂ መቋቋም የሚችሉ ተንቀሳቃሾችን (በእንግሊዝኛው  Mine- Resistant Ambush Protected (MRAP) vehicles ይሏቸዋል) ማንሳት ይጠይቃል። ታዲያ ዕድሜ ለኅብረ-መረብ (ኢንተርኔት)፤ ሰሞኑን ያነበብኳቸው መጣጥፎች እንደሚገልጹት፣ ከአሜሪካው ዜጋና የሕዝብ ተወካዮች ሸንጎ የተደበቀ መፍትሄ ቢሆንም የሠራዊቱ ዓለቆች ከሃያ በመቶ (በግምት ሰባት ቢሊዮን ዶላር)  የሚኾነውን የጦር መሣሪያና ተሽከርካሪዎች፤ የመገናኛ ቁሳ-ቁሶችና ንብረት — አላስፈላጊ ወይም ወደአሜሪካ የማጓጓዣው ወጭ ይከብዳል የሚል ውሳኔ ላይ ደርሰዋል — ከቻሉ ወዳጅ አገራት በራሳቸው ወጭ አስነስተው መውሰድ እንደሚችሉ፤ በዚህ ዓይነት ያልተነሳውን (ብልጫውን) ደግሞ እዚያው አፍጋኒስታን ውስጥ በመሰባበር ማውደም ላይ መኾናቸው ተዘግቧል። 

ለምሣሌ የአሜሪካው ሠራዊት በአፍጋኒስታን ካሰማራቸው አሥራ-አንድ ሺ (ልድገመውና አሥራ-አንድ ሺ) ኤም. አር. ኤ. ፒ. መኪናዎች (እያንዳንዳቸው አንድ ሚሊዮን ብር ነው ያወጡት! ይቅርታ የአሜሪካ ዶላር ማለቴ ነው) ሁለት ሺዎቹን መልሶ እንደማይወስድ (ከነኚህም አብዛኛዎቹ ማጓጓዣቸውን አመቻችቶ የሚወስድ ወዳጅ አገር ስለሌለ እዚያው እንደሚሰባበሩ) ቀሪዎቹ ዘጠኝ ሺ መኪናዎች ደግሞ ወደአሜሪካ እና በየአገሩ ወደተሠማሩት የአሜሪካ ሠራዊት እዞች (ይሄም ኢትዮጵያን ሊመለከት ይችላል) እንደሚላኩ  የፔንታጎን ቃል አቀባዮች መግለጻቸውን አንብቤያለሁ። ጉድ እኮ ነው!

ታዲያ ወያኔ ምኑ ሞኝ ነው! የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጭነት ጥያራዎችን አሰማርቶ በነፃ የሚገኘውን መሣሪያ እና ኤም. አር. ኤ. ፒ. መኪናዎች ለማንሳት ነዋ ወደካንዳሃር ያዘዛቸው! በርሮበት ወደማያውቀው ጥያራ ጣቢያ፤ የኔ ብጤውን ተከታታይ ለማደናበር ሰባቱንም በረራዎች ከካንዳሃር በቀጥታ ወደሆንግ ኮንግ በማብረር (መሠረታዊ የጭነት በረራ መሥመር ባይሆንም እንኳ ሆንክ ኮንግ ከካንዳሃር የተሻለ ታማኝነት ይኖረዋል) ያለጥርጥር መሣሪያውን በምሥጢር እያጓጓዙ ነው ወደሚለው ድምዳሜ  በበኩሌ የደረስኩ መሆኔ ይሰመርልኝ።  

መችም “የስጦታ ፈረስ ጥርሱ አይገለጥም” የሚባለው የአባቶች ብሒል አይታዘበኝና፤  ገዢው የወያኔ ኃይል ዘጠና ዘጠኝ ነጥብ ስድስት ከመቶውን ወንበር በሚቆጣጠርበት “የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት” (ድንቄም የሕዝብ ውከላ እቴ!) ያሉት አንድዬው ተቃዋሚ አቶ ግርማ ሰይፉ እውነታውን ተገንዝበው ጥያቄ ቢያቀርቡም እንኳን  ምናልባት ከአቶ መለስ የለመድነውን የትዕቢት ዘለፋ ከማትረፍ በቀር እውነት ያለበትን ጎራ እንኳ አቅጣጫ ይጠቆማሉ ብሎ ማሰብ ከንቱ ነው። እንኳን የአሜሪካኖቹ ትርፍራፊ በኛው ላይ ሊነጣጠር የታሰበ ሊሆን እንደሚችል  ሊነገረን ቀርቶ ለምጽዋቱ እንኳን እንደባህላችን “እግዚአብሔር ይስጥልን” ለማለት አይፈቀድልንም። ታዲያ አቶ ኦባንግ ሐሙስ ዕለት በአሜሪካው ኮንግረስ ላይ “እራሳችንን እኛው ነፃ እናወጣለን። እናንተ ግን የመንገድ እንቅፋት አትሁኑብን!” ያሉዋቸውን በአንድ ፊት እናዳምጣለን የሚሉን አሜሪካኖች በጎን ወያኔን በምስጢር እስከቅንድቡ ድረስ እያስታጠቁት ነው።

እንግዲህ ለተጋለጡት በረራዎች የወያኔ አካላትም ሆኑ ደጋፊዎቻቸው ምክንያት አድርገው ሊያቀርቡ የሚችሏቸውን መልሶች በመንደርደሪያዬ ላይ እንደሸፈንኳቸው ተስፋ እያደርግሁ ያልተለመደ፤ ያልተገለጸ፤ የንግድ ዓላማ ሊኖረው የማይችል እና ማደናበሪያ አቅጣጫዎችን ያካተተ  ከካንዳሃር አፍጋኒስታን የሚነሱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጭነት ጥያራ በረራዎች የጦር መሣሪያዎችንና  ወታደራዊ ቁሳ-ቁሶችን ለማንሳት ካልሆነ በቀር ሌላ ምክንያት አልታየኝም። ካንባብያን መኻል የምርምር ጋዜጠኞችም አይጠፉምና ጉዳዩን ጠለቅ ብለው ቢመረምሩት ደግሞ እውነታውን በተሻለ መልክ ልንረዳው እንችል ይሆናል።

ይልቁንስ ተቃዋሚ ቡድኖች ካሁኑ ማንሳት ያለባቸው 1) አሜሪካኖቹ በነፃ ውሰዱ ያሉትን ከፍ ያለ ዋጋ ከፈልንበት ብለው የለመዱትን ብዝበዛ እንዳያካሂዱ  2) ምስር ልትወጋን እየተነሳሳች ስለሆነ መከላከያ መሣሪያ ብለን ነው እንዳይሉ ከምስር ጋር እያካሄዱት ያለው የአፍ ጦርነት በሁለቱም በኩል የገዥ አካላቱን ዕድሜ ማራዘሚያ ስልት እንጂ ሌላ ምንም ትርጉም የሌለው መሆኑን 3) ምዕራባውያን በፊት ለፊት የዴሞክራሲ፣ የሰብአዊ መብት፣ ወዘተ ደጋፊናተቸውን በመለፈፍ እየሸነገሉ በኋላው በር ግን እኛኑ የሚያስቀጥቀጥ ግፊታቸውን እንደማያቆሙ እንደነቃንባቸው ማሳወቅ ነው።


ምንጮች

No comments:

Post a Comment

እርስዎስ ምን ይላሉ?