Sunday 14 April 2013

“ተፈራ ደገፌ በቫንኩቨር ፀጉር ማስተካከያ ቤት የዘረኝነት መድሎ ተፈጸመብኝ አለ”


ኼንን ዘገባ ይዞ የቀረበው ጋዜጣ “የዕለቱ ዩቢሲ” (The Daily Ubyssey) የሚባለው የ’ብሪቲሽ ኮለምቢያ ዩኒቨርሲቲ’ ልሣን ሲሆን ታሪኩን ያዘለው ዕትም ለንባብ የቀረበው ዓርብ መስከረም ፲፭ ቀን /ም ነበር።  ልክ ነዎት አልተሳሳቱም! አሥራ ዘጠኝ መቶ አርባ ዓመተ ምሕረት፤ የዛሬ ስድሳ ስድስት ዓመት ማለት ነው!


በዘረኝነት ተጠቃሁ ባዩም ከአንድ ዓመት በፊት ወደሰሜን አሜሪካ በማቅናት የንግድና የባንክ ትምህርት ለመቅሰም እዚያው የብሪቲሽ ኮለምቢያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበረ ኢትዮጵያዊ ወጣት ነው።  ታዲያ ይኽ ወጣት የመስከረም ሚካኤል ዕለት (ምናልባት ለመስቀል ዝግጅት ሊሆን ይችላል!) ፀጉሩን ሊከረከም አስተካካይ ቤት ይገባል። ከሦስቱ ወንበሮች ግራና ቀኝ ሁለት ነጮች ፅጉራቸውን ይስተካከላሉ። መሃለኛው ወንበር ባዶ ስለነበር፣ ተማሪው እዚያ ላይ ተቀምጦ ባለሙያውን ይጠባበቃል። የባዶው ወንበር ጌታ ጠና ያለ፣ ሰነፍ ብጤ ካናዳዊ ነው። ተማሪው ማስተካከያ ቤቱ ሲገባም ኾነ ወንበሩ ላይ ሲቀመጥ በሰመመን ላይ ከነበረበት መቀመጫው ልውስም አላለ።

ተማሪው ስለዚህ ክስተት ለከተማው ጋዜጣ በላከው የክስ ደብዳቤ ላይ፣ “በመደነቅ ቀና ብሎ ሲያየኝ ጅላጅል ፊቱ ላይ የሚነበበው በጠባብ አዕምሮው የመተማመን መሐይምነት ነው።” በሚል ነው የገለጸው። “በበቂ የልብ ድፍረት ራሱን ካበረታታ በኋላ በሚንቀጠቀጥ ድምጽ ፀጉሬን ለማስተካከል እንደማይችል አበሰረኝ።” ይላል ወጣቱ አፍሪቃዊ ተማሪ።

በምን ምክንያት? ለሚለው የተማሪው ጥያቄ መልስ ያልነበረው ፀጉር ቆራጭ፤ “ይኼ አቋምህ ለሁሉም ጎብኝ እንግዶችና ለኢትዮጵያውያንም ነው?” ሲለው ግን የተገልጋዩ ዜግነት በዚህ አቋም ምንም ፋይዳ እንደሌለው ነው ያበሠረው።

ይኼ ወሬ በዩኒቨርሲቲው ሲሰማ ጋዜጣው ያነጋገራቸው አንዳንድ ተማሪዎች በሰጡት አስተያየት በከተማቸው እንደዚህ ዓይነት ድርጊት መፈጸሙ እንዳስገረማቸው ከመዘገቡም ባሻገር፣ አንዳንድ ተማሪዎች ደግሞ ተፈራ ጉዳዩን አብሰልስሎ ሳያይ በአንድ ክስተት ላይ ብቻ ተመርኩዞ በችኮላ ድምዳሜ ላይ እንደደረሰ መግለጻቸውን ጋዜጣው አስነብቧል።  ዘገባውንም ሚዛናዊ ለማድረግ ጋዜጣው የፀጉር አስተካካዮች ማኅበር ዋና ፀሐፊንም አስተያየት አካቷል። ፀሐፊው የማኅበሩ አባላት በጥቁሮች ላይ የዘረኝነት መድሎ እንደማይፈጸሙ መናገሩን ካረጋገጠ በኋላ ሊከሰት የሚችለው አለመግባባት እንደየሱቁ ባለቤት አስተያየት መኾኑንም ለጋዜጣው ገልጿል፡፡

ወጣቱ ኢትዮጵያዊ ተማሪ ተፈራ ደገፌ ለጋዜጣው እንዳስረዳው፤ የአንዳንዶችን ዘረኝነት ቢገነዘብም በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የጎላ የቀለም ጥላቻ እንዳልተገነዘበ ገልጾልናል ይልና “ጥሩ የፒያኖ ሙዚቃ ለማዳመጥ ጥቁሮቹም  ነጮቹም የጣት ሰሌዳዎች እንደሚያስፈልጉ” በመግለጽ በሳል አመለካከቱን ለጋዜጣው አካፍሏል።  

የዚህ መጣጥፍ ዓላማ የተማሪውን የሕይወት ታሪክ ለማስነበብ ባይሆንም ለግንዛቤ ያህል ግን ይኽ ወጣት ኢትዮጵያዊ የሸዋ ነገሥታት መዲና በነበረችው አንኮበር ከተማ ላይ በ፲፱፻፲፰ ዓ/ም የተወለደው ተፈራ ደገፌ ሲሆን ለከፍተኛ ትምህርት ወደካናዳ ከማምራቱ ሁለት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተቀጥሮ ይሠራ እንደነበር፤ ከዚያም መጀመሪያ በካልጋሪ በኋላም በብሪቲሽ ኮለምቢያ ዩኒቨርሲቲ በንግድ ጥናት የመጀመሪያ ዲግሪ መመረቁን፤ እስከ ፲፱፻፵፭ ዓ/ም እዚያው ካናዳ በሕግ ሙያ ዕውቀቱን ሲያዳብር ከቆየ በኋላ ወደአገሩ ተመልሶ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በነገረፈጅነት ተቀጥሮ አገልግሏል።  ወዲያውም ከአዲስ አበባው ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በሕግ ሙያ ዲፕሎማ ተመርቋል።

አቶ ተፈራ ደገፌ በዓፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ለአገራቸው ካገለገሉባቸው ሥራዎች አንዱ የሲቪል አቪዬሽን ዳይሬክቶርነትም እንደነበር አጭር የሕይወት ታሪካቸው ያመለክታል። ዋናውና ብዙ ዕውቅና ያፈራላቸው ሥራ ግን በባንክ አገልግሎት ዘርፍ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንብ የካርቱም ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ፤ የብሔራዊ ባንኩ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ፤ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚደንት፤ የአዲስ አበባ ሮታሪ ክበብ አባል እና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የክብር ሒሣብ ሹም ሆነው አገልግለዋል።

ታዲያ ያን ዕለት በጭፍን የዘረኝነት አመለካከት ወጣቱን ተማሪ ከከርዳዳ ፀጉሩ አልፎ ሰብዕናውን ለማየት ያልቻለው ፀጉር አስተካካይ፤ ተፈራ ደገፌ ወደፊት የአገሩ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እንደሚሆን ቢታየው ኖሮ ምን ይሆን አቋሙ?  ከሃያ ስድስት ዓመታትስ በኋላ የብሪቲሽ ኮለምቢያ ዩኒቨርሲቲ ይሄንኑ ኢትዮጵያዊ “የተለየ እና የሚደነቅ የመሪነት ብቃት ያለው” በሚል ማሞካሻ  ግንቦት ፪ ቀን ፲፱፻፷፮ ዓመተ ምሕረት የክብር የሕግ ዶክቶሬት ዲግሪ (DOCTOR OF LAWS (honoris  causa)[1] እንደሚሸልመው ለዚያ ፀጉር አስተካካይ ቢታየው ኖሮ ያን ዕለት በምን ዓይነት መስተንግዶ ይሸኘው ኖሯል? ወደፊትስ በኢትዮጵያ  የኖርዌይ መንግሥት ቆንስላ ሆኖ በማገልገሉ የኖርዌይ ንጉሥ ሃራልድ አምስተኛ የአገራቸውን የአገልግሎት ኒሻን[2] እንደሚሸልሙት ቢያውቅ ኖሮ የዚያን ዕለት ድርጊቱ የቱን ያህል ባሳፈረውና በቆጨው።



[1] THE TITLE AND DEGREE OF DOCTOR OF LAWS (honoris causa) CONFERRED AT CONGREGATION, MAY 30, 1974 - TAFFARA DEGUEFE

No comments:

Post a Comment

እርስዎስ ምን ይላሉ?